1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ጋዜጠኞችና የመንግሥት እርምጃ

ሐሙስ፣ የካቲት 7 2005

« በአንድ በኩል ባለሥልጣናቱ ለማናቸውም መሠረታዊ ነፃነቶች ያልተገደቡ መሆናቸውን መናገራቸው ፤ በሌላ በኩል በዚህ ጉዳይ በጋዜጠኞች ላይ ለሚፈፀም አፈና ተጠያቂ መሆናቸው ያሳስበናል ።» የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ድርጅት RSF የአፍሪቃ ክፍል ሃላፊ አምብሯዝ ፕየር

https://p.dw.com/p/17eLJ

በጎርጎሮሳውያኑ 2012 አም ጋዜጠኞች በብዛት ከተገደሉባቸው ሃገሮች ግንባር ቀደሟ ሶማሊያ ናት ። በዚሁ አመት ፣ 18 ጋዜጠኞች ሶማሊያ ውስጥ በታጣቂዎች አለያም በተጠመዱ ቦምቦች ተገድለዋል ። እ.ጎ.አ በ2013 አም የሶማሊያ ጋዜጠኞችን የሚያሰጋው ከአክራሪ ሙስሊም ኃይሎች የሚሰነዘርባቸው ጥቃት ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከፀጥታ ኀያሎች በኩል የሚደርስባቸው አፈናና ወከባም ጭምር ሆኗል ። በቅርቡ አንዲት በፀጥታ ኅይሎች ተደፈርኩ ያለችን ሴት ያነጋገረ ጋዜጠኛ ተይዞ የ 1 አመት እሥራት ተበይኖበታል ። የጋዜጠኛውን መታሰር የተቸ ሌላ ጋዜጠኛ ደግሞ ለአንድ ሳምንት በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ተለቋል ። እነዚህ  በሶማሊያ የብዙሃን መገናኛዎች አፈና መገለጫ ተደርገው የተወሰዱት እርምጃዎችም ለጋዜጠኞች ና ለሰብአዊ መብት በሚከራከሩ ድርጅቶች ተወግዟል ከነዚህም አንዱ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ድርጅት RSF ነው ። የድርጅቱ የአፍሪቃ ክፍል ሃላፊ አምብሯዝ ፕየር በሶማሊያ ጋዜጠኞች የሚገኙበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ለዶቼቬለ ተናግረዋል

Newly appointed Somalia's Prime Minister Abdi Farah Shirdon Saaid addresses the media in Somalia's capital Mogadishu October 6, 2012. Somali President Hassan Sheikh Mohamud has named Saaid as the country's new prime minister, diplomats and a government source said, the first major decision by an administration installed after over 20 years of conflict. REUTERS/Feisal Omar (SOMALIA - Tags: SOCIETY POLITICS)
ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲ ፋራህ ሺርዶንምስል Reuters

« በሃገሪቱ ፍትህ ማስፈን እንፈልጋለን የሚሉ ባለሥልጣናት አሁን ጋዜጠኞችንም ባቀረቡት ዘገባ ምክንያት እያሰሩ ብዙሃን መገናኛን የሚያፍኑበትን ጊዜ እያየን ነው ። ስለዚህ ይዞታው በጣም ያሳስበናል ። ጋዜጠኞች አሁን በመንግሥት ባለሥልጣናት በዘፈቀደ የመታሰር አዲስ አደጋ ይገጥማቸዋል ብለን እንሰጋለን ። »

ፕየር ተደፈርኩ ያለችውን ሴት ካነጋገረ በኋላ የታሰረው ጋዜጠኛ ጉዳይ የተወሳሰበና ለመመዘንም አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመው ሆኖም እርምጃው መልዕክት ያለው መሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም ።

« የምናውቀው ነገር አንድ ጋዜጠኛ ባለሥልጣናትን ለሚተች አንድን ሰው ቃል መጠይቅ በማድረጉ የሚያዝና ወደ ወህኒ የሚወረወር ከሆነ ለብዙሃን መገናኛ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ ። ይኽውም ማድረግ የሚገባህን ማድረግ አይፈቀድልህም ። ማለትም ሥራህንም በነፃነት ማከናወን አትችልም ። ሰዎችንም መጠየቅ አትችልም ። በተለይም የሶማሊያ ባለሥልጣናትንም መተቸት አይፈቀድም ማለት ነው ። »

Reporter ohne Grenzen Logo

ይህ እርምጃም አምብሯዝ ፔር እንደሚሉት ጋዜጠኞች በነፃነት እንዳይዘግቡ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም ።

« ይህ ሁኔታ በስተመጨረሻ የሶማሊያ ጋዜጠኞች ራሳቸውን ሳንሱር እንዲያደርጉ ይገፋፋል ብዮ እሰጋለሁ ። የሶማሊያ ጋዜጠኞች መንግሥትን መተቸት ያሳስረናል ብለው ካሰቡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ላለመዘገብ ይወስናሉ ። »

ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በበርካታ ምዕራባውያን ሃገራት የሚደገፈው የሶማሊያ መንግሥት  በሃገሪቱ ለፕሬስና ሃሳብን ለመግለፅ ነፃነት እንደሚቆም በተደጋጋሚ ቃል ይገባል ። መንግሥት ከጋዜጠኞች ጀርባ እንደሚቆም የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲ ፋራህ ሺርዶን ከትናንት በስተያም ተናግረዋል ። ይሁንና አምብሯዝ ፕየር እንደሚሉት መንግሥት የሚለውና የሚያደርገው ይቃረናል ። ይህም ድርጅታቸውን እንደሚያሳስብ ለሶማሊያ መንግሥት አስታውቀዋል ።

«ባለፈው ሳምንት ለሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ግልፅ ደብዳቤ ልከናል ። በጣም ቀጥተኛና ግልፅ በሆነ መልኩ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሲኮን ማየታችን በጣም እንደሚያስፈራን ገልፀንላቸዋል ። በአንድ በኩል ባለሥልጣናቱ ለማናቸውም መሠረታዊ ነፃነቶች ያልተገደቡ መሆናቸውን መናገራቸው ፤ በሌላ በኩል  በዚህ ጉዳይ በጋዜጠኞች ላይ ለሚፈፀም አፈና ተጠያቂ መሆናቸው ያሳስበናል ።»

Selbstmordattentat in Mogadischu
ምስል dapd

እናም ይላሉ የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ድርጅት የአፍሪቃ ክፍል ሃላፊ አምብሯዝ ፕየር አለም አቀፉ ማህበረሰብ የመንግሥት እርምጃዎች በጥንቃቄ ሊከታተል ይገባል ።

«አለም አቀፉ ማህበረሰብ እነዚህን ባለሥልጣናት ይደግፋል ። በሶማሊያም ቋሚ መንግሥት እንዲመሰረትና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ብዙ ገንዘብ አፍሰዋል ። ስለዚህ በሃገሪቱ የሚሆነውን ሁሉ በጥንቃቄ መከታተል አለብን አለም አቀፉ ማህብረሰብ ለባለሥልጣናቱ ድጋፍ መስጠቱን መቀጠል አለበት ብዮ አስባለሁ ። ሆኖም እነዚህ ባለሥልጣናት ቃል ከገቡት በተቃራኒው እየሰሩ መሆን አለመሆናቸውን ማረጋገጥ አለበት ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ