1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ

ረቡዕ፣ መጋቢት 18 2005

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ትናንት የሀገሪቱን ደቡባዊ የወደብ ከተማ ኪስማዮን መጎብኘታቸዉ ተገልጿል። አንድ የሶማሊያ መንግስት መሪ ኪስማዮን ሲጎበኝ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲ ሺርዶን ሳይድ የመጀመሪያዉ ናቸዉ። ኪስማዮ በአሸባብ ቁጥጥር የቆየች ከተማ ነች።

https://p.dw.com/p/1859A
ምስል Reuters

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲ ሺርዶን ሳይድ ሥልታዊቱን ከተማ የጎበኙት ዋና ዓላማ የአካባቢዉ ማኅበረሰብ መሪዎችን ለመነጋገር ነዉ። ከዋና ከተማ መቃዲሾ በስተደቡብ በ500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ ኪስማዮ ላለፉት ሶስት ዓመታት በላይ በአሸባብ ጠንካራ ይዞታነት ቆይታለች። አሸባብ ባለፈዉ ጥቅምት ወር በአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ስር በተንቀሳቀሰዉ የኬንያ መከላከያ ሠራዊት በተሰነዘረበት ጥቃት ነዉ ኪስማዮን የለቀቀዉ። ከተማዋ ከእስላማዊዉ ተዋጊ አሸባብ ኃይሎች ቁጥጥር ነፃ ብትሆንም በጎሳዎች መካከል የተነሳዉ የይገባኝል ጥያቄ ፀጥታዋን ስጋት ላይ ጥሏል። ጋዜጠኛ መሀመድ ዑመር ሁሴይን እንደሚለዉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ምክንያት የሆነዉ ይኸዉ በኗሪዎቹ ማህበረሰቦች መካከል የተነሳዉ ዉዝግብ ነዉ፤

Somalia Soldaten
ምስል dapd

«ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ ምክንያት የሆነዉ ኪስማዮ የሚኖሩ ኅብረተሰቦች መካከል የተነሳዉ አለመግባባት ነዉ። ይኸዉም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎሳ እና ኦጋዴን በሚባለዉ ጎሳ መካከል ነዉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደዚያ የሄዱት ሁለቱን ማህበረሰቦች ለመሸምገልና ዉዝግባቸዉን በጥሩ መንገድ ፈትቶ ወደአንድነት ለማምጣት ነዉ። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማኅበረሰሙ መሪዎችና የከተማዋ አዋቂዎች ጋ ካካሄዱት ስብሰባ እስካሁን የተገኘ ዉጤት የለም።»

ጋዜጠኛዉ እንደሚለዉ ኪስማዮ የሚኖሩትን የጠቅላይ ሚኒስትር አብዲ ሺርዶን ሳይድ ጎሳ መሬሃን እና የኦጋዴን ጎሳ አባላትን የሚያነታርከዉ ከተማዋ የኔ ነች የኔ የሚለዉ የይገባኛል ጥያቄ ነዉ። በዚህ መልኩ በመካከላቸዉ የተባባሰዉ ፍጥጫም በአንድ ቀን ዉይይት ሊፈታ የሚችል አይመስልም፤

«በመሠረቱ በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል ኪስማዮ ከተማ የሚካሄደዉ ዉይይት ረዥም ጊዜ የሚፈጅ ነዉ የሚሆነዉ። ምክንያቱም እያንዳንዱ ጎሳ ከተማዉ በራሱ ቁጥጥር ስር እንድትሆን የሚፈልገዉ። ኦጋዴኖች ኪስማዮ ከተማ የእኛ ነዉ ይላሉ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎሳ መርሃን የሚባለዉም እንዲሁ ከተማ የእነሱ እንደሆነች ያጠይቃሉ።»

ኪስማዮ ከተማ ከአሸባብ ይዞታነት ተላቃ በሶማሊያ መንግስት ወታደሮች፤ እንዲሁም የአፍሪቃ ኅብረት ኃይሎች ሙሉ ቁጥጥር ስር ናት ቢባልም ፀጥታዋ የተረጋጋ አለመሆኗን ነዉ ጋዜጠኛ መሐመድ ዑመር ሁሴይን ያመለከተዉ። ከሁለቱ ወገኖች ሌላ አሸባብን ከስፍራዉ ለማስወጣት በተካሄደዉ ዉጊያ የተሳተፈዉ ራስካምቦኒ የተባለዉ የሶማሊያ አማፂ ቡድንም እዚያዉ ይገኛል። አሸባብ አልፎ አልፎ በአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ኬላ እና የሶማሊያ ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሶ የሚሰወርበት ሁኔታ መኖሩንም ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ወቅት ግን ጥብቅ የፀጥታ ጥበቃ እንደነበረ ነዉ መሀመድ የጠቆመዉ፤

Somalia Soldaten
ምስል picture-alliance/dpa

«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኪስማዮ ሲደርሱ የፀጥታ ጥበቃዉ ከአዉሮፕላን ማረፊያ አንስቶ የማኅበረሰቡን መሪዎች እስካነጋገሩበት ስፍራ ድረስ እጅግ ጥብቅ ነበር። የኬንያ ወታደሮች ናቸዉ ጥበቃዉን ያጠናከሩት ነገር ግን ባጠቃልይና በመሠረቱ የኪስማዮ የፀጥታ ሁኔታ የተረጋጋ ነዉ የሚባል አይደለም። በከተማዋ ተከታታይ ዉጊያ በርግጥ የለም ሆኖም በሁለት ወይ ሶስት ቀናቱ ከተማዋ ዉስጥ ወይም አቅራቢያዋ ዉጊያ አለ።»

የሶማሊያ ከተሞች ከጥቂት ወራት ወዲህ ዉጊያ ግጭቱ ሰክኖላቸዉ የተረጋጉ ቢመስልም የሰዎች ህይወት በታጣቂዎች መቀጠፉ ግን አሁንም አልተገታም። ጋዜጠኛ መሐመድ እንደሚለዉ ኪስማዮ ዉስጥ በየምሽቱ ቢያንስ የአንድ ታዋቂ ሰዉ ህይወት ያልፋል። መቃዲሾ ከተማም እንዲሁ እሁድ ምሽት አንዲት ጋዜጠኛ ተገድላለች። ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች እንዳስታወቀዉ ጋዜጠኛ ራህሞ አብዱልቃድር ከሁለት ሰዎች በተተኮሰባት አምስት ጥይት መንገድ ላይ ህይወቷን አጥታለች። ለጋዜጠኛዋ ህልፈት ኃላፊነት የወሰደ ቡድን እስካሁን የለም። ባለፉት ሶስት ወራት ዉስጥ ሶማሊያ ዉስጥ የተገደሉ ጋዜጠኞች ሶስት ደርሰዋል፤ ባለፈዉ ዓመት የወጡ ዘገባዎች ሶማሊያን ለጋዜጠኞች ተግባር እጅግ አደገኛ ብለዋታል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ