1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሌያና የኬንያ ውዝግብ፤ የሴቶች «የግጭት ይቁም» የረሀብ አድማ በካሜሩን

ቅዳሜ፣ ግንቦት 14 2013

በኬንያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላለፉት ስድስት ወራት እየሻከረ መጥቷል። ይህንን ተከትሎ የሀገራቱ የንግድ በረራዎች በመታገዳቸው በሁለቱ ሀገራት ሀዘቦች ኢኮኖሚ ላይ ጫናም እያሳደረ ነው።በሌላ በኩል በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ካሜሩን ሴቶች በሀገሪቱ ግጭት እንዲቆም ለመጠየቅ የረሀብ አድማ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/3toPi
Somalia Tabda|  Kenianische Soldaten | Militäroffensive
ምስል Ben Curtis/AP Photo/picture alliance

የሶማሌያና የኬንያ ውዝግብና የሴቶች «የግጭት ይቁም» ረሀብ አድማ በካሜሩን


በዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት በሶማሊያና ኬንያ መካከል በተፈጠረው  የዲፕሎማሲ ግንኑነት መሻከር መንስኤዎችና መፍትሄዎች ፤ እንዲሁም በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ካሜሩን ለዓምስት አመታት የዘለቀን የዕርስ በዕርስ ግጭት እንዲቆም ለመጠየቅ የሀገሪቱ ሴቶች የረሀብ እደማ  ማድረለተቃውሞ  መውጣታቸውን የተመለከቱ ዘገባዎችን አካተናል። 
በኬንያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላለፉት ስድስት ወራት የሻከረ  ይመስላል።የሁለቱ ሀገራት ውዝግብ በሀገራቱ በኢኮኖሚ ላይ እያሳደረ ያለው ጫናም ቀላል አይደለም። በሁለቱ ሀገራት  መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ ከመጣ ወዲህ   ወደ ሶማሊያ ጫት ለመላክ የኬንያ የጭነት መኪናዎች ወደ ናይሮቢ ዊልሰን አውሮፕላን ጣቢያ ማምራታቸውን  አቋርጠዋል። ምክንያቱም ናይሮቢ፤ ከግንቦት 11 ቀን ጀምሮ ለሦስት ወራት ወደ ሶማሊያ የሚደረጉ የንግድ በረራዎችን አቁማለች። በየቀኑ  ወደ 16 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ (148,000 ዶላር ፣ 121,000 ዩሮ)  ለሚያስገኘው የኬንያ ጫት ንግድ ሶማሊያ አስፈላጊ ገበያ ብትሆንም፤ የሞቃዲሾ ከተማ ነዋሪዋ  ሀሚድ አደን እንደሚሉት በሀገራቱ መካከል በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የንግድ ግንኙነት አይታይም።
«የንግድ በረራዎች «ሚራአ» ወይም ጫት የሚጭኑትን ጨምሮ ቀድሞውኑ ተሰርዘዋል። በአሁኑ ጊዜ በኬንያ እና በሶማሊያ መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት እያየን አይደለም።ሁለቱ ጎረቤት ሀገሮች በጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ ተመስርተው ግንኙነታቸውን ማሻሻል ይችላሉ። ነገር ግን ኬንያ በሶማሊያ ጉዳይ  በይፋ ጣልቃ መግባቷን ከቀጠለች፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁለቱ  ሀገሮች  መካከል ያለውን ግንኙነት መደበኛ የማድረግ ውጤት ማግኘት አይቻልም።»
ከነፃነት በኋላ 682 ኪ.ሜ (423 ማይል) ድንበር የሚጋሩት ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገሮች የግንኙነት ታሪካቸው  ጥሩ የሚባል አልነበረም። ሀገራቱ በድንበር ውዝግቦች ፣ በትንንሽ ግጭቶች እና በአንዳንድ አጋጣሚዎችም ደም አፋሳሽ ግጭቶች ውስጥ ሲገቡ ቆይተዋል።
ባለፈው ህዳር ወርም ኬንያ፤ በውጥ ጉዳዬ ጣልቃ ገብታለች የሚል ክስ ሶማሊያ ማቅረቧን ተከትሎ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸው የተቋረጠ ሲሆን፤ለቁርሾው መነሻ የሆነውም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት እውቅና ያነፈጋትን፤ የሶማሊላንድ የፖለቲካ አመራሮችን በሀገራቸው ተቀብለዉ  ማስተናገዳቸው ነበር። ይህንን ተከትሎም የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፋርማጆ ሞቃዲሾ የሚገኙትን የኬንያ ልዑክ ከማስወጣታቸው በተጨማሪ የሀገራቸውን አምባሳደርም ከኬንያ እንዲመለሱ አድርገዋል።
ኬንያ በበኩሏ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ  ጣልቃ አለመግባቷን በመግለፅ፤ ይልቁንም ፕሬዚዳንት ፎርማጆ በሀገር ውስጥ ላለው የፖለቲካ ችግር እንደማምለጫ  እየተጠቀሙበት ነው ስትል ወቅሳለች። 
ሶማሊያዊው ሱሌማን እስማኤል እንደሚሉት ሀገራቱ ግንነታቸውን ለማሻሻል በኢኮኖሚያዊ በፍላጎቶቻቸው ላይ እኩል መግባባት ሊፈጠር ይገባል።
«እኔ እንደማስበው ሁለቱ ሀገሮች በአስፈላጊ ፍላጎቶቻቸው ላይ እንደ እኩል ጎረቤቶታሞች እርስ በእርሳቸው  ከተባበሩ በሶማሊያ እና በኬንያ መካከል ያለው ግንኙነት የተሻለ ይሆናል። መደረግ ያለበት በጣም አስፈላጊው ነገር፤  ሁለቱ ሀገሮች ከኢኮኖሚ ማዕቀብ በስተቀር በሁሉም ነገር መስማማት ነው። ምክንያቱም ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች በተመለከተ  በኬንያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ አይደለም።»
ከውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነት ክስ በተጨማሪ ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከር የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያም ሌላው የውዝግብ  መነሻ ነው። 
 የሶማሊያ አምባገነን መሪ ሲያድ ባሬ ከወደቀበት ከጎርጎሪያኑ 1991 ዓ/ም ጀምሮ ኬንያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን ስደተኞችን ስታስተናገድ የቆየች ሀገር ነች። ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት  ወዲህ ፕሬዝዳንት ኬንያታ በተለያዩ አጋጣሚዎች በትልቅነቱ የሚታወቀውን  የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ  ለመዝጋት ሲያስጠነቅቁ  የቆዩ ሲሆን፤ አብዛኛው የሶማሊያ ስደተኛ አዲስ ቤት እንዲያገኝ  እስከ ሰኔ 2022 ዓ/ም ድረስ ብቻ መጠለያ ጣቢያው ክፍት ሆኖ እንዲቆይ የኬንያ መንግስት  ለተባበሩት መንግስታት የጊዜ ገደብ ሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ ሀገራት በሕንድ ውቅያኖስ ማዶ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የባህር ድንበር ይገባኛል ውዝግብ አላቸው።ቦታዎቹ የነዳጅ እና የጋዝ ክምችት አላቸው ተብሎ የሚታመን ሲሆን፤የይገባኛል ክርክሩም በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እጅ ይገኛል ፡፡ 
በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታ ላይ ያተኮረውና ሰሃን በመባል የሚጠራው  ተቋም መስራችና  አማካሪ የሆኑት ማት ብሪደን፤ እነዚህ ጉዳዮች ለሁለቱ ሀገራት ቀና የሆኑ ስልታዊ ፍላጎቶች ናቸው። ነገር ግን ጉዳዩን ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል ሲባል በሁለቱም ወገኖች በኩል አላስፈላጊ እና ሰው ሰራሽ በሆነ መልኩ አለመግባባቶቹ ተካረዋል ይላሉ። ብሬደን አያይዘውም ኬንያ ብዙ ነዋሪዎችን ወደ ሶማሊያ የመመለስ ፍላጎት ስለሌላቸው ዳዳብን መዝጋት ከስደተኛ ነፃ  እንደማያደርግ ጠንቅቃ ታውቃለች ብለዋል። ጣቢያው በቋሚነት ከመዘጋቱ በፊትም ለዳዳብ አስተዳደር የረጅም ጊዜ ዕቅድ  ማቅረብ ያስፈልግ እንደነበርም አክለዋል ፡፡ 
በሞቃዲሾ የ DW ዘጋቢ መሐመድ ኦዶዋ እንደሚለው የሁለቱ ሀገራት ውዝግብ የመጠለያ ጣቢያውና የባህር ይገባኛል ውዝግብ ብቻ አይደለም። ሙሀመድ እንደሚለው ናይሮቢ በጁባሌላንድ እና በሶማሌላንድ አስተዳደሮች ላይ የወሰደችው እርምጃ በታላቋ ሶማሊያ አንድነት እንዲሁም በፖለቲካዊ እና በግዛት ነፃነቷ ላይ ስድብ እና ትልቅ ስጋት ነው ብላ ሞቃዲሾ ታምናለች፡፡
 ስለዚህ ሁለቱ ሀገሮች ውጥረቱን ለማርገብ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ይላል። 
ብሪደን በበኩላቸው የባህር  ውዝግቡም ቢሆን የዜሮ ድምር ስሌት መሆን የለበትም ባይ ናቸው።ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በየትኛውም መንገድ ቢወስን አንዳንድ የነዳጅ ክምችቶች ከባህር ጠረፍ ተሻግረው የሀብት መጋራት ስምምነቶችን የሚጠይቁ ሊሆኑ ይችላሉ።ያ በመሆኑ ሁለቱም ወገኖች  በችግሮቻቸው ላይ መወያየት ወሳኝ ነው ይላሉ። የሞቃዲሾ ከተማ  ነዋሪ የሆኑት ማሩፍ ሀጂም ሁለቱ ሀገሮች ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ያሳስባሉ።
«በኬንያና ሶማሊያ መካከል  የባህር ላይ ውዝግብ ከተነሳ ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ጎረቤት ሀገሮች መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ በመሄዱ ሁለቱም  አምባሳደሮቻቸውን ለምክከር  ጠርተዋል። ጉዳዩ አሁንም ድረስ አልሰከነም። በኬንያና በሶማሊያ መካከል እየተባባሰ የመጣውን አለመግባባት ለመፍታትና  የነበረውን ጥሩ መተማመን ለመመለስ ሁለቱም  በጠረጴዛው ዙሪያ ሆነው በመደራደር  ልዩነቶችን በስምምነት መፍታት አለባቸው።» 
 የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታ ጥናት ተቋም አማካሪው  ማት ብሬደን ፤ ፎርማጆ በስልጣን እስካሉ ድረስ የሁለቱ ሀገራት  የዲፕሎማሲያዊ ችግር  ይፈታል ብለው አያምኑም።ሆኖም በሞቃዲሾ ተግባራዊ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን የሚከተል አዲስ አስተዳደር ከመጣ ጉዳዩ በአዲሱ አመራር ላይ የሚመረኮዝ ይሆናል ነው ያሉት። ያም ሆኖ እንደ ኢትዮጵያ ፣ ጅቡቲ እና ኤርትራ ካሉ ጎረቤት ሀገሮች ጋር ያለው ግንኙነትም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በሶማሊያ የውጭ ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር  አመልክተዋል። 
የሴቶች «የግጭት ይቁም» ረሀብ አድማ በካሜሩን
በጎርጎሪያኑ 1960 ነፃነቷን ያገነችው ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ካሜሩን አብዛኛው ህዝቧ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆን፤ወደ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ህዝቦቿ ደግሞ የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ናቸው።ያ በመሆኑ በሀገሪቱ ሁለት የስራ ቋንቋ ጥቅም ላይ የሚዉል  ሲሆን፤በእንግሊዝናዉና በፈረንሳይኛ ተናጋሪው መካከልም የተለያየ የትምህርትና የህግ ስርዓት ያላት ሀገር ነች።ይሁን እንጅ በሀገሪቱ አናሳ ቁጥር ያላቸው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ካሜሩናዉያን ጭቆናና እኩል ተጠቃሚ ያለመሆን በደል በማዕከላዊ መንግስቱ እየደረሰብን ነው።በሚል በተደጋጋሚ ሲቃወሙ ቆይተዋል። በ2016 ዓ/ም ባማንዳ በተባለው ከተማ መምህራንና የህግ ጠበቆች በሀገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል የሚኖሩ አናሳ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የህግ እና የትምህርት ስርዓቶችን ወደ ፈረንሳይኛ ተናጋሪው ስርዓት ለማዋሃድ የመንግስት ጥረት እያደረገ ነው። በሚል ጎዳና ላይ በመውጣት  ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።ይህንን ሰላማዊ ተቃዉሞ መንግስት በሀይል ለመበተን በመሞከሩ  በወቅቱ በፀጥታ ሀይሎች  ሰዎች ተገድለዋል። ይህንን ጥቃት ተከትሎም የእንግሊዥኛ ቋንቋ ተናጋሪ ካሜሩናዉያንን ከቀረው የሀገሪቱ ክፍል ለመገንጠል የሚታገል የታጠቀ አማፂ ቡድን ሊመሰረት ችሏል።ስለሆነም  ከመስከረም 2017 ወዲህ  የአካባቢው በጦርነት እየታመሰ ይገኛል። 
አምስት አመታትን ባስቆጠረው በዚህ የርስበርስ ጦርነት ታዲያ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት፣በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ደግሞ ቤት ንብረታቸውን  ለቀው እንዲሰደዱ አድርጓል። 
በሀገሪቱ ውስጥ ለቀጠለው ቀውስ መፍትሄ እንዲመጣ በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር የሀገሪቱ ሴቶች ከሰሞኑ ለተቃዉሞ ጎዳና ወጥተዋል።
ይሁንና ሰላማዊ ሰልፉ የተፈለገውን ምላሽ ሊያመጣ ባለመቻሉ፤ ሴቶቹ አዲስ የተቃዉሞ መንገድን መርጠዋል።በመሆኑም ከጎዳና ላይ ሰልፈኞቹ መካከል በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች የረሃብ አድማ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተሳታፊዎቹ ይገልፃሉ።
«ለሰባት ቀናት ያህል ምግብ አልበላሁም። በጣም ተዳክሜያለሁ።በረሀብ ተጎድቻለሁ። አሁን በምናገርበት ጊዜም እንኳ  ከፍተኛ ራስ ምታት እየተሰማኝ ነው።»
ሌላዋ የረሀብ አድማ ተሳታፊ በበኩሏ፤ « ምንም  ነገር አልበላሁም ። በረሃብ  ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ትኩሳት ይሰማኛል። ለቀናት ያለ ምግብ ስንቀሳቀስ ስለነበረም ክብደቴ ጭምር እየቀነሰ ነው።» 
የአድማው አስተባባሪ ፣ ባይዬ ፍሪዳ ኤባይ እንደሚሉት ተቃውሞው የሀገሪቱን ሁለት የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ክልሎችን ለሚያናውጠው  ቀውስ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ለመጠየቅ ነው።
እንደ አስተባባሪዋ ከመንግስት ኃይሎችም ሆነ ከተገንጣይ ተዋጊዎች የሚደርርሰውን ጥቃት በመፍራት የረሀብ አድማ አድራጊዎቹ  ማንነት ይፋ አይደረግም። ችግሩ  ተገቢውን ትኩረትና መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስም ተቃውሞው እንደሚቀጥል ይገልፃሉ። 
«አሁን ወደኋላ አንመለስም። ወደ ኋላ ሳንል የርሃብ አድማውን እንቀጥላለን። እና ሌሎች እህቶችም እኛን እንዲቀላቀሉ ጥሪ እናቀርባለን።የግል ቁርጠኝነት ነው። ማንንም አናስገድድም። »
በግጭቱ ሳቢያ ከሚደርሰው ግድያ እና አፈና በተጨማሪ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት  ተቃውሞውን እንዲቀጥሉ ያደረጋቸው ሌላው  ምክንያት ነው። «ሪች አፕ» ካሜሩን የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ኦማም ኢስተር  እንደሚሉት ይህ ግጭት የወሲብ ጥቃቶች እንዲባባስ አድርጓል። 
እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት  ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ክልል ውስጥ ባለፈው  ዓመት 2020 ዓ/ም ከ 4000 በላይ የሚሆኑ ወሲባዊ እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች የተመዘገቡ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻም  ወደ 500 የሚጠጉ  ጾታዊ ጥቃቶች ተመዝግበዋል። በጥቃቱም የመንግስት ወታደሮችና አማፅያኑ እየተወቀሱ ነው።
የተቃውሞው  አስተባባሪ ባይዬ ፍሪዳ እንደሚሉት የመንግስት ወታደሮችና አማፅያኑ በአካባቢው በሚያደርጉት ጦርነት ሳቢያ ሴቶች የበለጠ ተጎጅ ናቸው።
«ሴቶች እንደመሆናችን መጠን ልጆችን የማጣት ህመም የሚሰማን  እኛ ነን።በዚህ ቀውስ ምክንያት ልጆቼን አጥቻለሁ። የወንድሜን ልጆችም አጣሁ። የወሊድ ህመምና ስቃይ የሚሰማን እኛ ነን ፣ ልጆችን ያለ ወላጅ የማሳደግ ህመም የሚሰማን እኛ ነን። ለዚህም ነው ይህንን የረሃብ አድማ ለመቀጠል  ጽኑ ቁርጠኝነት የወስደነው።» 
በካሜሩን ሁለቱ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ክልሎች ውጊያው አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ ከሰሞኑን እንኳ በአጎራባች ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የምዕራብ ክልል  ጋሊም  በተባለ አካባቢ አማፂያኑ በአንድ የመንግስት ወታደራዊ የጦር ሰፈር ላይ ያካሄዱትን ጥቃት ተከትሎ በተቀሰቀሰ ውጊያ 12 የአማፂ ቡድን አባላትና እና አራት የመንግስት ወታደሮች መገደላቸውን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ ፡፡የምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል  አስተዳዳሪ ፎንቃ አውጉስቲን መንግስት ሁኔታው በጣም እንዳሳሰበው ተናግረዋል። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ በበኩላቸው በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን መግዳደላችንን አቁመን ወደ ንግግር መምጣት አለብን። ሲሉ ከአማፅያኑ ጋር ውይይት ለመጀመር ፈቃደኝነታቸውን ገልፀዋል። 
የባይደን አስተዳደርም በካሜሩን  የተፈጠረው ቀውስ  ትኩረት የሚያሻው መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኩል አመልክቷል ፡፡ 

Symbolbild Vergewaltigung sexuelle Gewalt Afrika
ምስል picture-alliance/dpa
Kamerun Sprachenstreit um Englisch
ምስል Getty Images/AFP
Kamerun Sprachenstreit um Englisch
ምስል Getty Images/AFP/A. Huguet
Kenia Flüchtlingslager Dadaab
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba
Infografik Seegrenzen Somalia Kenia EN

ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ