1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ጊዜያዊ ሁኔታ

ረቡዕ፣ የካቲት 14 1999

በሶማሊያ መዲና መቃዲሾ ሁኔታዎች እየተባባሱ መሄዳቸዉ ይሰማል። በዛሬዉ ዕለትም እዛዉ የሚገኙት ታጣቂዎች ወደሶማሊያ ይገባል ተብሎ ለሚጠበቀዉ የሰላም አስከባሪ ኃይል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/E0Yh
በፈንጂ የነጎደ ተሽከርካሪ
በፈንጂ የነጎደ ተሽከርካሪምስል AP

በከተማዋ ከሰኞ ጀምሮ በደርሰዉ የመሳሪያ ልዉዉጥም ወገኖቻቸዉን ያጡ ቤተሰቦች ሲቀብሩ መዋላቸዉ ተገልጿል። ሰኞ ማታ በተለይ በተካሄደዉ የተኩስ ልዉዉጥም 15ሰዎች ህይወታቸዉን አጥተዋል 45ሰዎች ቆስለዋል። የከተማዋ ኗሪ የሆነዉ ጋዜጠኛ አዌስ ኦስማን ዩሱፍ ሁኔታዉን እንዲህ ይገልፃል።

«በሶማሊያ ሁኔታዉ ዉጥረት የነገሰበት ነዉ። የከተማዋ ኗሪዎች ቤታቸዉን ትተዉ መሸሽ ጀምረዋል። ይህ የሆነዉ ባልታወቁ ታጣቂዎችና በኢትዮጵያና በመንግስት ወታደሮች መካከል ሰኞ ማታ የተኩስ ልዉዉጥ ከተደረገ በኋላ ነዉ። ከሁለት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደከተማዋ ከገቡ ወዲህ ይህ የደረሰዉ ጥቃት ከሁሉ የከፋና አደገኛ ነበር። በዚህም 13 ሰዎች እንደሞቱና ወደ42የሚደርሱ ሰዎች በዚሁ የተኩስ ልዉዉጥ መጎዳታቸዉ ይታመናል።»

ይኸዉ የአይን ምስክር እንደሚለዉ በዛሬዉ ዕለት ጠዋት በርካታ ሰዎች ከተማዋን ለቅቀዉ ለመዉጣት ሲሞክሩ ታይቷል። ሰዎቹ የሚሸሹት ምናልባት ከመቃዲሾ ከተማ መጠነኛ መረጋጋት ወዳለባቸዉ ከተሞች ነዉ። ለመሆኑ እነዚህ ወገኖች ወደሌላ የአገሪቱ ክፍሎች ለመሸሽ መሞከራቸዉ ተኩስና ፍንዳታዉ መቃዲሾ ከተማ ብቻ ስለሆነ ነዉ?

«በአሁኑ ጊዜ ሁኔታዎች በጣም የከፉባት መቃዲሾ ናት። በሌሎቹም የአገሪቱ ክፍሎች በእርግጥም የደህንነት ስጋት አለ። ስርቆት ይፈፀማል። የታጠቁ ዘራፊዎች ህዝቡን እየዘረፉ ነዉ። እዚህ መቃዲሾ ግን ባልታወቁ ታጣቂዎችና በኢትዮጵያ ወታደሮች በሚታገዙ የመንግስት ወታደሮች መካከል ጦርነት ተከፍቷል። ኗሪዎቹ የሚሸሹበት ምክንያትም በሚካሄደዉ ጦርነት ሰለባ ስለሆኑ ነዉ።»

በርካታ የዜና አዉታሮች በመዲናዋ መቃዲሾ እየተካሄደ ስላለዉ የተኩስ ልዉዉጥና ስለከተማዋ አለመጋጋት መዘገባቸዉን ቀጥለዋል። በአንድ ወገን በኢትዮጵያ የሚደረገፈዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ወታደሮች በሌላ ወገን የታጠቁ ኃይላት የተኩስ ልዉዉጡን መቀጠላቸዉ ይነገራል። በእርግጥ እነዚህ የታጠቁ ኃይላት ይታወቁ ይሆኖ? ፍልሚያዉስ በማንና በማን መካከል ነዉ መናገር ይቻላል?

«እየሆነ ያለዉ ምንድነዉ፣ ያልታወቁ ታጣቂዎች አሉ፣ ማንነታቸዉ ያልታወቀ የታጠቁ ሰዎች ቦምቦችና ሞርታር ጥይቶችን መቃዲሾ ወደሚገኘዉ የኢትዮጵያና የመንግስት ወታደራዊ ሰፈሮች ይተኩሳሉ። የኢትዮጵያና የመንግስት ወታደሮች ደግሞ የአፀፋ ተኩስ እንዳገኙ በተመሳሳይ መሳሪያዎች ወደመኖሪያ መንደሮች ይተኩሳሉ። ይህ በእርግጥ በርካታዎች እንዲሞቱና እንዲጎዱ ምክንያት ሆኗል። ጦርነቱ አለ። በኢትዮፕያና በመንግስት ወታደሮች እንዲሁም ባልታወቁ መሳሪያ አንጋቾች ማንነታቸዉን በእርግጥ አናዉቅም። ለዚህ ሁሉ ድርጊትም ሃላፊነት የወሰዱ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች እስካሁን የሉም።»

የከተማዋ ሁኔታ እንዲህ ከድጡ ወደማጡ እየወረደ ባለበት ሰዓት በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች እየተረዳ ከባይደዋ ወደመዲናዋ የገባዉ የሽግግር መንግስት በከተማዋ በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ላይ ይዞታዉን ማጥበቁ ተነግሯል። ትናንት የተሰሙ ዘገባዎች ሶስት የራዲዮ ታቢያዎች መዘጋታቸዉን ገልፀዋል። ጋዜጠኛዉ እንደሚለዉ በከተማዋ ስለሚካሄደዉ ጦርነትና ስለሚገደሉት ንፁሃን ዜጎች ዘገባ ማቅረብ የለባችሁም በሚል ለሶስት FM ራዲዮ ጣቢያዎች ላይ የዘገባ እገዳ ተጥሏል።

«አልታገዱም ማስጠንቀቂያ ነዉ የተሰጣቸዉ። በከተማዋ ስላለዉ ሁኔታ እእዳይዘግቡ እገዳ ብጤ ነዉ የተጣለባቸዉ። ስለዚህም መዘገብ አቁመዋል። መንግስት ለራዲዮ ጣቢያዎቹ ምን ምን ላይ መዘገብ እንደሚችሉና የትኞቹን ደግሞ እንደማይችሉ መመሪያ ሰጥቷቸዋል።»

የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት የአፍሪቃ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ሁኔታዎችን እንዲያረጋጋ ወደሶማሊያ እንዲገባ ማዘዙን ተከትሎ ከታጣቂዎቹ ወገን የተቃዉሞ ድምፅ ተሰምቷል። በሶማሊያ የጥቃት እርምጃዉን የሚወስዱት ታጣቂዎች መሪ መሆናቸዉ የተጠቆመዉ አንድ ታጣቂም የመንግስታቱ ድርጅት በአገራቸዉ ጉዳይ እጁን ከማስገባት እንዲታቀብ ማስጠንቀቂያ ሰንዝረዋል። ሰማያዊም ሆነ ጥቁር መለዮ ያደረጉ የዉጪ ወታደሮች ወደሶማሊያ ቢገቡ እስላማዊዉ ቡድን እነሱን ለመፋለም ዝግጁ ነዉ ማለታቸዉም ተዘግቧል።