1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ የሠላም ድርድር

ዓርብ፣ የካቲት 17 2009

በትናንትናዉ ዕለት የመንግስትና የተቃዋሚ ኃይሎች ተወካዮች ለመጀመሪያ ጊዜ ለድርድሩ ፊት ለፊት ተገናኝተዋል። በዛሬዉ ዕለትም የሰላም ድርድሩ በተናጠል ተካሂዷል። በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት በጀኔቭ ስዊትዘርላንድ የሚካሄደዉ ይሄዉ ድርድር በሶሪያ ላለፉት 6 አመታት የዘለቀዉን ከባድ ጦርነት ለማስቆም በአንዳንዶች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል።

https://p.dw.com/p/2YDx1
Schweiz Genf Staffan de Mistura
ምስል Getty Images/AFP/F. Coffrini

UN Syria talks open in Geneva, - MP3-Stereo

  በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም በመካከለኛዉ ምስራቅና በሰሜን አፍሪቃ አንዳንድ የአረብ ሀገሮች የተካሄደዉን «የአረብ  አብዮት » ተከትሎ በሶሪያ የተቀሰቀሰዉ ፀረ-መንግሥት ተቃዉሞ  ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከተሸጋገረ እነሆ ስድስት አመታትን አስቆጥሯል። ከጦረነቱ በፊት የ11 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ የነበረችዉ ሶሪያ፤ የተረጋጋ ሰላም ያላት ፣ በኢኮኖሚ አቅሟም ቢሆን መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ ሃገራት ተርታ የምትመደብ ነበረች።
ላለፉት 17 ዓመታት ስልጣን ላይ በሚገኙት በበሽር አልአሳድ መንግሥትና ነፍጥ ባነሱ ተቃዋሚ ኃይሎች መካከል በሚደረገዉ ጦርነት ሳቢያ ግን በየዕለቱ በቦምብ አረር የምትታረስ ፣ ሕጻፃናት የሚሞቱባት፣ ዜጎቿም ሕይወታቸዉን ለማትረፍ ጥለዋት የሚሸሹ ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረች ሀገር ሆናለች።
ሀገሪቱን ከገባችበት ቀዉስ ለማዉጣት በተቀናቃኞቹ ኃይሎች መካከል በተደጋጋሚ የሰላም ድርድር ለማካሄድ ተሞክሯል። በትናንትናዉ ዕለትም የመንግስትና የተቃዋሚ ኃይሎች ተወካዮች ለመጀመሪያ ጊዜ ለድርድር  ፊት ለፊት ተገናኝተዋል። በዛሬዉ ዕለትም የሰላም ድርድሩ በተናጠል መጀመሩም  ከወደ ጄኔቫ  ተሰምቷል። 
ከ 3 አመታት ወዲህ የመጀመሪያ ነዉ የተባለዉ ይሄዉ የቀጥታ የሰላም ድርድር በተባበሩት መንግሥታት ሸምጋይነት የሚካሄድ  ሲሆን ፤ በመንግሥት በኩል አምባሳደር በሻህ አልጃፋሪ በተቃዋሚ ኃይሎች በኩል ደግሞ ነስሪ አልሃራሪ ዋነኛ ተደራዳሪወች ሆነዉ ቀርበዋል። 
መቀመጫቸዉን  በሩሲያና በግብፅ ያደረጉና በጀኔቫ ስዊዝ የሚገኙ ሌሎች የተቃዋሚ ቡድኖች በድርድሩ ለመሳተፍ  ቢፈልጉም  በምህጻሩ ኤን ኤች ሲ የተባለዉ የተቃዋሚ ቡድኖች ከፍተኛ ተደራዳሪ ኮሚቴ  ግን  በሰላም ንግግሩ ብቸኛዉ የአማጽያን ተወካይ ሆኖ ቀርቧል።
ዉይይቱ ካሁን ቀደም ከተደረጉት 3 የሰላም ድርድሮች በቀጥታ ፊት ለፊት ተገናኝቶ በመነጋገር ረገድ የመጀመሪያና በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለዉን ጦርነት ለማስቆም በአንዳዶች ዘንድ ተስፋ የተጣለበት መሆኑ ተመልክቷል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶሪያ ልዩ መልክተኛ ስቴፋን ዲ ሚስቱራ የሁለቱ ወገኖች ዋና አደራዳሪ ናቸዉ። እሳቸዉ እንደሚሉት ጦርነቱን ለማስቆም የተናጠል ሥራ አያዋጣም ።
 «አሁን የሶሪያንና የህዝቦቿን ፍላጎት ስለመጠበቅ እናስብ። አብረን እንሥራ፤ ቀላል እንዳልሆነ አዉቃለሁ ነገር ግን ይህንን ዘግናኝ ግጭት ለማቆምና የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት በሰላም መሰረት ላይ ለመጣል አብሮ መስራትን መሞከር አለብን።»   
የሶርያ ተቃዋሚ ቡድኖች ዋነኛ ተደራዳሪ ነስሪ አልሃራሪ በበኩላቸዉ ዉይይቱ የፓለቲካ ሽግግር ላይ ማተኮር አለበት ይላሉ።
 «ስቴፋን ነገሩን የምር የሚወስዱት ከሆነ፤ በአጀንዳዉ ዉስጥ ቀዳሚ ርዕሰ ጉዳይ ስለሆነዉ፤ በሶሪያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ ፓለቲካዊ ሽግግር ማድረግ ላይ ማተኮር አለባቸዉ።»

Syrien russische Soldaten bei der Minenräumung in Aleppo
ምስል picture alliance/Russian Defence Ministry Press Office

ድርድሩ ተስፋ የተጣለበትን ያህል በሀገሪቱ የሚታየዉ የማያቋርጥ ጥቃትና ሞት ጥላ እያጠላበት ነዉ ያሉም አልታጡም። የሰላም ድርድሩ እየተካሄደ ባለበት በዛሬዉ እለት እንኳ የ42 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት መፈጸሙ ድርድሩን በጥያቄ ምልክት ዉስጥ ከቶታል። በሶርያ ጦርነቱ እስካሁን በመቶ ሽ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በሀገር ዉስጥ ከቤት ንብረታቸዉ አፈናቅሏል። 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ሀገር ጥለዉ ተሰደዋል።

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ