1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ፕሬዝደንትና አዲሱ ጠ/ሚኒስትራቸው

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4 2006

የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ትላንት አዲስ ጠ/ሚ መሰየማቸው ተዘገበ። ፕሬዝደንት መሐሙድ የቀድሞውን ጠ/ሚ ካባረሩ ሳምንታት ቢቆጠሩም ጠ/ሚ ሺርዶን ግን ኣሻፈረኝ ብለው ቆይተው ነበር። የሶማሊያው ም/ቤት የመተማመኛ ድምጽ ከነፈጋቸው በኃላ ግን ሺርዶን ስልጣን መልቀቃቸው ታውቐል።

https://p.dw.com/p/1AZTq
Symbolbild Somalia Abstimmung Wahlen
ምስል imago/Xinhua

ፕሬዝደንት መሀሙድም በትላንትናው ዕለት የምጣኔ ሀብት ባለሙያውን አብዱወሊ ሼክ ኣህመድን አዲሱ የሶማሊያ ጠ/ሚ ኣድርገው ሾመዋል።

በሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ መሀሙድ እና በጠ/ሚ አብዲ ፋራህ ሺርዶን መካከል የተካረረው እና በቐፍ ያለውን የኣገሪን መንግስት ይበልጥ ኣሽመድምዶ ለሳምንታት የዘለቀው ኣለመግባባት መነሻው ፕሬዝደንቱ እንደሚሉት ጠ/ሚ ኃላፊነታቸውን በብቃት ኣልተወጡም የሚል ነበር። ጠ/ሚኒስትር ሺርዶን ባይቀበሉትም። የምስራቅ ኣፍሪካ የጸጥታ ኣማካሪ የሆኑት ሚ/ር አንድሪውስ አታ አሳማዋ እንደሚሉት ግን በቀድሞዎቹ የሽግግር መንግስታት ወቅትም ሲሆን እንደነበረው ሁሉ ኣሁንም የሁለቱ ባለስልጣናት ኣለመግባባት በአዲሱ ካቢኔያቸው ውስጥ በነበረው በጎሳ ላይ የተመሰረተ የስልጣን ክፍፍል ጭምር ነው።

«እንደሚመስለኝ ከስራ ብቃት ጋር የተያያዘ ነው። የሶማሊያን ህገመንግስት ብትመለከቱ ዋናው የኣስፈጻሚ ስልጣን የጠ/ሚኒስትሩ ነው። እናም ደካማ ጠ/ሚ መጣ ማለት መንግስት ደከመ ማለት ነው። በመሆኑም ያለው ብቸኛ ኣማራጭ ጠ/ሚኒስትሩን መቀየር ነው። እንግዲህ አዲሱ ጠ/ሚ ደግሞ አዲስ ካቢኔ ይሰይማል። ካቢኔው ደግሞ የጎሳ ተዋጽኦው ስለሚታይ የልዩነት ምክኒያት ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ስራው ይፈልገዋል ተብሎ እንዲህ በዋዛ አዲስ ማምጣት ኣይቻልም።»

Hassan Sheikh Mohamud Präsident Somalia
ምስል Getty Images

ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከሀውያ ጎሳ ሲሆኑ ጠ/ሚ ሺርዶን ደግሞ ከዳሮድ ጎሳ ናቸው። የሆነ ሆኖ በሁለቱ መካከል በተካረረው ኣለመግባባት በጸጥታ ስጋት ውስጥ ላለችው ሶማሊያ መንግስታዊው ተግባርም መሰናከሉን የተረዱት ፕሬዝደንት መሀሙድ ጠ/ሚኒስትር ሺርዶንን ከስልጣን ማባረራቸውን ኣስታወቁ። ሺርዶን በበኩላቸው ኣሻፈረኝ ብለው ሰነበቱ። ሚ/ር አታ ኣሳማዋ

«ችግሩ ከህገ መንግስት ትርጉዋሜ የመነጨ ይመስለኛል። ምክኒያቱም ህገመንግስቱ ለፕሬዝደንቱ ጠ/ሚኒስትሩን የመሰየም ስልጣን ይሰጣል። ማሰናበቱ ላይ ግን ግልጽ ያልሆነ ነገር ኣለ። ፕሬዝደንቱ ጠ/ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲለቁ መጠየቅ ኣለበት። በቀጥታ ማባረር ኣይችልም። ጠ/ሚኒስትሩ መልቀቂያ ኣለቀርብም ካሉ ግን ያው ወደ ም/ቤት መሄድ ነው ያለው ኣማራጭ። ለዚህ ነው ጠ/ሚ ሺርዶን ፕሬዝደንቱ በቀጥታ ሊያባርሩኝ ኣይገባም ብለው ኣታካራ የገጠሙት።»

Somalia Terror Shabaab Kämpfer tranieren bei Mogadishu
ምስል picture-alliance/AP

ትላንት ግን ችግሩ እልባት ማግኘቱ ታውቐል። የሶማሊያ ም/ቤት ለጠ/ሚኒስትር ሺርዶን የመተማመኛ ድምጽ በመንፈጉ። ፕሬዝደንት መሀሙድም ትላንትናውኑ አዲስ ጠ/ሚኒስትር ሰይሟል። አብዱወሊ ሼክ ኣህመድ ይባላሉ። ሚ/ር ኣህመድ ለሶማሊያ ጠ/ሚኒስትርነት ከማንም በላይ ኣስፈላጊ ሰው ናቸው ያሉት ፕሬዝደንት መሀሙድ ጠ/ሚ ኣህመድ ኣገሪቱን ወደፊት እንደሚያራምዷት ተስፋ ኣደርጋለሁ ሲሉም ለም/ቤቱ ኣስረድቷል።

በደቡባዊ ጌዶ ክ/ሀገር የሚወለዱት ጠ/ሚ ኣህመድ የሶማሊያው የእርስ በርስ ጦርነት ሲቀጣጠል ነበር ከኣገር የወጡት። በ1991። ከዚያ ወዲህ በስደት የኖሩት ጠ/ሚ ኣህመድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ በሳውዲ አረቢያ ዲዳ በሚገኘው እስላማዊ የልማት ባንክ ውስጥ ይሰሩ ነበር። ቀደም ሲልም የምስራቅ እና ደቡባዊ ኣፍሪካ የጋራ ገበያ ኮሚሳ ኣማካሪ የነበሩ ሲሆን እንደ ፕሬዝደንት መሀሙድ ሁሉ ለፖለቲካው ዓለም ግን አዲስ መሆናቸው ኣልቀረም። ይሁን እንጂ ተንታኞች እንደሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው አብዱወሊ በጠ/ሚኒስትርነት መሾማቸው ለዚያች ኣገር የገንዘብ እርዳታ ለማስገኘት የለጋሾችን ትኩረት ይስብ ይሆናል በሚል እምነት ጭምር ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል ከሶማሊያ እና ከሶማሊያ ፖለቲካ ርቀው የቆዩት አብዱወሊ ወደ ኣገር ቤት ተመlrሰው ጠ/ሚ መሆናቸው ለፕሬዝደንት መሀሙድ በቀላሉ ተጽዕኖ እያሳረፉ ያለ ችግር በበላይነት ለመግዛት ያመቻቿል የሚሉ ወገኖችም ኣሉ። ኣሁንም ሚ/ር ኣታ ኣሳማዋ

Somalia Anschlag Maka Al-Mukarama Mogadischu
ምስል Reuters

«ከሶማሊያ ኣንጻር ጠንካራ ጠ/ሚ ማለት ፕሬዝደንቱን መጋረድ ማለት ነው። ፕሬዝደንቱ ተጋረዱ ማለት ደግሞ በጠ/ሚኒስትሩ ላይ ችግር ተፈጠረ ማለት ነው። መስራት ኣይችልም። ከፕሬዝደንቱ ጋር መስማማት ይኖርበታል። ምክኒያቱም ፕሬዝደንቱም መታየት፣ መታወቅ፣ እና ገናና መሆን ይፈልጋል። ስለዚህ ጠ/ሚኒስትሩ ገናና ከሆኑ ፕሬዝደንቱም ይበልጥ ለመግነን ኣሊያም ላለመጋረድ ይንቀሳቀሳል። የሶማሊያ ሁኔታ በዚህ ኣይነት ኣሁሪት ውስጥ ነው የነበረው። አዲሱ ጠ/ሚ ኣብዱወሊም ካልተጠነቀቁ ተመሳሳይ ግጭት ሊከሰት ይችላል።»

የሆነ ሆኖ እርምጃው በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተፈጠረው የኣመራር ክፍተት ለኣልሸባብ ኣማጺያን ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ዳግም ኣማጺያኑ ወደፊት እንዳይገሰግሱ ኣንዣቦ የነበረውን ስጋት የገፈፈ ነው ተብሏል። ከኣልቃኢዳ ጋር ቁርኝት እንዳለው የሚነገርለት ኣልሸባብ ኣሁንም ቢሆን ከዋና ዋና ከተሞች ውጪ ያሉትን አብዛኞቹን የደቡብ ሶማሊያ አካባቢዎች ይቆጣጠራል።

ጃፈር ዓሊ

ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ