1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ግራ አጋቢ ዕዉነታ

ሰኞ፣ ጥር 16 2008

«ጠብ የሚፈልግ ሰዉ ከሱ የበለጠ ጠበኛ ያጋጥመዋል» ብሒልን ከሐሰን ሼኽ ማሕሙድ እኩል አሕመድ ዑመር ወይም አቡ ዑቤይዳሕም ያዉቁታል።ሁለቱም ሶማሌ ናቸዉ።ለምን አይታረቁም።የሊቢያ፤የየመን፤የሶሪያ ተፋላሚዎች ለዕርቅ ከተደራደሩ፤ሳልቫ ኪር፤ ከማቸር፤ ካቡሎች ከታሊባን፤አሜሪካኖች ከኢራን ከተስማሙ፤ ሞቃዲሾች ካሸባብ የማይደራደሩበት ምክንያት ግራ ነዉ

https://p.dw.com/p/1HjhN
ምስል Reuters/F. Omar

የሶማሊያ ግራ አጋቢ ዕዉነታ

የዩጋንዳን ይዞ-የኬንያ፤ የኢትዮጵያን ይዞ-የቡሩንዲ፤ የሴራሊዮንን፤ የጀቡቲን ይዞ የአፍሪቃ፤ ታንክ፤መድፍ፤መትረየስ ከምድር ፤ ጄት ሔሊኮብተሩ ካየር፤ ሶማሊያን ያርሳሉ።ወታደሩ እየገደለ-ይገደላል።የዩናይትድ ስቴትስ የድሮን ሚሳዬል-የሶማሌን አፈር፤ ዛፍ አለት በሶማሌዎች ደም-አጥንት ይለስናል።የአዉሮጳ-አረብ ገንዘብ ይከሰከሳል። የካምፓላ፤ የሞቃዲሾ፤ የናይሮቢ፤ የአዲስ አበባ፤የዋሽግተን፤ የኒዮርክ፤ የብራስልስ መሪ ዲፕሎማቶች አሸባብን እንደሚያጠፉ ይፎክራሉ።አስረኛ ዓመታቸዉ።አሸባብ ዛሬም ወታደር ከሲቢል፤ ሹም ከተራ ሳይለይ ያጠፋል።ሶማሌ ዛሬም ያልቃል፤ይሸበራል፤ የታደለዉ ይሰደዳል።ላፍታ እንዴት ለምን እንበል?

ሶማሌዎች «ጠብ የሚፈልግ ሰዉ ከሱ የበለጠ ጠበኛ ያጋጥመዋል»-የሚል አባባል አላቸዉ አሉ።ማሕበረ-ባሕላዊ ትርጓሜዉን የሐሰን ሼሕ ማሕሙድን ያክል የሚያዉቅ የሐገር መሪ መኖሩ በርግጥ አጠራጣሪ ነዉ።ወታደራዊ፤ፖለቲካዊ ፍቺ-ምግባሩን ደግሞ የዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒን ያክል የሚረዳ አፍሪቃዊ መሪ ይገኛል ብሎ መገመት ከባድ ነዉ።

ከ1971 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እስከ 1979 ኢዲ አሚን ዳዳን፤ ከ1980 እስከ 1985 ሚልተን አቦቴን ከሥልጣን ለማስወገድ በተደረገዉ ዉጊያ አማፂያንን በመምራት፤ማደረጃት-ለድል ያበቁት፤ ምሥራቅ አፍሪቃዊቱን ሐገር ለ30 ዘመን የመሩት፤ በቅርቡ ደግሞ ከኮንጎ እስከ ሩዋንዳ፤ከደቡብ ሱዳን እስከ ሶማሊያ ጦር ያዘመቱት ፖለቲከኛ ሥለ ሶማሊያዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ እና አሸባብን ሥለሚወጋዉ ጦራቸዉ ጥንካሬ፤ ሥልትና ብልሐት የሚሉትን አለመቀበል በርግጥ ከባድ ነበር።

አሸባብ «ተሸንፏል» አሉ አስራ-ሰወስት ዓመት ሸማቂዎችን፤ 30 ዓመት ዩጋንዳን የመሩት ሙሴቬኒ ባለፈዉ ሚያዚያ፤ ምክንያቱም ቀጠሉ ሰዉዬዉ፤ (አሸባቦች) ጦራችንን ቀርቶ ፖሊሶችን እንኳን ማጥቃት አይችሉም።መደበኛ ቀርቶ የሽምቅ ዉጊያ እንኳን መዋጋት አይችሉም።» እያሉ።

Afrika AMISOM Symbolbild African Standby Dorce
ምስል Reuters/A. Wiegmann

የሙሴቬኒ ወታደራዊ፤ፖለቲካዊ እና ሥለላዊ ማብራሪያ ከናይሮቢ እስከ ሞቃዲሾ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ብራስልስ፤ ከዋሽግተን እስከ ኒዮርክ ሲተነተን ሰኔ ላይ አሸባብ እንደገና አጠቃ።ሙሳቬኒ ጦራችንን ቀርቶ ፖሊሶቻችንን እንኳ የማጥቃት አቅም የለዉም ያሉት ቡድን የጥቃት ኢላማ ሌጎ የሠፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ነበር።

ቡድኑ የገደላቸዉ ወታደሮች ቁጥር ያዉ እንደሁሌዉ አወዛጋቢ ነዉ።አሸባብ ሰባ ወታደሮች ገደልኩ ብሎ የነበር፤ የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከ20 እስከ 25 ይላሉ፤ የመንደሪቱ ነዋሪዎች 50 አስከሬን ማየታቸዉን ይመሰክራሉ።የአሸባብ ጥቃትም፤ የፖለቲካ አዋቂዎች ትናንታኔም የሙሳቬኒና የብጤዎቻቸዉን መሪዎች ቃል ሐሰትነት መስካሪ ነዉ።

የብሪታንያዉ የኦርየንታል እና የአፍሪቃ ጥናት ትምሕርት ቤት መምሕርት ዶክተር ላዉራ ሐሞንድ አንዷ ናቸዉ።«እነሱ (የአፍሪቃ ወታደሮች) ያደረጉት ምንድነዉ (የአሸባብ ታጣቂዎችን) ከአብዛኞቹ ዋና ዋና ከተሞች ማስወጣት ችለዋል።ትንሽ የገጠር መንገዶችንም ተቆጣጥረዋል።ይሁንና አሸባብን ሙሉ በሙሉ ለማሸነፍ በቂ ወታደራዊ ሐይል የላቸዉም።»

አሸባብ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ደምስሶ ሌጎን መቆጣጠሩ አነጋግሮ ሳያበቃ፤መስከረም መባቻ ጃናአሌ የሠፈረዉን የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ሠፈርን ወረረ።የዚሕ ጥቃት ሰለቦች የሙሴቬኒዋ ዩጋንዳ ወታደሮች ነበሩ። በትንሽ ግምት ሃያ-ተገደሉ።

የኢትዮጵያ ጦር የሶማሊያ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረትን በ2006 ከሥልጣን እስካስወገደበት ጊዜ ድረስ አሸባብን እንደ ጠንካራ የጦር ቡድን የሚያዉቀዉ አልነበረም።ሐሞንድ እንዳሉት ከ2007 ጀምሮ አሸባብን የሚወጋዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር -ባደረሰበት ጫና ምክንያት ርዕሠ ከተማ ሞቃዲሾ፤ የወደብ ከተማይቱን ኪስማዩን እና ባይደዋን የመሳሰሉ ትላልቅ ከተሞችን ለቅቆ ለመዉጣት ተገድዷል።የሶማሊያዉ ፕሬዝደት በቅርቡ እንዳሉት ደግሞ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር እና የመንግሥታቸዉ ወታደሮች ከሶማሊያ ግዛት 75 ከመቶዉን ይቆጣጠራሉ።

አሸባሪዉ ቡድን ግን ከሞቃዲሾ እስከ ናይሮቢ ከኪስማዮ እስከ ከጋሪሳ፤ ሆቴል ቤቶችን፤ የሥብሰባ አዳራሾችን፤ ትምሕርት ቤቶችን፤ የገበያ ማዕከላትን ከሁሉም በላይ የጦር ሠፈሮችን ማዉደም-ማሸበሩን አላቋረጠም።በቅርቡ የተጠቃዉ ኤል አዴ የሚገኘዉ የኬንያ ጦር ሠፈር ነዉ።ጥር 15።በጥቃቱ የተገደሉትን ወታደሮች ብዛት አሸባብ 100፤ መገናኛ ዘዴዎች በደርዘን የሚቆጠር ይሉታል።መንግሥታት እስካሁን ያሉት የለም።

የኬንያ ጦር ቃል አቀባይ የኮሎኔል ዴቪድ ኦቦንዮ የመጀመሪያ መግለጫማ የሞተ ወታደር የለም የሚል ነበር።«ከኬንያ መከላከያ ሐይል ጦር ሰፈር አጠገብ የሚገኘዉ ሠፈር ተጥቅቷል።ጥቃቱን ለመከላከል የኬንያ ጦር አፀፋ ጥቃት ከፍቷል።ዉጊያዉ እንደቀጠለ ነዉ።በሁለቱም ወገን የሞተ የለም።»

የሶማሊያ ይሁን ሶማሊያ ጦር ያሠፈሩ መንግሥታት ጦር ያዘመቱበትን ትክክለኛ ምክንያት፤የሞቱና የቆሠሉ ወታደሮቻቸዉን ብዛት፤ የሚወጣዉን የገንዘብ መጠን፤ ወታደሮቹ የሚገጥማቸዉን ፈተና አይናገሩም። የሚጠይቃቸዉም የለም።የኢትዮጵያ ጦር የአፍሪቃ ሕብረትን ጦር እስከተቀላቀለበት እስከ 2014 ድረስ 17,731 አባላት ለነበሩት ጦር በዓመት 500 ሚሊዮን ዶላር በጀት ይቆረጥለት ነበር።

ከአራት ሺሕ የሚበልጠዉ የኢትዮጵያ ጦር አሚሶሞን ከተቀላቀለ በሕዋላ በጀቱ በአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱ ይገመታል።ሕይወት፤ ደም፤ አካሉን ለሚገብረዉ ወታደር፤ በነብስ ወከፍ የሚደርሰዉ የገንዘብ መጠን ግን የአዝማቾችና አዛዦች ሚስጥር ነዉ።የተገደለዉ ወታደር ትክክለኛ ቁጥርን ማወቅ ሥለማይቻልም መገናኛ ዘዴዎች ከ2 እስከ ሰወስት ሺሕ እያሉ ለመገመት ተገድደዋል።የአፍሪቃ መሪዎች የወታደሮቻቸዉን ተልዕኮ፤የሚገጥማቸዉን ፈተና እና ጉዳታቸዉን የሚደብቁትን ያክል ጦራቸዉ ለድል መቃረቡን ለማወጅ፤ አሸባብን የመሳሰሉ ጠላቶቻቸዉን አረመኔነት፤ አቅመ ቢስነት ለመናገር ያመነቱበት ጊዜ ግን የለም።

UN Vollversammlung 26.09.2014 - Hassan Sheikh Mohamud
ምስል Reuters/Lucas Jackson

«እናዉቃቸዋለን።አላማቸዉን ለመደበቅ የፈለጉትን ያክል ቢሞክሩም እንነግራቸዋለን።ከዚሕ በፊት ተቋቁመናቸዋል።አሁንም እንቋቋማቸዋለን።ከዚሕ በፊት ለድል እንደበቃን ሁሉ አሁንም ድል እናደርጋለን።»

የኬንያዉ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ።ከዌስት ጌት የገበያ አዳራሽ እስከ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ፤ ከአዉቶቡስ መንገደኞች እስከ ኬንያ ወታደሮች አሸባብ ኬንያዉንን በገደለ ቁጥር ዛቻዉ ይንቆረቆራል።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሐይለ ማርያም ደሳለኝም ከሙሴቬኒ ወይም ከኬንያታ የተለየ መልዕክት የላቸዉም።አሸባብ «እየጠፋ ነዉ» ይላሉ «አያሰጋንም።»

«የኢትዮጵያ መንግሥትና ጦር ሐይሉ፤ የሶማሊያ መንግሥትና ሕዝብ ከአሸባብ ጋር የሚደርጉትን ዉጊያ እያገዙ ነዉ።አሸባብ አሁን እየጠፋ ነዉ።እኛን አሁን የሚያሳስበን አሸባብ ከISIL እና ከሌሎች አሸባሪ ቡድናት ጋር እንዴት እንደሚገናኝ ነዉ።ትኩረታችን ይሕ ነዉ እንጂ (አሸባብ) ትልቅ ሥጋት አይደለም።»

አሸባብ ግን እያሰላ፤ እያደባ፤ ቦታ እየቀያየረ ያሸብራል።የቡድኑ ታጣቂዎች ኤል አዴን የሠፈረዉን የኬንያን ጦር የወረሩት የኬንያታ ዛቻ፤ የሐይለ-ማርያም ትንታኔ ከተሰማ በኋላ ነበር።ባለፈዉ ሐሙስ ደግሞ ሞቃዲሾ ባሕር ዳርቻ የሚገኝ አንድ መዝናኛ ሆቴልን አጥቅተዉ በትንሽ ግምት ሃያ ሰዉ ገደሉ።

«የሆነዉ ምድነዉ ሸባብ ከከተሞች ወጥቶ በገጠራማ አካባቢዎች ጊዜ ወስዶ እንደገና እንዲደራጅ ነዉ የተተወዉ።እና ይሕን (የሐሙሱን) የመሠለ ትልቅ ጥቃት በተደጋጋሚ መፈፀም ችለዋል።አሸባቦች ወታደራዊ ሐይላቸዉ ትንሽ በመሆኑ ለአሚሶም የማያቋጥ አደጋ የሚጥሉ ከፍተኛ ጠላት አልሆኑም እንጂ ይሕን የመሰለ ከፍተኛ ጥቃት እየፈፀሙ ነዉ።»

በቅርቡ ኮንትራታቸዉን ጨርሰዉ ወደ ኒዮርክ የተመለሱት በሶማሊያ የተባሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ኒኮላስ ኬይ ሶማሊያ «የተጨናጎለች» መንግሥት አይደለችም ብለዉ ነበር።«ጠንካራ ለመባል ብዙ የሚቀራት ግን በማገገም ላይ ያለች» ፤በዲፕሎማቱ ብያኔ።የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼሕ ማሕሙድም መግንሳታቸዉ መስከረም 2012 ሲመሠረት በገባዉ ቃል መሠረት የሶማሊያን ፀጥታና የመንግሥት መዋቅሮች መገንባቱን አስታዉቀዋል።

Kenia Garissa Universität Anschlag Kenias Präsident Uhuru Kenyatta äußert sich zu demAnschlag
ምስል picture-alliance/dpa/ZUMA Press

«ማረጋጋት ችለናል።የመንግሥትነት የሥልጣን መዋቅር ዘርግተናል።ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ተስፋ እንዲኖረዉ ማድረግ ችለናል።መንግስቴ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ቅድሚያ የሚያስፍልጋቸዉ የተለያዩ ዕቅዶችን አቅርቧል።እቅዶቹ በቅጡ የተበጀቱ ብቻ ሳይሆኑ፤ የገንዘብ ፍሰቱን መቆጣጠር፤ የሚችል ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የገንዘብ ሥርዓት ያላቸዉ ናቸዉ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሐምሌ 2013 ባወጣዉ ዘገባ የሶማሊያ ማዕከላዊ ባንክ ካወጣዉ ገንዘብ ሰማንያ በመቶ ያሉ ወጪ የሆነዉ ለግለሰቦች (ባለሥልጣናት ነዉ)።የያኔዉ የባንኩ ገዢ አብዲሠላም ኡመር የድርጅቱን ዘገባ አጣጥለዉ ነቀፉት።በሁለተኛ ወሩ መስከረም ግን አብዲሠላም በሙስና ተጠርጥረዉ ሥልጣን ለቀቁ።ዩሱር አብራር ተተኩ።በሁለተኛ ወራቸዉ ዩሱርም ሥልጣን ለቀቁ።ምክንያት «ባለሥልጣናቱ አላሰራ አሉኝ» አሉ ወይዘሮዋ የባንክ ባለሙያ።

ፕሬዝደንት ሐሰን ሼሕ ማሕሙድ ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቀ የገንዘብ ሥርዓት ያዋቀሩላት ሶማሊያ ከ1991 ጀምሮ እንዲያ ነበረች።አሁንም ያዉናት።ኒኮላ ኬይ በማገገም ላይ ያለች የሚሏት ሶማሊያ ከአራት ዓመት በፊት በተያዘዉ ዕቅድ መሠረት ዘንድሮ ሐምሌ ምርጫ ማድረግ አለባት።የሶማሊያ ሕዝብ ድምፁን የሚሰጥበት ምርጫ ግን አይደረግም።ምክንያት፤ የኬይዋ «በማገገም ላይ ያለች» ሶማሊያ ፀጥታዉም፤ መንግሥታዊ መዋቅሩም፤ የፖለቲከኞችዋ ፍቃደኝነትም የለባም።«እስካሁን ያለዉ ሒደት ይቀለበሳል የሚል እምነት የለኝም።ይሁንና በሚቀጥሉት ዓመታትም አሸባብ ተጨማሪ ጥቃቶችን ሲፈፅም ማየታችን አይቀርም።ምክንያቱም በተቻላቸዉ መጠን ፖለቲካዊዉ ሥርዓት እንዳይፀና ለማደናቀፍ ነዉ የሚፈልጉት።»

Somalia Soldaten
ምስል AP

«ጠብ የሚፈልግ ሰዉ ከሱ የበለጠ ጠበኛ ያጋጥመዋል»-ብሎ ብሒልን ከሐሰን ሼኽ ማሕሙድ እኩል አሕመድ ዑመር ወይም አቡ ዑቤይዳሕም ያዉቁታል።ሁለቱም ሶማሌ ናቸዉ።ለምን አይታረቁም።የሊቢያ፤የየመን፤የሶሪያ ተፋላሚዎች ለዕርቅ ከተደራደሩ፤ሳልቫ ኪር፤ ከማቸር፤ ካቡሎች ከታሊባን፤አሜሪካኖች ከኢራን ከተስማሙ፤ ሞቃዲሾች ካሸባብ የማይደራደሩበት ምክንያት ግራ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ