1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ ምስቅልቅልና የወደፊት ዕጣዋ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2005

«ፀረ-አዉሮፕላን ሚሳዬል ቢኖረን ኖሮ» አሉ ጄኔራሉ-አሶስየትድ ፕረስ ለተሰኘዉ ዜና ወኪል ዘጋቢ ባለፈዉ ሳምንት።«ይሕን ሥርዓት ባንድ ወር ዉስጥ እናስወግደዋለን።» ፀረ-አዉሮፕላን መሳሪያዉ ካልተገኘ ደግሞ ፥ ቀጠሉ የሐምሳ አምስት አመቱ ጄኔራል «ሰወስት ወር»

https://p.dw.com/p/178c1
Source News Feed: EMEA Picture Service ,Germany Picture Service Syria's President Bashar al-Assad (R) meets International peace envoy for Syria Lakhdar Brahimi in Damascus December 24, 2012 in this handout photograph released by Syria's national news agency SANA. Brahimi met with Assad in Damascus on Monday to discuss a solution to the country's 21-month-old conflict. Brahimi told journalists after the meeting that he discussed the situation in Syria overall and gave his views on how to solve the crisis. He said conditions in the country were still poor. REUTERS/Sana (SYRIA - Tags: POLITICS CIVIL UNREST) FOR EDITORIAL USE ONLY. NOT FOR SALE FOR MARKETING OR ADVERTISING CAMPAIGNS. THIS IMAGE HAS BEEN SUPPLIED BY A THIRD PARTY. IT IS DISTRIBUTED, EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS
ብራሒሚና አሰድምስል Reuters


የደፈጣ ተዋጊዎቹ አዛዥ ጄኔራል ሳሊም ኢድሪስ እና ስደተኛዉ ጋዜጠኛ ማሊክ አብድሕ ሲጠብ ለየግላቸዉ ሥልጣን፣ ሐገራቸዉ ለመኖር፣መሥራት-ጉጉት ስኬት፣ ሲሰፋ ብዙዎች ብዙ ጊዜ እንደሚሉት ለሶሪያዎች፣ መብት፣ ነፃነት መከበር ፍላጎት-ግብ፥ የአሰድ ሥራዓትን መወገድ እኩል ይፈልጉታል።ይታገላሉም።ብሪታንያዉያኑ፥ጄኔራል ቲም ክሮስና ሚንስትር አላስተር በርት በየግላቸዉ ምናልባት ለመሾም-መሸለም፣አማፂያኑን እንደምትረዳ ሐገር ሹማምንት በጋራ የአሰድን መወገድ ይሹታል።አራቱ-እኩል ከሚፈልጉት እንደርሳለን የሚሉበት ሥልት፣ጊዜ፣ ሥለ ወደፊቷ ሶሪያ ያላቸዉ ዕምነት ዝግጅት ግን ይቃረናል።የአራቶቹ አንድነት፣ ተቃርኖ ሥለ አንዲሲቱ ሶሪያ፥ ሶሪያዎችም የዓለም ዘዋሪዎችም አድም-ተቃራኒም አቋም የመያዛቸ ነፀብራቅ መሆኑ ያሰጋል።እንደገና ሶሪያ እያልን እንደገና አንድም-ተቃርኖዉን ላፍታ እንቃኝ።

ሐልፋያ-ሶሪያ። ትናንት።አማፂያን እና ደጋፊዎቻቸዉ እንዳስታወቁት የመንግሥት የጦር አዉሮፕላኖች በጣሉት ቦምብ አንድ ዳቦ ቤት አጠገብ ተሰብስበዉ የነበሩ ዘጠና ሰዎች ተገደሉ።የቆሰለዉ በመቶ ይቆጠራል።የሶሪያ መንግሥት መገናኛ ዘዴዎች ባንፃሩ እንደዘገቡት አደጋዉን የጣሉት እነሱ «አሸባሪ» የሚሏቸዉ አማፂያን ናቸዉ።በዚያም ብሎ በዚሕ ሌላ ቦምብ፥ ሌላ እልቂት፥ ሌላ ጥፋት፥ እና ለቀሪዎች የሰቆቃ ጩኸት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአረብ ሊግ ልዩ መልዕክተኛ ላሕዳር ብራሒሚ ከፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ ጋር ዳግም ተነጋገሩ።ደማስቆ-ትናንት።የልዩ መልዕክተኛዉ መልዕክት፥ የዉይይቱ ዝር ዝር ይዘት፥ ሒደት ዉጤቱ በግልፅ አልተነገረም።ጥቅል ዓላማዉ ግን ባለፉት ሃያ-ሰወስት ወራት ከካይሮ፥ ከብራስልስ፥ ከኒዮርክ ደማስቆ እየደረሱ ከተመለሱት የአረብ ሊግ፥ የአዉሮጳ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት መልዕክተኞች ካሉት የተለየ አይደለም።ለሶሪያ-ሰላም የሶሪያ ተፋላሚዎች ማስታረቅ።

እስካሁን የዉጊያዉ ግመት፥ የሕዝቡ እልቂት ፍጅት፥ስደት-እንግልት ንረት እንጂ የሰላም ተስፋ ጨርሶ የለም።ልዩ መልዕክተኛ ብራሒሚ ደማስቆ ከመግባታቸዉ ጥቂት ቀደም ብሎ ትናንትናዉኑ የሶሪያዉ ማስታወቂያ ሚንስትር የመንግሥታቸዉን የተለመደ መልዕክት ባስተርጓሚ አስተላለፉ።

«ለእኒያ ድርድርን እንቢኝ ላሉት የፖለቲካ ሐይላት አጠቃላይ ምክር አለኝ።ጊዜዉ እየከነፈ ነዉ።ለፖለቲካዊ መፍትሔ ፈጥናችሁ ተንቀሳቀሱ።መንግሥትን እና ፕሬዝዳንቱን አስወግዶ፥ ርዕሠ ከተማይቱን ለመቆጣጠር የሚደረገዉን ይሕን ወታደራዊ ዘመቻ እርሱት።ይሕ ነዉ-የኔ ምክር።»

ጄኔራል ሳሊም ኢድሪስ ለማስታወቂያ ሚንስትሩ ማስጠንቀቂያ የሰጡት መልስ ሥለመኖር አለመኖሩ ላሁኑ የታወቀ ነገር የለም።የቀድሞዉ የሶሪያ ወታደራዊ ኮሌጅ የኤሌክትሮኒክስ መምሕር ሰላሳ ዓመት ያገለገሉትን፥ የጄኔራልነት ማዕረግ የለጠፉበትን ጦር ከድተዉ አማፂያኑን ከተቀላቀሉ ታሕሳስ አምስተኛ ወራቸዉ ነዉ።

አንድ መቶ ሃያ-ሺሕ ተዋጊዎች እንዳሉት የሚታመነዉ የአማፂያን ቡድናት ጦር ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሆነዉ ባለፈዉ ወር ተሰይመዋል።«ፀረ-አዉሮፕላን ሚሳዬል ቢኖረን ኖሮ» አሉ ጄኔራሉ-አሶስየትድ ፕረስ ለተሰኘዉ ዜና ወኪል ዘጋቢ ባለፈዉ ሳምንት።«ይሕን ሥርዓት ባንድ ወር ዉስጥ እናስወግደዋለን።»

ፀረ-አዉሮፕላን መሳሪያዉ ካልተገኘ ደግሞ ፥ ቀጠሉ የሐምሳ አምስት አመቱ ጄኔራል «ሰወስት ወር» አሉ ፍርጥም ብለዉ።ጄኔራሉን «አዲስ መጤ» የሚላቸዉ የአማፂ ቡድናት መሪዎች ግን የእሳቸዉን አዛዥነት አልተቀበሉትም።አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱበት በተለይም በሰሜን-ምዕራብ ኢድሊቢ አዉራጃ ያሉ የሐገር ሽማግሌዎና የጎሳ ታጣቂ መሪዎችም በጄኔራሉም ሆነ በጄኔራሉ አለቆች የሚታዘዘዉን ተዋጊ ሐይል አይፈቅዱትም።

ጄኔራሉ ራሳቸዉ የሚያዙት ጦር ወደ ሚቆጣጠራቸዉ አካባቢዎች የሚገቡ የሚወጡት በጥምጣም፥ ኮፊታ፥ በአልባሌ ልብስ ማንነታቸዉን ደብቀዉ ነዉ።የማደሪያ ወይም የዕዝ ጣቢያቸዉን «የመንግሥትን ሰላዮች ፍራቻ ባንድ ሌሊት ሁለቴ ወይም ሰወስቴ ለመቀየር እገደዳለሁ» ይላሉ።

ጄኔራሉ የአማፂያኑን ሐይል በቅጡ አላስተባበሩም። የሚታዘዛቸዉ ጦር በሚቆጣጠረዉ አካባቢ ሕዝብ እንኳን በቂ ድጋፍ የለዉም።ተዋጊዎቻቸዉን ለማስተባበርና ለመምረት መንቀሳቀስ አይችሉም። የመሸጉበት ቱርክ፥ የሚደግፏቸዉ የዓረብና የምዕራባዉያን መንግሥታት ለጦራቸዉ እሳቸዉ የሚመኙትን የጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ ታማኝነቱን አላገኙም።በዚሕ መሐል ነዉ፥- ጄኔራሉ የአሰድን ስርዓት ሲፈጥን-በወር፥ ሲዘገይ በሰወስት ወር አስወግዳለሁ የሚሉት።

ጄኔራሉ እንዳቀዱት፥ የበላይ-የበታቾቻዉ እንደሚተመኙት፥ ደጋፊዎቻቸዉ እንደፈለጉት የአሰድ ሥርዓት ቢወገድ አስወጋጆቹ ሶሪያን የሚመሩበት ሥልት-ዝግጅታቸዉን ሊያስታዉቁ ቀርቶ ሐገር ለመምራት የማቀድ-መዘጋጀቱን አስፈላጊነት እንኳን በግልፅ አላስታወቁም።ይሕ ነዉ እንደ ብዙ የሶሪያዊዉያን ሁሉ የሶሪያዊዉ ጋዜጠኛ ሥጋት፥ ይሕ ነዉ-እንደ ብዙዉ የዉጪ የጦር ባለሙያ ሁሉ የብሪታንያዉ ጄኔራል ትችት መሠረት።

እና ምናልባት ሶሪያ ዳግማዊት ኢራቅ፥ አፍቃኒስታን ወይም ሊቢያ የመሆንዋ ጥፋት ምልክት።

ያ-አሜሪካዊዉ ወፈፌ ወጣት ሃያ-ሕፃን ተማሪዎችን ከስድስት አስተማሪዎቻቸዉ ጋር የመረሸኑ አስደንጋጭ ክስተት ዛሬም በአስረኛ ቀኑ የትልቂቱ ሐገር ትልቅ ሕዝብ ትልቅ ርዕስ፣ ለተቀረዉ አብዛኛ ዓለም የብዙ ጥያቄ፣ የትዝብት ግራሞት ሰበብ እንደሆነ ነዉ።

እርግጥ ነዉ አሜሪካ ከልዕለ-ሐያልነቱ መንበር ብቻዋን ተደላድላ የመቀመጧ ሚስጥር ከሐብቷ ግዝፈት፣ ከእዉቀት፣ ብልሐቷ፧ርቅቀት ይበልጥ ከጦር መሳሪያዋ አይነትና ብዛት የሚተረተር ሐቅ መሆኑ አንድ ሁለት አላሰኘም።የጦር መሳሪዋ እንደ መርሕ፣ ጥቅሟ ሁሉ የተቃርኖ እርምጃ ጉዞዋ መሠረትነቱ ለዜጎችዋም፣ ለታዛቢ፣ ከጃይ ተከታዮቿም እንግዳ አይደለም።


የዓለም ድሐ፣ በሽተኛ፣ ረሐብተኞችን የመርዳት ለጋስነቷ፣ የመሳሪያዋን የማጥፋት አቅም በማሳደጓ ጥፋት የሚጣፋባት፣ ለተበዳዮች መብት ነፃነት የመሟገቷ ሰናይ፥ ብዙ አጥፊ ጦር መሳሪያ ብዙ ከማምረቷ ሐቅ፣ ለጨቋኞች ሳይቀር ከመሸጥ ማስታጠቋ እኩይ ጋር የሚቃረንበት፣ ለዓለም ሠላም የመሟገቷ ጥሩ፥ ብዙ አጥፊ መሳሪያ በታጠቀ ጦሯ ብዙ ከማስጥፋቷ መጥፎ ጋር መላተሙ የሁሌም እንጂ የትናንት ወይም የዛሬ ብቻ እዉነት ብአይደለም።


የዜጎቿን ደሕንነት ለማስጠበቅ የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲ ከሁሉም በላይ የጦር ጉልበቷን በድፍን ዓለም ለማዝመት የማታመነታዉ ትልቅ ሐገር፥ ሕዝቧን ብዙ በማስታጠቅ፣ ብዙ በማስገደልም ዓለምን የመምራቷ-ሐቅም ድንቅ ተቃርኖ ነዉ።የበቀደሙ ግድያ የፈጠረዉ ንዝረት፣ ድንጋጤ፣ ሐዘን ሲሰከንም፣ የዚያች ሐገር ነባር የእኩይ ሰናይ ቅይጥ ታሪክ ቁንፅል እዉነት ከመሆን አያልፍም።ያም ሆኖ ንዝረት ድንጋጤዉ የዋሽግተን መሪዎችን ሳይቀር እንባ አራጭቷል።የዋሽግተኖች የዉስጥ ጉድ-ድንጋጤ ሶሪያን አላስረሳቸዉም።የፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድን መንግሥት ይደግፋሉ ያሏቸዉን የሊባኖድ ፖለቲከኛ ባሸባሪነት ፈረጁ።

«ይሕ (እርምጃ) እኛ ባለን ግንዛቤ እና የአሰድ ደጋፊዎች አጎራባች ሐገራትን ማወክ እንዳይችሉ ለማድረግ ባለን ቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትሷ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ቪክቶሪያ ነላንድ-ባለፈዉ ሰኞ።

ዋሽግተኖች በቀድሞዉ የሊባኖስ ሚንስትር ሚሼል ሳመሐ ላይ የወሰዱት እርምጃ የሶሪያ አማፂ መሪ ጄኔራል ሳሊም ኢድሪስንም ሆነ ስደተኛዉን ጋዜጠኛ ማሊክ አብዴሕን ባያስደስት እንኳን የሚያስከፋ አይደለም።ለሶሪያና ለአካባቢዋ ሠላም የሚተክረዉ መኖር-አለመኖሩ ግን በርግጥ ግልፅ አይደለም።

በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት የስለላ ጉዳይ ኮሚቴ መሪ እንደራሴ ማይክ ሮጀርስን ብዙ ያስጨነቀዉ ግን ከሶሪያ ሰላም ይልቅ በሶሪያ ምሥቅልቅል መሐል የሐገሪቱ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ከማን እጅ ይወድቅ ይሆን የሚለዉ ነዉ።

«የኬሚካል ጦር መሳሪያዎቹ እንደተከማቹባቸዉ የምናዉቃቸዉ አንዳድ አካባቢዎች ከመንግሥት ሐይላት ቁጥጥር እየወጡ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ የመደበኛ መሳሪያቸዉ ረቂቅነትም በጣም ያሳስበናል።በአብዛኛዉ ከሩሲያ መንግሥት የተገኙት እነዚሕ መሳሪያዎች በጣም ብዙ ናቸዉ።እንዲሕ ዓይነት የሥርዓት ለዉጥ ሲደረግ ለረጅም ጊዜ የፀጥታ ክፍተት እንደሚፈጠር እናዉቃለን።በዚሕ ክፍተት ደግሞ እነዚያ የጦር መሳሪዎች መጥፎ ነገር ከሚያደርጉ ወገኖች እጅ እንዳይገቡ ያሰጋል።»

የአሰድን ሥርዓት ለመዋጋት አንዳድ ዘገቦች እንደሚጠቁሙት የሰባ ዘጠኝ ሐገራት ዜጎች ዘምተዋል።የየጎጡን ተዋጊ ቁጥር የቆጠረዉ የለም።ጄኔራል ሳሊም ደማስቆን ዳግም የሚረግጡበትን ቀን ከማስላት ዉጪ ለቁጥር የሚታክተዉን ታጣቂም ሆነ አስጊዉን ጦር መሳሪያ የሚቆጣጠሩበት አቅም፥ ፍላጎት ሐሳቡም ያላቸዉ አይመስልም።

የብሪታንያዉ የመካካለኛዉ ምሥራቅና የሰሜን አፍሪቃ ጉዳይ ምክትል የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አላስተር በርትን እንደሚሉት በተለይ የኬሚካል ጦር መሳሪያዉ ከማይሆኑ ሰዎች እጅ ገብቶ አካባቢዉን እንዳያፋጅ ፈጣን እርምጃ ሥለሚወሰድበት ሥልት መንግሥታቸዉ ይመለከታቸዋል ከሚላቸዉ መንግሥታት ጋር እየተናገረ ነዉ።

የሶሪያ አማፂያን ዕቅድ አልባ-ዕቅድ፥ የዋሽግተን፥ ለንደን ፖለቲከኞች የመጨረሻ ሰዓት ጥድፊያ፥ ሩጫ፥ ብሪታንያዊዉን ጄኔራል ቲም ክሮስን ሳያሰገርም አልቀረም።የፕሬዝዳት ሳዳም ሁሴን መንግሥት በተወገደ ማግስት ኢራቅ ዘምተዉ የነበሩት ጄኔራል ሥርዓትን ለማስወገድ ብቻ ያለመ ዉጊያ፥ጦርነት የሚያስከትለዉን ጥፋት ከትምሕር ቤት፥ ከፊልም ወይም ከቴሌቪዥን ሳይሆን ኢራቅ ኖረዉበት፥ ምስቅልቅሉን ለማስወገድ ሰርተዉበትም፥ አልሳካ ብሏቸዉም ያዉቁታል።

«ምዕራቡ ይሕን የሶሪያን ጉዳይ በተገቢዉ መንገድ ይዞታል ብዬ አላስብም» አሉ ጄኔራሉ ከትናንት በስቲያ።«አሰድን ለማዉገዝ፥ ለማግለልና ኢሰብአዊ ለማድረግ በጣም ተጣድፈናል።አሁን መዘዙን እያየን ነዉ።» አከሉ።ብሪታንያ የሚኖረዉ ሶሪያዊ ጋዜጠኛ የማሊክ አብዴሕ ሥጋት ደግሞ የኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ይዞታ ብቻ አይደለም።ሶሪያ ሥርዓተ አልበኝነት ይሰፍንባታል የሚለዉ ጭንቀት ጭምር እንጂ።

«ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ከሌለ» ይላል ጋዜጠኛዉ ዩናይትድ ስቴትስ፥ ብሪታንያም ሆነች መላዉ ምዕራባዊ ዓለም የሚፈይዱት ነገር የለም።የአሰድ ሥርዓት ሲወገድ ጦሩ ከተበተነ ሶሪያ ቢያንስ ለአምስት አመት ካሁኑ ይበልጥ ትመሰቃቀላለች።» እያለ ቀጠለ ጋዜጠኛዉ።

የበሽር አል-አሰድ ሥርዓትን መወገድ እኩል የሚደግፉት የሶሪያ አማፂ መሪ፥ ጋዜጠኛ፥ የአማፂያኑ ደጋፊ ሐገራት ፖለቲከኞች እና የጦር ባለሙያዎች፥ በተቃርኖ ሐሳብ ሲፋጩ፥ የደማስቆ መንግሥት ደጋፊ የምትባለዉ ኢራን «የሰላም ዕቅድ» ያለችዉን ሐሳብ ሰንዝራ ነበር።የምዕራባዉያኑ የማዕቀብ ዱላ ከሶሪያ እኩል የሚደቁሳት ኢራን አቀረበች የተባለዉ ባለሥድስት ነጥብ የሰላም ሐሳብ የዓለም ዘዋሪዎችን ትኩረት ሊስብ ቀርቶ ለመገናኛ ዘዴዎቻቸዉ የዜናነት ሚዛን እንኳን የሚደፋ አልነበረም።

እንደ ቴሕራን ሁሉ የደማስቆዎች ደጋፊ የሚባሉት የሞስኮ ባለሥልጣናት የሚሉ የሚያደርጉትን ግን ወቃሽ፣ ተቺዎቻቸዉ፥ መገናኛ ዘዴዎቻቸዉም ጭምር እንደ ቴሕራኖች ሊዘጉት አይችሉም። የቴሕራኖች ዕቅድ-መኖሩ ሳይነገር፣ በወደቀ በአራተኛዉ ቀን የሩሲያዉ ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቱን ከሞስኮ ተናገሩ።ሐሙስ።

«ሩሲያ የበሽር አል-አሰድ ሥርዓት ሕልዉና አያስጨንቃትም።ይሕ ቤተ-ሰብ ለላለፉት አርባ ዓመታት በሥልጣን ላይ መቆየቱን እናዉቃለን።ለዉጥ እንደሚያስፈልግ አያጠያይቅም።የዛሬዎቹ ተቃዋሚዎች ሥልጣን የሚይዙ ከሆነ፥ የዛሬዎቹ የመንግሥት መሪዎች በተገላቢጦሹ ተቃዋሚ ሆነዉ
ጦርነቱ እንዲቀጥል አንፈልግም።ሩሲያ በዚያ አካባቢ ጥቅም ስለሌላት ጥቅሟን ለማስከበር የሚያሳስባት ነገር የለም።ሐገሪቱንና አካባቢዉን ከጥፋት ለማዳን ግን ለችግሩ ትክክለኛ መፍትሔ እንዲገኝ እንሻለን።የሩሲያ አቋም ተፋላሚ ሐይላት የራሳቸዉን ፀጥታና ደሕንነት ለማስከበር፥ በመንግሥታዊ አስተዳደር ለመጋራትና ሐላፊነትን ለመዉሰድ እንዲስማሙ ማድረግ ነዉ።የዚሕ ተቃራኒዉ አይደለም።በጦርነት የሚመጣ የሥርአት ለዉጥ ለሶሪያ ሕዝብም ለመላዉ አካባቢዉም ዉጤታማ ሊሆን አይችልም።»

ፑቲን መንግሥታቸዉን የሚያሰጋዉ የሶሪያዉ ፕሬዝዳንት የበሽር አል-አሰድ ሕልዉና ሳይሆን የሶሪያ እና የአካባቢዉ ሠላምና ደሕንነት ነዉ ማለታቸዉን አንዳድ የፖለቲካ ተንታኞች ሩሲያ ከቀድሞ አቋሟ የማፈግፈጓ ማረጋገጪያ አድርገዉ ተርጉመዉታል።


የድሕረ-ዚያድ ባሬዋን ሶማሊያ፣ የድሕረ ታሊባኗን አፍቃኒስታን፣ የድሕረ-ሳዳሟን ኢራቅ፣ የድሕረ ቃዛፊዋን ሊቢያን እልቂት፣ ፍጅት፣ ዉድመት ጥፋት ያየ-የሰማ ግን የሶሪያ የወደፊት እጣ አያሰጋዉም ማለት በርግጥ ጅልነት ነዉ።በእስካሁኑ ጦርነት ብቻ በትንሽ ግምት ከአርባ ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ከመቶ ሺሕ በላይ ቆስሏል።ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ተሰዷል።አራት ሚሊዮን ተፈናቅሏል።አማፂያን ዛሬ እንዳስታወቁት አንድ የመንግሥት የጦር አዉሮፕላን ጥለዋል።እና ጦርነቱ ቀጥሏል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ለዛሬ ይብቃን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ








A Free Syrian Army soldier walks next to a burned tractor in Sarmin, north of Syria, Tuesday, Feb. 28, 2012. According to the residents of the city at least fourteen people were killed yesterday during clashes between the Free Syrian Army and President Assad's forces. (Foto:Rodrigo Abd/AP/dapd) Die Freie Syrische Armee (arabisch ‏الجيش السوري الحر‎ al-Dschaisch as-Suri al-Hurr, französisch Armée syrienne libre, Kürzel ASL) ist die größte bewaffnete Oppositionsgruppe in Syrien.[2] Sie ist mit dem Syrischen Nationalrat verbunden.[
አማጺያኑምስል AP
Syrien01: Mädchen in Syrischen Flüchtlingslager Autor: Marine Olivesi Ort: Boynuyogun Flüchtlingslager Datum: 06/02/2012 ### Unser Autor hat uns die Bilder geschickt und uns die Erlaubnis gegeben die zu publizieren in Zusammenhang mit ihrer Geschichte über ein Flüchtlingslager an der Syrien/Türkei Grenze. ###
ሰደትምስል Marine Olivesi
A view shows the wreckage after a car bomb exploded near a police station in the central Bab Touma district of Damascus October 21,2012, in this handout photograph released by Syria's national news agency SANA. Ambulances sped to the site and security forces cut off access to the area. Several cars were burnt, the witnesses said.The explosion took place as President Bashar al-Assad was meeting international envoy Lakhdar Brahimi, who has called for a temporary truce in Syria's civil war. REUTERS/Sana (SYRIA - Tags: CIVIL UNREST MILITARY POLITICS CONFLICT) FOR EDITORIAL USE ONLY. NOT FOR SALE FOR MARKETING OR ADVERTISING CAMPAIGNS. THIS IMAGE HAS BEEN SUPPLIED BY A THIRD PARTY. IT IS DISTRIBUTED, EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS
የጦርነቱ ጥፋት-ደማስቆምስል Reuters
Rebel fighters have lunch in the old sector of the northern city of Aleppo, on October 23, 2012. Violence raged across war-torn Syria a watchdog said, dimming hopes of a ceasefire for this week's Muslim Eid al-Adha as proposed by UN-Arab League envoy Lakhdar Brahimi. AFP PHOTO/PHILIPPE DESMAZES (Photo credit should read PHILIPPE DESMAZES/AFP/Getty Images)
የጦርነቱ ጥፋት-አሌፖምስል PHILIPPE DESMAZES/AFP/Getty Images
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ