1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ የወደፊት ጉዞ

ሰኞ፣ ሰኔ 25 2004

የሶሪያን እልቂት ፍጅት ለማስቆም የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት የሚጠይቀዉን እቅድ ያፀደቁት ሐያላት ዕቅዱን እንዳሻቸዉ እንደተረጎሙት ሁሉ የሶሪያ ተፋላሚዎችም እንደፈለጋቸዉ ተርጎመዉታል።የሚዋጉት ሐይላት አንድ-ያደረጋቸዉ ነገር እቅዱን እኩል መቃወማቸዉ ነዉ

https://p.dw.com/p/15Q8C
(L-R) U.S. Secretary of State Hillary Clinton, Russia's Foreign Minister Sergei Lavrov, British Foreign Minister William Hague, France Foreign Minister Laurent Fabius, Chinese Foreign Minister Yang Jiechi and Joint Special Envoy of the United Nations and the Arab League for Syria Kofi Annan wait for the start of the meeting of the Action Group on Syria at the United Nations European headquarters in Geneva June 30, 2012. REUTERS/Denis Balibouse (SWITZERLAND - Tags: POLITICS CIVIL UNREST)
የጂኒቫዉ ጉባኤምስል Reuters

የሶሪያ መፃኤ ጉዞ በዓለም ሐያላን ዉል ተበየነ።ቅዳሜ።ሶሪያዎች ግን ይፋጃሉ።አረቦች ሥለ ሶሪያና በሶሪያ ጉዳይ እስወስት ተከፍለዉ በድብቅ ይወዛገባሉ።ቱርኮች የደማስቆ ቤተ-መንግሥትን ከደማስቆ ገዢዎች ቀምተዉ ለመረጡት ለማስረከብ ይፎክራሉ።ዋሽግተን-ሞስኮ፥ ለንደን ቤጂንጎች ይሻኮታሉ። የቅዳሜዉ ስምምነት ለዓለም ዲፕሎማቶች ጭላንጭል ተስፋ መፈንጠቁ በርግጥ አላጠያየቅም። ተስፋዉ ሚዚያ ላይ እንደተፈረመዉ የሰላም ዉል በፍጅት፣ ዉዝግቡ፣ በፉከራ ዛቻዉ ግመት፥ ከሁሉም በላይ በሽኩቻዉ ንረት ላለመደፍለቁ ምንም ዋስትና አለመኖሩ እንጂ ቀቢፀ-ተስፋዉ። የቅዳሜዉ ዉሳኔ መነሻ፣ የዋናዎቹ ተዋኞች ያለፈና ያሁን ሁነት ማጣቀሻ እድምታዉ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

«ማንያኛዉም ፖለቲካዊ ሥርዓት ለሶሪያ ሕዝብ የሚበጅ እንዲሆን ሶሪያ መራሽ የሽግግር ሥርዓት በሚመሰረትበት መርሕና የአሠራር እቅዶች ማዕቀፍ ላይ ተስማምተናል።ለወደፊቱ ሁሉም ሶሪያዋዉያን ሊጋሩት የሚችሉት መፃኤ ተስፋ ፈንጥቀናል።እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ መንግሥት በነፃ ምርጫ እንዲመሠረት፥ ሠብአዊ መብት፥ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፥ ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆኑና የአነስተኛ ማሕበረሰብ አባላት መብትና እድገት እንዲጠበቅ ተስማምተናል።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአረብ ሊግ ልዩ መልዕክተኛ ኮፊ አናን።ቅዳሜ-ጂኒቫ።ደማስቆ-ቅዳሜ።

አስሮች ሞቱ።ብዙዎች ቆሰሉ።

ቅዳሜ-ካይሮ፥-አዲሱ የግብፅ ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲይ በዓለ-ሲመታቸዉን ሲያከብሩ አዲሱ መንግሥታቸዉና «አዲሲቱ ያሏት ግብፅ» የሶሪያን ሕዝብ ፍላጎት ይደግፋሉ፣ ያከብራሉ፣ ከሕዝቡ ጋር ይተባበራሉም» አሉ።

ምሕንድስና ሲማሩ፣ ለእስልምና ሲገዙ አድገዉ፣ ምሕንድስና ሲያስተምሩ እስልምናን ሲያጠብቁ የጎለመሱት መሐመድ ሙርሲ በሐይማኖት በኩል ለተቀየጡት ፖለቲካ አማተር፣ ለዲፕሎማሲ፥ ለሐገር መሪነቱ እንግዳ፣ ለታሪክም በርግጥ ባይተዋር ናቸዉ።ቅዳሜ ለሶሪያዎች ያስተላለፉት መልዕክት አላማም የመረጣቸዉን ሕዝብ ስሜት ለማንፀባረቅ፣ የሶሪያን እልቂት አስከፊነት ለመስረገጥ ምናልባትም አቋማቸዉን ለዓለም ለማሳወቅ እንጂ የጂኒቫዉን ዉሳኔ፣ ከጥንት ታሪክ ጋር አገጣጥመዉ እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ ለመሸርደድ አልመዉ ነዉ ማለትም መረጃ አልቦ ትርጉም ነዉ የሚሆን።


ያም ሆኖ አዲሱ የግብፅ ፕሬዝዳት የግብፅ-አረቦችን ያለፈ ታሪክ፣ በተለይም ታሪክ ተሻግሮ ለዛሬ ታሪክ የተረፈዉን ደባ ግርድፍ እዉነት ለማወቅ በፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲዉ ታሪክ እንደ ምሕንድስናዉ መዶክተር አያሻቸዉም።አረብ እና ግብፃዊነታቸዉ ብቻ በቂ ነዉ።

የጂኒቫ ተሰብሳቢዎችም ዘጠኝ-ሰዓታት መክረዉ-ዘክረዉ ሥለ ሶሪያ ሲወስኑ ከሙርሲ ይበልጥ የሚያዉቁትን፥ አያት ቅድመ አያቶቻቸዉ የፈፀሙትን ያለፈ ታሪክ፥ የሚያስታዉሱበት፣ ለማስታወስ የሚጨነቁበት ሰበብ ምክንያትም አልነበረም።ድሮም ዘንድሮ አይደለም።አጋጣሚዉ ግን ዘንድሮ-ድሮን-ድሮን ዘንድሮ አስመስሎታል።ወይም በተለመደዉ አባባል ታሪክ እራሱን ደጋሚነቱን መሰከረ።

«ከሩሲያና ከቻይና ጋር ገና ሥምምነት ላይ አልደረሰንም።የሺዎችን ሕይወት ለማዳንና ዓለም አቀፍ ሐላፊነታችንን ለመወጣት መቻላችንን አላዉቅም።ይሕ በጣም ከባድ እንደሆነ ነዉ።ቢሆንም ይሕን ለማድረግ እንሞክራለን።»

የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ። ባለፈዉ አርብ።

ከዘጠና አራት ዓመት በፊት።ለንደን።የኦስማን ቱርክ ቅርብ ምስራቅ ዉስጥ ከተሸነፈች በሕዋላ «ብሪታንያን የሚያሳስበዉ ከግብፅ ሊሰነዘር የሚችለዉ ጥቃት ነዉ» የታላቅዋ ብሪታንያ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ።መጋቢት 9 1916 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)

በቀደም፥ ሔግ ከለንደን፥ ሙርሲ ከካይሮ ሥለ ሶሪያ ያሉትን ሲሉ የድሮዉን ማስታወሳቸዉ አይደለም። ያኔ፥ ዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይናም ዓለም ለመዘወር የዛሬዉ አቅም ጉልበት አልነበራቸዉም ። እንደዛሬዉ «ዓለም አቀፍ ሐላፊነት» አይባል እንጂ የጀርመኖችን እብጠት የማስተፈሱ፥ የቱርኮችን አገዛዝ የማስወገዱ «ሐላፊነትም» በትልቁ የታላቋ ብሪታንያና የፈረንሳይ፥ በትንሹ የሩሲያ ነበር።

ብሪታንያ፣ ፈረንሳይና ተከታዮቻቸዉ፣ ከጀርመን፥ ከቱርክንና ከተባባሪዎቻቸዉ ጋር የገጠሙት «የመጀመሪያዉ የዓለም» ያሉት ጦርነት አዉሮጳን አክስሎ፣ እስያና አፍሪቃን እያጋየ ነበር።አፍሪቃና እስያ ምክንያት ዉጤቱን በማያዉቀዉ ጦርነት ሲረግፍ፣ አረብ፣ አይሁድ ከቱርኮች አገዛዝ ነፃ ትወጣለሕ የሚለዉን የለንደን ፓሪሶችን ቃል አምኖ ቱርክና ጀርመኖችን እየገደለ ይሞት ነበር።

ዛሬ፥ ሶሪያዊዉ-ሶሪያዊዉን እየገደለ-ይሞታል።ሶሪያዊዉ እንዲተላለቅ የሪያድ፥ የዶሐ፥ የትሪፖሊ አረብ ያስታጥቃል።ቱርክ ያደራጃል።ይዝታልም።

በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት የቱርኩ አምባሳደር።ባለፈዉ ሳምንት።

ድሮ፥-በቱርክና በጀርመን ተባባሪዎቻቸዉ ላይ የየሐገሬዉን አረብ ያስዘመቱት የለንደንና የፓሪስ ሐያላን ፥ቱርኮች ከአራት መቶ አመታት በላይ ከገዙት ከመካከለኛዉ ምሥራቅ ተነቅለዉ እንደሚወጡ ጦርነቱ በተጀመረ በሁለተኛዉ ዓመት ግድም አዉቀዉት ነበር።ነፃ እንደሚወጣ ቃል የገበሉት አረብ ግን ከቱርኮች ሽንፈት በሕዋላ እንግዛሕ ቢሉት አፈሙዝ-ጎራዴዉን በነሱ ላይ እንደሚያዞርም ለንደን ፓሪሶች እርግጠኞች ነበሩ።

በተለይ ጥንት ፈረንዓኖች፥ ኋላ መሙሉኮች የፈለቁባት ግብፅ ከቱርክ አገዛዝ ከተላቀቀች የአያት-ቅድመ አያቶቼን ግዛት ልረከብ ብላ በብሪታንያና በፈረንሳይ ላይ ጦርነት ታዉጃለች የሚለዉ ግምት ለንደኖችን ሲበዛ አሳሳቦ ነበር።ለንደኖች የድላቸዉ ፅናት የሚረጋገጠዉ ግብፅን ሲቆጣጠሩ ብቻ እንደሆነ ሲያስታዉቁ፥ ፓሪስሶች ሶሪያ ላይ አነጣጠሩ።

የያኔዉ የፈረንሳይ እዉቅ ዲፕሎማት ዦርዥ ለጌ «ሜድትራኒያን መቆጣጠር የምንችለዉ ሶሪያን በኛ ተፅዕኖ ሥር ካደረግን ብቻ ነዉ» አሉ።መጋቢት 1916።በዚያዉ ዓመት ሁለቱ ሐያላን ቱርክን ሲያሸንፉ የሚፈልጉትን አካባቢ መቆጣጠር የሚያስችላቸዉን ዉል በሚስጥር ተፈራረሙ።

የምሥራቃዊ ሜድትራኒያን አጎራባች በተለይም የሳቫስቶፖል ወደብንና አካባቢዉን ለመቆጣጠር ቱርኮች እስኪሸነፉ አድፍጣ የምትጠብቀዉ ሩሲያ የፈረንሳዩ የዉጪ ዲፕሎማት ፍራንሷ ዦርዥ-ፒኮ እና የብሪታንያዊ አቻቸዉ ኮሎኔል ጌታ ማርክ ስይኬስ የፈረሙትን ዉል መቀበሏን አስታወቀች። ግንቦት 1916።

ስምምነቱ የዛሬዋን ሶሪያንና ሊባኖስን ለፈረንሳይ፥ ግብፅና መላዉን ፍልስጤም ለብሪታንያ፥ ሰቫስቶፖልና አካባቢዉን ለሩሲያ የሚሰጥ ነዉ።ከሒጃዝ ተነስቶ ቱርኮችን እየገፋ ወደ ሶሪያ የሚገሰግሰዉን የአረብ ጦር የሚመሩት ልዑል ፈይሰል ቢን ሁሴይን ዓሊ አል-ሐሽማይት ግን ሥለ ሥምምነቱ የሚያዉቁት-የነገራቸዉም አልነበረም።ፈይሰል ዘዉድ ለመድፋት፥ የሚመሩት ጦር ነፃ ለመዉጣት፥ በእሕል ተዋግተዉ የቱርኮችን ጦር ደምስሰዉ ደማስቆን ተቆጣጠሩ።ጥቅምት 1918።

ሶሪያ ከኦስማን ቱርክ ነፃ በመዉጣትዋ ለንደን፥ ፓሪስ፥ አረብም እኩል ቦረቁ።ፈይሰልም ነገሱ። ወዲያዉ ግን ብሪታንያና ፈረንሳይ በሚስጥር በተፈራረሙት ዉል መሠረት ጄኔራል ዦሴፍ ጎራዉድ የሚመሩት የፈረንሳይ ጦር የአረቦቹን ጦር ደምስሶ፥ ፌይሰልን ወደ ኢራቅ አሰድዶ ሶሪያን ለፓሪስ ቅኝ ገዢዎች አስረከበ።ሐምሌ 1920።


ዘንድሮ፥- ቱርኮች እንደ ብሪታንያና እንደ ፈረንሳይ ሁሉ ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራዉን ጎራ ተቀይጠዋል።ሳዑድ አረቢያዎች፥ ቀጠሮችና ሊቢያዎች ይከተላሉ።ሩሲያዎችና ቻይኖች በሌለኛዉ ጎራ ቆመዋል።እና ትናንት በርግጥ ዛሬ አይደለም።የሶሪያ መፃኤ ዕድል ግን ያዘም አልያዘ ልክ እንደ ድሮዉ ሶሪያዎች በሌሉበት ጂኒቫ ላይ ተወሰነ።

የተስማሙት፥ እኩል የወሰኑት ሐይላት ስምምነት-ዉሳኔያቸዉን ለየቅል መተርጎማቸዉ ነዉ-ግራዉ። የመጀመሪያዉን ጎራ የምትመራዉ ዩናይትድ ስቴትስ፥ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን እንዳሉት አሁንም ፕሬዝዳት በሽር አል አሰድ መወገድ አለባቸዉ ባይ ናቸዉ።

«አሰድ አሁንም ቢሆን መወገድ አለባቸዉ።እጃቸዉ በደም እንደተጨማለቀ ሁሉን ለማግባባት የሚጠብቀዉን ፈተና ሊያልፉ አችሉም።ኮፊ አናንም በመሠረቱ ይሕንኑ ሲሉ የሰማችኋቸዉ መሠለኝ።(የስምምነቱ) ፅሁፍም ሐገር የማስተዳደሩ ሙሉ ሐላፊነት፥ እሳቸዉን (አሰድን)ና ስርዓታቸዉን ሥልጣን ካለቀቁ ሥልጣናቸዉን መግፈፍ የሚችለዉ የሽግግር አካሉ መሆኑን በግልፅ አስቀምጦታል።»

የስምምነቱ ሰነድ ግን ፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድን በስም ጠቅሶ-ከሥልጣን ይወረዱ አላለም። የቻይናዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ያንግ ጂቺም በሶሪያ የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይቻልም ነዉ ያሉት።

«ለሶሪያ ፖለቲካዊ መፍትሔ የማፈላለጉ ዕቅድ መመራት ያለበት በሶሪያ ሕዝብ ነዉ።ዕቅዱ ሶሪያ ዉስጥ ባሉ በሚመለከታቸዉ ወገኖች በሙሉ ተቀባይነት ሊኖረዉ ይገባል።ማንም የዉጪ ሐይል ለሶሪያ ሕዝብ ሊወስንለት አይችልም።ቻይና በሶሪያ ላይ የዉጪ እቅድ መጫኑን ትቃወማለች።»

የሶሪያን እልቂት ፍጅት ለማስቆም የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት የሚጠይቀዉን እቅድ ያፀደቁት ሐያላት ዕቅዱን እንዳሻቸዉ እንደተረጎሙት ሁሉ የሶሪያ ተፋላሚዎችም እንደፈለጋቸዉ ተርጎመዉታል።ላለፈዉ አንድ-ዓመት ከመፈንቅ የሚዋጉት ሐይላት አንድ-ያደረጋቸዉ ነገር ካለም ግራ-አጋቢዉን እቅድ እኩል መቃወማቸዉ ነዉ።የደማስቆ መንግሥት የጂኒቫዉን ዐቅድ ስምምነት «ዋጋ ቢስ» ሲለዉ።የሶሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰኘዉ ተቃዋሚ ቡድን ቃል አቀባይ ደግሞ አሻሚ ብሎዉታል።

«ትናንት ጂኒቫ ዉስጥ ያየነዉ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሥለ ሶሪያ ካደረጋቸዉ በጣም መጥፎ ሥብሰባዎች ሁሉ መጥፎዉ ነዉ።የሥብሰባዉ ዋና ጭብጥ አሻሚ ነዉ።የዕቅዱ ዋና ጭብጥ አሻሚ ነዉ።ትናንት ያየነዉ ነገር ቢኖር አሻሚ ነገርን ብቻ ነዉ።»

ግብፅ ከሳዑዲ አረቢያ ከቀጠር ጎን በቀጥታ አልተሰለፈችም። ዛሬ ግን የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎችን ካይሮ ላይ ስብሰባ ጠርታለች።የሶሪያዎች ግን ሶሪያ ዉስጥ የታጠቁት እየተጋደሉ-ያልታጠቁትን እየገደሉ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሟቾችን ይቆጥራል።አስራ-አምስት ሺሕ አለ በቀደም።የሶሪያ እጣ ግን በሺ ዘመን ታሪኳ ግሪኮች ሜቂዶኒያ፥ ሮሞች ሮም፥ ዑመያዶች መካ፥ መምሉኮች ካይሮ፥ ቱርኮች ሶጉት፥ ወይም ቆስጠንጥኒያ፥ ብሪታንያና ፈረንሳዮች ለንደን-ፓሪስ እንደወሰኑላት ሁሉ ዘንድሮም ጂኒቫ፥ አንካራ ካይሮ እንደወሰኑላት ይቀጥል ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ለዛሬ ይብቃን።

Source News Feed: EMEA Picture Service ,Germany Picture Service Lebanese army soldiers take position in their armoured vehicle as gunmen are seen in the background at the Sunni Muslim Bab al-Tebbaneh neighbourhood in Tripoli, northern Lebanon, during clashes May 16, 2012. Heavy fighting rocked Lebanon's northern port of Tripoli for a fourth day on Wednesday, wounding at least six people in a city where sectarian tensions have been growing over the revolt in neighbouring Syria, security sources said. REUTERS/Omar Ibrahim (LEBANON - Tags: POLITICS CIVIL UNREST MILITARY)
ሶሪያ፦የመንግስት ጦርምስል Reuters
In this picture taken on Saturday, June 23, 2012, Syrian rebels run during clashes with Syrian government forces, at Saraqeb town, in the northern province of Idlib, Syria. Investigators say they have concluded that Syrian government troops could be behind the killing of more than 100 civilians in the village of Houla last month. The findings, which were presented to the U.N.'s top human rights body, could lay some of the groundwork for prosecuting alleged crimes against humanity or war crimes in Syria. (Foto:Fadi Zaidan/AP/dapd).
ሶሪያ፦አማጲያንምስል AP
U.S. Secretary of State Hillary Clinton and Kofi Annan, Joint Special Envoy of the United Nations and the Arab League for Syria, pose before the Action Group on Syria meeting at the United Nation's Headquarters in Geneva June 30, 2012. REUTERS/Haraz N. Ghanbari/Pool (SWITZERLAND - Tags: POLITICS)
ጉባኤተኞች፦አናንና ክሊንተንምስል Reuters
Joint Special Envoy of the United Nations and the Arab League for Syria Kofi Annan (C) speaks with Russia's Foreign Minister Sergei Lavrov (R) next to U.N. Secretary-General Ban Ki-moon at the start of the meeting of the Action Group on Syria at the United Nations European headquarters in Geneva, June 30, 2012. REUTERS/Denis Balibouse (SWITZERLAND - Tags: POLITICS CIVIL UNREST TPX IMAGES OF THE DAY)
ጉባኤተኞች በከፊልምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ