1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሻከረው የግብጽና ሱዳን ግንኙነት መባባሱ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 2010

በግብጽ እና ሱዳን መካከል የተፈጠርው ውዝግብ እየከረረ መምጣቱ ተነገረ። የግብጽ መገናኛ ብዙሃን፤ ሱዳን የገንዘብ ለማግኘት ስትል ከቱርክ እና ከቀጠር ጋር የጀመረችው ግንኙነት በእሳት የመጫወት ያህል ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

https://p.dw.com/p/2qBst
Ägypten Präsident al-Sisi trifft al-Baschir
ምስል Reuters/The Egyptian Presidency

የግብጽና ሱዳን ግንኙነት እየተካረረ ነው

የሱዳን እና የቱርክ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ፤ የሁለቱ ሐገራት መሪዎች አንዱ የሌላዉን ርዕሠ-ከተማ መጎብኘታቸዉ እየተደጋጋመ ነዉ። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኢየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና መዲና ናት ሲሉ የሰጡትን ዕውቅና በተቃወመዉ የሙስሊም ሐገራት ጉባኤ የተካፈሉት የሱዳኑ ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽር በአንካራ ቆይታቸዉ ከቱርኩ አቻቸዉ ሬሴፕ ጠይብ ኤርዶኻን ጋር ተወያይተዋል።

በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ ደግሚ የቱርኩ ፕሬዝደንት ካርቱምን ጎብኝተዋል። ይሕ የጉብኝት ልዉዉጥ እና በየጉብኝቱ ካርቱምና አንካራ ያደረጉት ሥምምነት አልሲሲ ለሚመሩት ለግብፅ መንግስት ትልቅ ራስምታት ነዉ-የሆነዉ። 

የግብፅ መንግስት እስካሁን ሱዳን ከቱርክም ሆነ ከቀጠር  ጋር እያጠናከረች በመጣችው ግንኙነት ዙሪያ ይፋዊ መግለጫ አልሰጠም። የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ግን ሱዳን ለገንዘብ  ስትል  በእሳት መጫወት ጀምራለች ሲሉ የሚሰነዝሩት ነቀፋ የካይሮ መንግስት አቋም ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይገምታሉ።

በአሁኑ ወቅት ሱዳን ከቱርክ እና ቀጠር ጋር የጀመረችው ወዳጅነት እስላማዊ የወንድማማቾች ህብረት የተባለውን ማሕበር አባላት ለማጥፋት ቆርጨ ተነስቻለሁ ለሚለው የግብጽ መንግስት ትልቅ  ሥጋት ሆኖበታል።

Äthiopien Grand Renaissance Staudamm
ምስል Reuters/T. Negeri

የሱዳን እና የግብጽ ዉዝግብ  አሁን የተፈጠረ አይደለም አካባቢውም በውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት ተመሰቃቅሏል የሚሉት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ የሱዳን መንግስት በሳዑዲ ከሚመራው ጥምር ሃይል ጋር ከዚህ በፊትም የፈጠረው ግንኙነት ስልታዊ መሆኑ የሚገለጸው የግንኙነቱ ዓላማ ከገንዘብ ልገሳ እና ኢንቨስትመንት ባሻገር በዩናይትድስቴትስ የተጣለውንም ማዕቀብ ለማስነሳት እና የስልጣን ሃይልንም ከማስጠበቅ አኳያ የታለመ በመሆኑ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ በምትገነባው ታላቁ የአባይ ግድብ ምክንያት የውሃ ፍሰቱ መጥን ይቀንስብኛል የሚል ስጋት ያደረባት ከሱዳን ድጋፍ አለማግኘቷም በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረውን ግንኙነት እንዳሻከረው ይነገራል። ግብፅ በሱዳን የዳርፉር አማጽያንን በግልጽ ከመደገፍ ጀምሮ ኢጋድ  የጀመረውን የሰላም ጥረት ለማኮላሸት ከዩጋንዳ እና ከሌሎችም ሃገራት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ክፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኗንም ፕሮፌሰር መድሃኔ ይገልጻሉ።

አሁን በሁለቱ ሃገራት እና በመካከለኛው ምስራቅ በሃገራት እየከረረ የመጣው ውዝግብ ዩናይትድስቴስ በእስራኤል ላይ ባላት ፖለቲካዊ አቋም ጭምር መሆኑንም ጠቁመዋል። ይኽው ፍጥጫ እና ውዝግብ መቋጫ ካላገኘ በአባይ ተፋሰስ ስምምነትም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እና የተጓዳኝ ጦርነት እና ግጭቶችንም ሊያባብስ እንደሚችል ፕሮፌሰር መድሃኔ ያስረዳሉ።

ቱርክ አሁን ከሱዳን ጋር የጀመረችውን ግንኙነት አስመልክቶ የፖለቲካ ተንታኞች እና የመገናኛ ብዙሃን በሱዳን የቀይ ባህር ዳርቻ የጦር ሰፈር የመገንባት ዕቅድ አላት የሚለውን ጥርጣሬ የአንካራ መንግስት ማስተባበሉ ይታወሳል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ