1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽብር ፀረ-ሽብር ዘመቻ

ሰኞ፣ ጥር 11 2007

ኩሊባሊ የኮሸር የገበያ አዳራሽ ሺያጭ-ሸማቾችን አግቶ ጥያቄዉ ካልተሟላለት ታጋቾቹን እንደሚገድል ሲዝት፤ ሲፎክር፤ ባቲሌይ እቅርቡ ያሉትን ገበያተኞች ይዞ-ከምድር በታች ወደሚገኘዉ ሸቀጥ ማከማቻ ክፍል ወረደ።

https://p.dw.com/p/1EMsK
ምስል David Osipov

ፓሪስን ያሸበሩ ሙስሊም ፅንፈኞች የገደሏቸዉን ፈረንሳዉያንን፤ በመቅበር መዘከር፤ ገዳዮቹን በማዉገዝ፤ ተባባሪዎቻቸዉን በማደን፤ መበቀል ዘመቻ ለተጠመደዉ ዓለም የዚያ ወጣት ማንነት፤የምግባሩ እንዴትነት ብዙም ከቁብ የገባ አይደለም።የዓለም ታላላቅ መሪዎችምፓሪስ ላይ ባንድ መታደማቸዉ አስተንትኖ ሳያበቃ የብዙ መሪዎችልዩነት፤የገሚሶቹ ዉዝግብ፤የጥቂቶቹ ስድድብ ይናኝገባ።ከእየሩሳሌም እስከ ካርቱም ባደባባይ ሠልፍ ሲጥለቀለቁ፤ ከከካራቺ እስከ ኒያሚ በግጭት ግድያ ቃጠሎ ሲናጡ ቤልጂግ፤ፈረንሳይና ጀርመን ላይ ተጠርጣሪ አሸባሪዎች መግደል፤መታሰራቸዉን ሰማን።ያየን የሰማነዉን እየጠቃቀስን፤ አስራ-አራተኛ ዓመቱን የያዘዉን የዓለም አቀፍ ፀረ-ሽብር ዘመቻን ዉጤት-ዉድቀት ባጭሩ እንቃኛለን።አብራችሁን ቆዩ።

ብዙ ጊዜ እንደሚባለዉ፤ በተለይ በምዕራቡ ዓለም እንደሚታሰበዉ የዘር ሐረግ፤ የቆዳ ቀለም፤ እና የሐይማኖት መመሳሰል ወይም አንድነት የሰዎች አስተሳሰብ ገዢ ማዕከል ቢሆን ኖሮ የማሊያዊዉ ስደተኛ ምግባር ከሴናኔጋላዊዉ የስደተኛ ልጅ ድርጊት ጋር በተመሳሰለ ነበር።ግን ተቃራነ።የሴኔጋላዊ የስደኛ ልጅ አሜዲያ ኩሊባሊ ጥቁር፤ ሰላሳዎቹን የዕድሜ ዘመን የረገጠ፤ወጣት እና ፤ሙስሊም ፈረንሳዊ ነበር።

Malian Lassana Bathily
ምስል Guillot/AFP/Getty Images

ማሊያዊዉ ወጣት ላሳና ባቲሌይም እንደ ኩሉ ባሊ ሁሉ ጥቁር፤ የሃያ-አራት ዓመት ወጣት፤ሙስሊም ግን ፈረንሳዊ ለመሆን የሚጓጓ ፈረንሳይ የሚኖር ስደተኛ ነዉ።ኩሊባሊ ፓሪስን ሊያሸብር፤ አይሁዶችን ሊያግት-ሊግድል፤ ባቲሌይ እንደወትሮዉ ለዕለት ጉርሱ፤ለወር ኪራዩ፤ላመት ልብሱ ሊሸቅል ከአይሁዱ የምግብ ሸቀጣሸቀጥ መደብር ተገናኙ።ፓሪስ።

ኩሊባሊ የኮሸር የገበያ አዳራሽ ሺያጭ-ሸማቾችን አግቶ ጥያቄዉ ካልተሟላለት ታጋቾቹን እንደሚገድል ሲዝት፤ ሲፎክር፤ ባቲሌይ እቅርቡ ያሉትን ገበያተኞች ይዞ-ከምድር በታች ወደሚገኘዉ ሸቀጥ ማከማቻ ክፍል ወረደ።

«ወደ ማቀዝቀዣዉ ክፍል ሮጥኩና ማቀዝቀዣዉን ከፈትኩት።አብረዉኝ ብዙ ሰዎች ነበሩ።መብራቱን አጠፋሁት።እሱ (ኩሊባሊ) ወደላይኛዉ ክፍል እንደመጣ ጠየቀን።ቢያገኘን ኖሮ ይገድለን ነበር።አብሩኝ ያሉትን ጠየቅኋቸዉ „ወደ ላይ መዉጣት ትፈልጋላችሁ፤ወይስ እዚሁ ትቆያላችሁ ብዬ?“አብረዉኝ ከነበሩት የሁለት ዓመት ልጅም ነበር።ከዚያ ሁሉንም ማቀዝቀዣዉ ዉስጥ አስገብቼ በሩን ዘጋሁባቸዉና እኔ ወደላይ እዉጣለሁ እናንተ ግን ድምፅ እንዳታሰሙ ብያቸዉ ወጣሁ።አካባቢዉን ስቃኝ አጋቹን አላየሁትም።ወዲያዉ እየሮጥኩ ወደ ዉጪ ወጣሁ።ፖሊሶች አገኘሁ።በኋላ ሰዎቹ ሲወጡ በጣም እናመሰግናለን አሉኝ።ምንም አይደለም አልኳቸዉ ሕይወት እንዲሕ ነዉ»

የዓለም ትላልቅ መገኛ ዘዴዎች የኩሊባሊን ጨካኝ፤ አሸባሪ፤ ወንጀለኛ ሙስሊም ፅንፈኝነትን የተናገሩለትን ያክል፤ የባቲሌይን ድፍረት፤ ሕይወቱን ለሌሎች አሳልፎ ለመስጠት የመቁረጡን ጀግንነት ብዙም አላወሱትም።የፈረንሳይ መንግሥትም ዜጎቹን ላዳነዉ ወጣት የሚጓጓለትን የፈረንሳይ ዜግነት ከመፍቀድ ባለፍ ሌሎች ባቲሌዎችን ለመፍጠር የሚረዳዉ ሽልማት ቢያንስ እስካሁን አልሰጠዉም።«ሕይወት እንደዚሕ ናት» ብሏል እሱም።

ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን ደግሞ የታቅርኖዉን ግጥምጥሞሽ የአሸባሪ-ሽብርን ብያኔ ዉስብስብነት ጠቋሚ ይሉታል።አሸባሪዎች የገደሏቸዉን ፈረንሳዉያን ለማሰብ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትርም፤ የቱርኩ አቻቸዉም የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንትም ፓሪስ ላይ እኩል ታድመዉ፤ ሽብሩንም እኩል አዉግዘዉ ነበር።የፓሪሱ ሽብር ሽብርና መዘዙ ተንትኖ ሳያበቃ ግን የቱርክና የእስራኤል ባለሥልጣናት ይወነጃጀሉ፤ ይሰዳደቡ ገቡ።

Niger Anti Charlie Hebdo Protest Islam 17.01.2015
ምስል Reuters/T.Djibo

ከ65 ዘመናት በላይ ያስቆጠረዉ የፍልስጤም እስራኤሎች ጠብ ደግሞ የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እና የእስራኤል ባለሥልጣናት ዉዝግብን እንደተላበሰ ሳምንቱ ሌላ ሳምንት ተካ።የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት እና የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርም በፓሪሱ የድጋፍ ሠልፍ ላይ አኩል ተካፋዮች ነበሩ።

የኪየቭና የሩሲያ ደጋፊዎች ምሥራቃዊ ዩክሬን ዉስጥ ለመገዳደል የሁለቱ ሐገራት ባለሥልጣናት ኪየቭና እና ሞስኮ እስኪ ደርሱ አልጠበቁም።ዩናይትድ ስቴትስ ለፓሪሱ ሐዘን ባለሥልጣንዋን አለመላክዋ ፓሪስን ጨምሮ የምዕራብ አዉሮጳ ተከታዮችዋን ቅር ማሰኘቱ ዛሬም ጭምር እየተተነተነ ነዉ።

ከፓሪሱ ጥቃት ጀምሮ በየሐገራቸዉ በተጠርጣሪ አሸባሪዎች ላይ ዘመቻ የከፈቱት የቤልጂግ፤ የፈረንሳይና የጀርመን ፀጥታ አስከባሪዎች ከሐያ በላይ ተጠርጣሪዎችን ማሰራቸዉን አስታዉቀዋል።በተለይ የቤልጂግ ፅጥታ አስከባሪዎች «ተኩስ ሊከፍቱ ነበር» ያሏቸዉን ሁለት ተጠርጣሪዎችን ገድለዋል።

የሽብር ፀረ-ሽብሩ ዘመቻ አፍቃኒስታን፤ኢራቅ፤ ሶሪያ፤ ፓኪስታን፤ የመን፤ ናይጄሪያ፤ማሊ፤ሶማሊያ በዚሕ ሰሞን የደረሰበት ደረጃ ለዓለም ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች ለትልቅ ርዕስነት አልበቃም።የሽብር፤ ፀረ-ሽብር ግድያ፤ አፀፋ ግድያዉ ግን በርግጥ አላባራም።አስራ-አራት ዓመቱ።ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን ወጥንቅጡ የወጣ ይሉታል።

ዓለም «አኔም ሻርሊ ኤብዶ» ነኝ ብሎ ሳያበቃ፤ ምፀተኛዉ መፅሔት ለአሸባሪዎች ጥቃት ያጋለጠዉን ነብዩ መሐመድን የሚያንቋሽሽ ካርቱኑን መልሶ አሳተመ።የመጨረሻዉ ሕትመት በብዛት መሸጡ ለካርቱኑ አታሚዎች ታላቅ ድል፤ ጠርቀም ያለ ገንዘብ ያስገኘ ነበር።ከካራቺ እስከ አልጀርስ፤ ከኢየሩሳሌም እስከ ካርቱም፤ ከቴሕራን እስከ አማን ለሚገኙ ሙስሊሞች ግን ንቀትና ስድብና ጠብ አጫሪነት ነዉ።ለኒጀር ደግሞ የግጭት፤ግድያ፤ቃጠሎ ሰበብ ምክንያት።

Niger Proteste gegen Mohammed Karikaturen in Charlie Hebdo 16.1.2015
ምስል STR/AFP/Getty Images

ለኒጀር ፕሬዝዳንት መሐመዱ ኢሱፉ ለተገደሉት ፈረንሳዉያን ፓሪስ ድረስ ሔደዉ ሐዘናቸዉን መግለፅ ከፖለቲከኝነትም በላይ ሐገራቸዉ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ጋር ያላትን ወዳጅነት የመግለጥ ግዴታም ጭምር ነዉ።ኢሱፉ የሴኔጋል፤የጋቦን፤የማሊ፤እና የሌሎችም የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ የነበሩ የሁለት የአፍሪቃ ሐገራት መሪዎች ካደረጉት ዉጪ ያደረጉት አልነበረም።

ኢሱፉ ኒያሚ ሲገቡ ግን «ለቅሶ የደረሰላቸዉ» የሻርሊ ኤብዶ ባልደረቦች እስልምናን የሚያንቋሽሸዉን ካርቱን በድጋሚ ማሳተማቸዉ ያስቆጣዉ ሕዝብ ኒጀር የሚኖሩ ፈረንሳዮችን እንዳይገድል፤የፈረንሳይ ተቋማትን እና አብያተ ክርስቲያናትን እንዳያቃጠል ማስጠበቅ ሆነ ሥራቸዉ።ዓለም አቀፉ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ሰፊ፤በረሐማይቱን፤ ደሐ ሐገር ዳግም ያጋድል፤ያነድ፤ ያቃጥላት ገባ።.........ችግሩ እንደቀጠለ ነዉ። ነጋሽ መሐመድ ነኝ እኛ ለዛሬ ይብቃን።

ነጋሽ መሐመድ

ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ