1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶስት ሳምንቱ የሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት

ሰኞ፣ ሐምሌ 25 1997

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት በመባል ቃለ መሃላ የፈፀሙት የሱዳን መንግስትን በተቃዋሚነት ሲታገል የኖረዉ የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጪ ንቅናቄ ቡድን መሪ ዶክተር ጆን ጋራንግ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

https://p.dw.com/p/E0jf

የዑጋንዳ ባለስልጣናት እንደገለፁት ጋራንግ ህይወታቸዉ ያለፈዉ በሄሊኮፕተር አደጋ ሲሆን ከሳቸዉ ጋር አብረዉ የተሳፈሩና የሄሊኮፕተሯ ሰራተኞችም አልተረፉም።
የአደጋዉ መንስኤም ገና ያልታወቀና በመጣራት ላይ የሚገኝ መሆኑ ነዉ የተገለፀዉ። በመንግስት በኩልም በደቡብ ሱዳን አካባቢ በሚገኘዉ መጥፎ የአየር ሁኔታ ነዉ የሚለዉ ግምትም ተሰንዝሯል።
የ60ዓመቱ ጆን ጋራንግ በአፍሪካ ረዥም ዘመን ያስቆጠረዉንና በበርካቶች መስዋዕትነት በቅርብ ጊዜ ወደሰላም የቀረበዉን የደቡብ ሱዳን ነፃዉጪ ንቅናቄ SPLM ትግል መሪ በመሆን ይታወቃሉ።
የታገሉለት ሁሉ ለፍሬ ሊበቃ ከአገሪቱ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ዉል ባለፈዉ ጥር ወር ተፈራርመዉ በምክትል ፕሬዝደንትነት ሊሰየሙ የዛሬ ሶስት ሳምንት በይፋ ቃለ መሃላ ፈፀሙ።
ብዙዎች ከእንግዲህ ሱዳን በዳርፉር ያለዉ ችግሯ ሊወገድ፤ ወደሰላምና ልማት ጎዳና ልትገባ ነዉ የሚል ተስፋ ጣሉ።
የሱዳኑ መሪ በሺርና ጋራንግም ወዳለሙት የሚያደርሳቸዉን አዲስ መንግስት በጋራ ለመመስረት ስምንት ቀናት ብቻ ቀርቷቸዉ ነበር።
ጋራንግ የፈረሙለትን የሰላም ስምምነት ጅምር እንጂ ፍፃሜ ለማየት ሳይታደሉ ትናንት ከዑጋንዳ ወደደቡብ ሱዳን ለመሄድ የተሳፈሩባት ሄሊኮፕተር ኪዴፓ በተባለዉ የጠረፍ አካባቢ መሰወሯ ተነገረ።
በመጀመሪያ የሱዳን መንግስት ቴሌቪዥን ጋራንግ በሰላም መሬት ላይ ማረፋቸዉን ገለፀ ብዙም ሳይቆይ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አብደል ባሲጥ ሳብዳራት ጋራንግ የተሳፈሩባት ሄሊኮፕተር ከራዳር መሰወራን አስታወቁ።
ከዚያ በፊት በዘርፉ የሚገኙ ባለስልጣናት ጋራንግ ከዑጋንዳ የሚመጡባት ሄሊኮፕተር ግንኙነት መቋረጡን አስታወቀዉ ነበር።
ዛሬ ንጋት ላይ የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣናት አዲሱ የሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት በሄሊኮፕተር አደጋ መሞታቸዉን አረጋገጡ።
ከዚያም ዛሬ ረፋዱ ላይ የሱዳኑ ፕሬዝደንት ዖማር አልበሺር በቴሌቪዥን ቀርበዉ ባደረጉት ንግግር ከዑጋንዳዉ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ተገናኝተዉ ወደአገራቸዉ በመመለስ ላይ ሳሉ ጆን ጋራንግ በአደጋ መሞታቸዉን በይፋ አስታወቁ።
ሆኖም በሺርም ሆኑ ጋራንግ ሲመሩት የኖሩት SPLM በሱዳን የተጀመረዉን የሰላም ሂደት እንደሚገፉበት ተስፋ ሰጥተዋል።
በደቡብ ሱዳን የረድኤት ጉዳይ አስተባባሪ ሩዲ ሙለር ለሮይተር እንደገለፁት ከሌሊቱ በዘጠኝ ሰዓት በተካሄደ ስብሰባ ላይ ነዉ የሌክ አዉራጃ ገዢ ፓጋን አሙም ዶክረት ጆን ጋራንግ በአደጋ መሞታቸዉን የነገሯቸዉ።
አሙም ስለጉዳዩ የሚያዉቁት ዝርዝር መረጃ ባይኖርም የጋራንግ ቡድን የSPLM ከፍተኛ አባል ናቸዉ።
የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደሚሉት ጉዳት የደረሰባት ጋራንግ የተጓዙባት ሄሊኮፕተር በዑጋንዳ ጠረፍ አካባቢ በሚገኘዉ የደቡብ ሱዳን ምድር ላይ በአካባቢዉ ሰዎች ነዉ የተገኘችዉ።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የፈጀዉን የደቡብ ሱዳን ትግል የመሩት ጋራንግ ከሙሴቪኒ ጋር የነበራቸዉን ዉይይት ጨርሰዉ ቅዳሜ ዕለት ነበር ዑጋንዳን የለቀቁት ይላሉ እኝሁ ምንጭ።
ዑጋንዳም በበኩሏ ከሄሊኮፕተሯ ጋር የነረዉ ግንኙነት በመቋረጡ የጦር ኃይሏ ፍለጋ መጀመሩን ትነገራለች።
ለዑጋንዳ ጦር የቀረቡ ምንጮችም ጋራንግን ጨምሮ በሄሊኮፕተሯ ዉስጥ የነበሩት ሁሉ ህይወታቸዉ አልፏል ቢልም በወቅቱ SPLM ሄሊኮፕተሯ ሳትገኝ ይህን ማረጋገጥ አንችልም ብለዉ ነበር።
ሙሴቪኒ በመኩላቸዉ ዛሬ ጠዋት በሰጡት መግለጫ ቅዳሜ ዕለት የተሰናበቷቸዉ ጋራንግን ያሳፈረችዉ ሄሊኮፕተር መድረስ ከሚገባት ሰዓት 24ሰዓታት በማለፋቸዉ ምንም እንኳን ፍለጋቸዉ የተሳካ ባይሆንም የህዝቡን ስጋት እንደሚጋሩ ገልፀዋል።
ፕሬዝደንት ባሺርና ሁለተኛዉ ምክትል ፕሬዝደንታቸዉ አሊ ኦማር ጠሃ አስቸኳይ ስብሰባ ትናንት አካሂደዋል። ካቢኔዉም ዛሬ ከሰዓት በፊት ስብሰባ አካሂዷል።
ባሺር ዛሬ ለህዝባቸዉም ሆነ ለዓለም ለማሳወቅ እንደሞከሩት የተጀመረዉ የሰላም ስምምነት ቀጣይነት እንደሚኖረዉ አረጋግጠዋል።
በSPLM አባላት ወንድሞቻችንም ያለን እምነት የጠነከረነዉ ያሉት በሺር እግዚአብሄር በፈቀደ የጋራንግን ምትክ ባስቸኳይ መርጠዉ ያሳዉቁናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ነዉ ያሉት።
በደቡብ ሱዳን በተፈጠረዉ የእርስ በርስ ጦርነት ከጋራንግ ጋር ለ16 ዓመታት በጠላትነት የኖሩት ባሽር ላለፉት ሶስት ሳምንታት ምክትላቸዉ ለነበሩት ለጆን ጋራንግ የሶስት ቀን ብሄራዊ ሃዘን አዉጀዋል።
ዘግየት ብሎ አጃንስ ፍራንስሬስ እንደዘገበዉ ደግሞ አደጋዉ የደረሰዉ በአካባቢዉ ባለዉ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ነዉ ቢባልም ህዝቡ ግን የመንግስት እጅ ይኖርበታል የሚል ጥርጣሬ አድሮበታል።
ይህን መሰል አደጋ በዚሁ አካባቢ ባለፈዉ ሰኞ የደርሶ ሶስት ሃላፊዎችን ጨምሮ የጦር ኃይሉ አባላት የሞቱ ሲሆን የዛሬ አራት ዓመት ሚያዝያ ወር መጀመሪያ አካባቢ ተመሳሳይ አደጋ ደርሶ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩን ጨምሮ 14 ባለስልጣናት ህይወታቸዉ አልፏል።
በተጨማሪም የዛሬ ሰባት ዓመት የካቲት ወር ላይ የቀድሞ የሱዳን ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ዙባየር ሞሃመድ ሳላህ የተሳፈሩበት አንቶኖቭ ሲያኮበኩብ ተከስክሶ ከሌሎች 26 ሰዎች ጋር መሞታቸዉ ይታወሳል።