1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ እዉነት እና የሐያላኑ ልዩነት

ማክሰኞ፣ ጥር 29 2004

ሩሲያ ያልተቀበለችዉን ረቂቅ የሚተካ ሌላ ረቂቅ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት አሰራጭታም ነበር።በዩናይትድ ስቴትስ ዘነድ ተቀባይነት አላገኘም።እነዚሕ ሁለቱ ሐገራት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣናቸዉን እንዲጠቀሙ እንደምክንያት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናችዉ።

https://p.dw.com/p/13y8l
Member states vote on a draft resolution backing an Arab League call for Syrian President Bashar Assad to step down, which was later vetoed by Russia and China, during a meeting of the United Nations Security Council at UN headquarters Saturday, Feb. 4, 2012. The unusual weekend session comes as Syrian forces pummel the city of Homs with mortars and artillery in what activists are calling one of the bloodiest episodes of the uprising. (AP Photo/Jason DeCrow)
የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትምስል dapd


ከሮብ-እስከ ቅዳሜ ቻይናን የጎበኙት የጀርንዋ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የቤጂግ ጉዟቸዉን ያጠናቀቁት ከፕሬዝዳት ሁ ጂንታኦ ጋር እንደ ጥሩ ወዳጅ መክረዉ፣ጥሩዉን ለማጠናከር ተስማምተዉ ነዉ-ነበር-የተባለዉ።ሜርክል ወደ በርሊን-ሲያቀኑ ሙኒክ ጉባኤ የተቀመጡት የቤጂንግ፥-የዋሽግተን፥የሞስኮ ትላልቅ ዲፕሎማቶች የመሰብሰባቸዉ-ሰበብ በማያግባቧቸዉ ለመግባባት ተብሎ ነበር።የሜርክሏ ጀርመን ያስተናገደችዉ ጉባኤ-ሒደት ሳይታወቅ ትንሺቱ ሶሪያ-የትላልቆቹ ትልቅ ልዩነት መሠረትነቷ ከኒዉዮርክ ፈጋ።ቅዳሜ።የሶሪያ እዉነት፣ የሐያላኑ ልዩነት፣ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ረቂቅ ዉሳቄ ዉድቀት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።


የፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ አስከሬንን እንደ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ባደባባይ ተዘረርሮ ለማየት የተመኙት፥ ወይም አሰድ እንደ ሜሎሶቪች እንደ ቴለር እንደ ባግቦ ዘብጥያ ሲወረወሩ ማየት ለፈለጉት፥ይሕ ቢቀር የደማስቆ ገዢዎች ምናልባት ወደ ቴሕራን እንዲሰደዱ ለሚሹት ተቃዋሚዎቻቸዉ በርግጥ አሳዛኝ ዕለት ቀን ነዉ።

የዶሐ ገዢዎች ምክንያት-አለማ ብዙ ያነጋግር ይሆናል። ምኞት-ፍላጎታቸዉ ግን ከደማስቆ መንግሥት ተቃዋሚዎች የተለየ ነዉ ማለት አይቻልም።የቀጠሩ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር ደ ኤታ ኻሊድ መሐመድ ኤ.አል-አቲያሕ ትናንት እንዳሉት አለቆቻቸዉ የመሩና የዘወሩት የአረብ ሊግ አጥብቆ የታገለለት ረቂቅ ዉሳኔ ዉድቅ የሆነበት ዕለት አሳዛኝ ቀን ነዉ።

«እንደ አለመታደል ሆኖ ትናንት አሳዛኝ ቀን ነዉ።ይሕ በትክክል እንዳይሆን የምንፈራዉ ነበር።ይሕ በትክክል ለሩሲያዎችና ለቻይናዎች ለአል-አሰድ የማይሆን ምልክት ካሳዩ የመግደል ፍቃድ ከመስጠት እኩል እንደሚቆጠር ያስጠነቀቅናቸዉ ነዉ-የሆነዉ።»

ሚንስትር ደኤታ አል-አቲያሕ ሥለ ማን፥ ምን እንደሚናገሩ ብቻ ሳይሆን መቼ እንደሚናገሩም ጠንቅቀዉ አዉቀዉታል።ያሉትን ያሉት እሁድ ነዉ።ቀጠር በግንባር ቀደምትነት ያስረቀቀችዉን የዉሳኔ ሐሳብ ሩሲያና ቻይና ድምፅን በድምፅ በመሻር ሥልጣናቸዉ ዉድቅ ያደረጉት ግን ቅዳሜ ነበር።

የዶሐ ሹማምንት እራሳቸዉ ያሥረቀቁት፥ እንዲፀድቅ አጥብቀዉ የተመኙትን የዉሳኔ ሐሳብ ዉድቅ ያደረጉባቸዉን ትላልቆቹን መንግሥት ባደባባይ ለመቃወም ማዉግዝ መጠበቅ ነበረባቸዉ።ምናልባትም የሚሉ-የሚያደርጉትን የሚያስብሉ-የሚያስደርጓቸዉን ወገኖች ምኞት-ፍላጎትን እሲኪያዉቁ ለማወቅ ከሃያ-ሰዓታት በላይ ጠበቁ።በዚሕ ጊዜ ዉስጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሱዛን ራይስ-ከዚያዉ ከኒዉዮርክ ያሉት በድፍን ዓለም መገናኛ ዘዴዎች ከብዙ ጊዜ በላይ ተደጋግሟል።

«የኛ መሠረታዊ አላማ ከግብ እንዳይደርስ የሚያደናቅፉ ጥቂት የዚሕ ምክር ቤት አባላት አሉ።አላማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣዉን የሶሪያን ቀዉስና እያደገ ለመጣዉ ለአካባቢዉ የሠላምና የፀጥታ ሥጋት መፍትሔ መፈለግ ነዉ።»

ከዩናይትድ ስቴትስ፥ እስከ ብሪታንያ፥ ከፈረንሳይ እስከ ጀርመን ያሉ አስራ-ሰወስት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚና ተለዋጭ አባላት ረቂቅ ዉሳኔዉን ድምፅ-በድምፅ የሻሩትን ሩሲያና ቻይናን ከወቀሱ፥ ካወገዙ በጥዋላ ቀጠሮች የዋሽንግተኖችን ምኞት ፍላጎት ከዶሐ-ለማስተጋባት የሚያሰጋቸዉ ነገር የለም።

እርግጥ ነዉ ዕለቱ ለአል-አሰድ ተቃዋሚዎች፥ ተቃዋሚዎቹን ለሚረዱት መንግሥታት፥ ለዩናይትድ ስቴትስና ለተባበሪዎቿ ብቻ ሳይሆን ረቂቁን ዉድቅ ላደረጉትም መንግሥታት አስደሳች አልነበረም። ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሩሲያዉ አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን እንዳሉት ሩሲያም ሆነች ቻይና ያደረጉት ማድረግ የነበረባቸዉን ነዉ።«ረቂቅ ዉሳኔ ዉድቅ ሲሆን ጥሩ ቀን አይሆንም።ግን እንዳለ መታደል ሆኖ ይሕ ከነዚያ ቀናት አንዱ ነዉ።»

ዕለቱ ያለ አበሳዉ የሚረገም፥የሚወገዝበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።ለፖለቲካ አዋቂ አስተንታኞች ግን-አንድ ነገር አስታዉሷል።ወይም የሆነ ትዝታ ቀስቅሷል።የምሥራቅ-ኮሚንስትችና የምዕራብ ካፒታሊስቶችን የፍጥጫ ወይ’ም የቀዝቃዉ ጦርነት ዘመንን።ከዚሕ ዉጪ ሩሲያና ቻይና ረቂቁ ካልተሻሻለ ድምፅን በድምፅ በመሻር ሥልጣናቸዉ ዉድቅ እንደሚያደርጉት ደጋግመዉ አስታዉቀዉ አስታዉቀዉ ነበር።የቅዳሜ አቋማቸዉ የፖለቲካዉን አዋራ ከማጤስ ባለፍ የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት የሚጠበቅ ነበር።

የአረብ ሊግ የዉሳኔ ሐሳብ እንደሚጠይቀዉ የፕሬዝዳንት በሽር አል-አሰድ መንግሥት ሥልጣን መልቀቅ አለበት።የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች በተለይም ጦር ሐይሉ ከከተሞች መዉጣት አለበት።ረቂቁ እንዴት ለሚለዉ ጥያቄ መልስ አይሰጥም።የሩሲያዉ አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን ባለፈዉ ማክሰኞ እንዳሉት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የአባል መንግሥትን መሪ የመሾምና የመሻር ሥልጣን ሐላፊነትም የለበትም።የሁለቱ ሐገራት ጥያቄ ረቂቁ የዉጪ የዉጪ ጦር ጣልቃ እንዳይገባ ዋስትና በሚሰጥ መልኩ እንዲሻሻል ወይም እንዲዘጋጅ ነበር።ከብዙ ድርድርና ዉይይት በሕዋላ መጠነኛ መሻሻል ቢደረግበትም የሞስኮና የቤጂንግን ፍላጎት የሚረካ አይነት ግን አልሆነም።

ሩሲያ ያልተቀበለችዉን ረቂቅ የሚተካ ሌላ ረቂቅ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት አሰራጭታም ነበር።በዩናይትድ ስቴትስ ዘነድ ተቀባይነት አላገኘም።እነዚሕ ሁለቱ ሐገራት ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣናቸዉን እንዲጠቀሙ እንደምክንያት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናችዉ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን ግን ሞስኮና ቤጂንግን የአል-አሰድን አረመኔ መንግሥት የደገፉ በማለት ነዉ ያወገዟቸዉ።

«የትናንቱ ቀን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማርባ ቀን ነበር።እነዚያ የአረብ ሊግ እቅድን አንቀበልም ያሉ ሐገራት የደማስቆን የጭካኔ እርምጃ ለመደገፋቸዉ ሐላፊነት መዉሰድ አለባቸዉ።»

የዓል-ሐስካብ፥ ሶሪያዉ ተወላጅ ሐሰን ዓሊ አክላሕ አካሉ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ እራሱን ያጋየዉ እንደ ቱኒዚያዉ መሐመድ ቡአዚዚ የደረሰበትን ብሶት-ግፍ በደል ሲሆን ለዓለም ይሕ ቢቀር ለሐገሩ ሕዝብ ለማሳየት ነበር።ሐሰን እራሱን ካጋየ ጥር ሃያ-ስድስት (ዘመኑ በሙሉ እጎአ ነዉ) ዓመት አለፈዉ።በራሱ ላይ የለኮሰዉ እሳት እንደ ቡአዚዚ ሁሉ የሶሪያን ሕዝብ ለአመፅ ማነሳሳቱ አልቀረም።ሕዝባዊ አመፅ ግን እንደ ቱኒዚያ ወይም እንደ ግብፅ በሰላም እንደተጀምረ በሰላም ከመቀጠል ይልቅ እንደ ሊቢያ በአደባባይ ሠልፍ ተጀምሮ-በጠመንጃ ግጭት ዉጊያ እያዘገመ ነዉ።

በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎችና በታጣቂዎች መካካል በተደረገዉ ግጭት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ከአምስት ሺሕ በላይ ሰዉ ተገድሏል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ወደ ቱርክ ተሰዷል።የአል-አሰድ መንግሥት በተለይም ሶሪያን ከአርባ አመት በላይ የገዛዉ የበዓዝ ፓርቲ አገዛዝ አረመኔነት፥ በሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉ ግድያ-እንግልት ልክ የለሽነት አላነጋገረም።

የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት ግን ልዩ የፖለቲካ ጥቅም ካለዉ በስተቀር ሊቢያ ላይ የተፈፀመዉን ያየ-ሶሪያ እንዲደገም አይመኝም።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መጋቢት አስራ-ሰባት ሁለት ሺሕ አስራ አንድ ያፀደቀዉ ዉሳኔ ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለማዳን የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ተዋጊ ጄቶች እንዳይበሩ መከልከል የሚል ነበር።

ከበረራ እግድ ቀጠናን ለማስከበር በሚል ሽፋን የዘመተዉ የምዕራባዉን ጦር ከሊቢያ አማፂያን ጋር ተባብሮ ከኮሎኔል ቃዛፊ መንግሥት ጋር በገጠመዉ ዉጊያ በትንሽ ግምት ከሰላሳ ሺሕ በላይ ሰዉ አልቋል።ከሐምሳ ሺሕ በላይ ቆስሏል።ከአንድ ሺሕ አምስት መቶ የሚበልጥ አፍሪቃዊ ስደተኛ ባልሰራዉ ወንጀል ዉሐ በልቶታል።በኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መንግሥት ላይ የተላለፈዉ ዉሳኔ እንዲተላለፍ የጠየቀዉ የአረብ ሊግ ነበር።የሶሪያዉንም የአረብ ሊግ።

ሩሲያና ቻይና በሊቢያ ላይ እንዳደረጉት በሶሪያ ላይ የቀረበዉን በድምፀ ተአቅቦ ሊያልፉት አልፈለጉም።ሻሩት።ምክንያት-ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እንዳሉት ረቂቁ ወገናዊ ነዉ።«ይሕ ከእዉነታዉ የራቀ ነዉ።የታጠቁ አማፂያን ሐይላት የከተሞችን የተወሰኑ አካባቢዎች እየተቆጣጠሩ የሶሪያ መንግሥት ከነዚሑ ከተሞች ጦሩን እንዲያስወጣ መጠየቅ ሊሆን የማይችል ነዉ»

የአሜሪካና የተሻራኪዎቻቸዉ ፍላጎት ግልፅ ነዉ።እስራኤልን የሚተናኮለዉ፥ ከኢራን የሚተባበረዉ፥ ሊባኖስ ዉስጥ እጁን የሚዶለዉ የአሰድ መንግሥት መወገድ አለበት።አንዳድ የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት ነገስታት የሚመሯቸዉ የአረብ መንግሥታት የዘመናት ተቃዉሞ ጥላቻቸዉን ለመበቀል፥ እንደ ቱኒዚያና ግብፅ በሕዝባዊ አመፅ፥ እንደ ሊቢያ በጠመንጃ ዉጊያ ሥልጣን የያዙት የአረብ መንግሥታት ብጤያቸዉን ሥለሚፈልጉ የአሰድ መንግሥትን መወገድ ይደግፋሉ።ቱርክ ለረጅም ጊዜዉን የኩርዶች ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ ባታገኝ ለማስተንፈስ የደማስቆ መንግሥት መለወጡን ትፈልገዋለች።

ሩሲያ ግን የጦር መሳሪያ ደንበኛዋን፥ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት ተሻራኪዋን ማጣት አትሻም።ቻይና የጥሩ ገበያዋን መሠረት ለሌሎች አሳልፋ መስጠት አትፈልግም።እና ሞስኮና ቤጂንግ-ሶሪያ ሊቢያ አይደለችም አሉ።እንቢኝ።ይሕ ማለት ግን የሶሪያ ጉዳይ ከፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ርዕስነት አበቃ ማለት አይደለም።ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል ቤጅግ ዉስጥ ምናልባት ሶሪያን ስለሚመለከተዉ ረቂቅ ዉሳኔ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር በዝግብ በር ሲነጋገሩ-መካከለኛዉ ምሥራቅ የነበሩት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ጊዶ ቬስተር ቬለ በግልፅ አንስተዉት ነበር።አሁንም የሶሪያን ቀዉስ ለማስወገድ እንጥራለን ይላሉ የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር።

ግን የደማስቆ መንግሥትና የአማፂያን ዉጊያ እንደቀጠለ ነዉ።የአደባባይ ሰልፉም እንዲሁ።መቼና እንዴት ያበቃ ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ




















In this picture taken on January 6, 2012 and released by the citizen journalism image provide by the Local Coordination Committees in Syria, anti-Syrian regime protesters, hold a placard against Syrian President Bashar Assad with Arabic words read:"The lions look like this," during a demonstration, in Edleb province, Syria. Throughout 40 years of Assad family dictatorship, one thing united Syrians _ the culture of self-censorship, fear and paranoia. But the uprising against President Bashar Assad has unleashed a burst of blunt irreverence and black humor that would have been unthinkable before, when any satire had to be indirect or hidden. (Foto:Local Coordination Committees in Syria/AP/dapd) EDITORIAL USE ONLY, NO SALES, THE ASSOCIATED PRESS IS UNABLE TO INDEPENDENTLY VERIFY THE AUTHENTICITY, CONTENT, LOCATION OR DATE OF THIS HANDOUT PHOTO
አሰድና ሕዝባቸዉምስል AP
Demonstrators protest against Syria's President Bashar al-Assad in the town of Hula near the city of Homs February 3, 2012. Picture taken February 3, 2012 REUTERS/Handout (SYRIA - Tags: POLITICS) THIS IMAGE HAS BEEN SUPPLIED BY A THIRD PARTY. IT IS DISTRIBUTED, EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS. FOR EDITORIAL USE ONLY. NOT FOR SALE FOR MARKETING OR ADVERTISING CAMPAIGNS
ተቃዉሞዉምስል Reuters
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ