1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ መገደል

ሐሙስ፣ ጥቅምት 9 2004

ትልቅ ሆነዉ ሌላ ትልቅ እንዳሰቡ እንደ ትንሽ ወታደር ሲዋጉ ከተወለዱባት ትንሽ ከተማ ተገደሉ። ቃላቸዉን ግን አከበሩ።ሙዓመር መሐመድ አቡሚኒያር አል-ቃዛፊ።አለቀ ደቀቀ።

https://p.dw.com/p/Rs2O
ምስል dapd

20 10 11

የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ዛሬ ተገደሉ።የሊቢያ የሽግግር ምክር ቤት ባለሥልጣና እንዳስታወቁት ቃዛፊ የተገደሉት ትዉልድ ከተማቸዉ ሲርት ዉስጥ ወይም አካባቢዉ በተደረገ የቱኩስ ልዉዉጥ ነዉ።የቃዛፊ ታማኝ ጦር አዛዥ ሐኪም ቤንሐጂም ተገድለዋል።የቀድሞዎቹ አማፂያን የኮሎኔል ቃዛፊ ታማኞች የመጨረሻ ይዞታ የነበረችዉን ሲርት መቆጣጠራቸዉንም አስታዉቀዋል።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

እንደ አርብቶ-አደር ደሐ ልጅ ግመል እየጠበቁ-በረሐ እንዳቋረጡ አደጉ።እንደ ቆራጥ ወታደር ዙፋናዊ ሥርዓትን አስወግደዉ ገና በሃያ ሰባት አመታቸዉ ቤተ-መንግሥት ተቆጣጠሩ።እንደ አብዮተኛ ልዩ መርሕ መቀመሩ።

«ሰወስተኛዉን ሁለንተናዊ ትወራ ቀምረን በአረንጓዴዉ መፅሐፍ አሥፍረናል።የጁሙሕሪያ ሥንፀ ሐሳብ ሕዝባዊት ሐገር ማለት ብቻ አይደለም፥ የሰፊዉ ሕዝብ ሐገር ማለት እንጂ።ይሕ ነዉ-የኛ ግኝት።በዚሕ ፅንሰ ሐሳብ መሠረት መንግሥት፥ ምርጫ ወይም ፓርቲ የሌላበት ሐገር መመሥረት ነዉ።ሕዝቡ ወንድም ሴትም በእኩልነት የሥልጣን ባለቤቶች ናቸዉ።»

የትሪፖሊን ቤተ-መንግሥት ግን ለአርባ ሁለት ዘመን ከሰቸዉ ሌላ-የኖረ-የተቀማጠለ ያዘዘ-የናዘዘበት የለም።በገማል አብድናስር እርምጃ-አስተምሕሮት ተነሳስተዉ ሥልጣን የያዙት፥ አብዮታዊዉ መሪ እንደ ናስር ዓረብን አንድ ለማድረግ ሞክረዉ ነበር።ግን ከሌሎች የአረብ ሐገራት ጋር እንደተላተሙ መሸባቸዉ።

እርግጥ ነዉ-የፍልስጤሞችን የነፃነት ትግል፥ የደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮችን የእኩልነት ፍልሚያ ረድተዋል።የዚያኑ ያክል የሰሜን አየርላንድን ጦር ደግፈዋል።ከሌሎች የምዕራባዉያን ሐገራት ጠላቶች ጋርም አብረዋል።ምዕራቡን አሸብረዋል ወይም የሚያሸብሩ ሐይላትን ደግፈዋልም።የማይጋፉትን ሐይል-መጋፈጣቸዉ የዛሬ ፍፃፍሜያቸዉ ጥንስስ ነበር።ዘንድሮ በርግጥ ጨለባቸዉ።ግን አልተረዱትም ወይም መቀበል አልፈለጉም ከጥቂት ወራት በፊት።

«ይወዱኛል።ሕዝቦቼ በሙሉ ይወዱኛል።ለኔ ይሞታሉ።»

የሞቱላቸዉ በርግጥ አልጠፉ።አብዛኛ ሕዝባቸዉ ግን እሳቸዉ ሲመሽባቸዉ ሲመቸዉ በይፋ ሲያቅተዉ በድብቅ ከዛሬ ገደዮቻቸዉ ጎን ከቆመ ዉሎ አድሯል።ቤንጋዚ ላይ ያደሙት ጠላቶቻቸዉ ከምድር ፥ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ጦር ካየር ታማኞቻቸዉን ሲያዋክቧቸዉ እንደ ብዙዎቹ አምባገነኖች ሐገር ሕዝብ ጥለዉ «የመኮብለያቸዉ ጊዜ» ተቃረበ አሰኝቶ ነበር።

እንዲያዉም አንዳድ የምዕራብ ሐገራት ባለሥልጣናት ሰዉዬ ወደ ቬኑዚዌላ ኮበለሉ እስከማለት ደርሰዉ ነበር።ግምቱ-ሐሰት፥ መግለጫዉ ዉሸት ነበር።እና ሰዉዬዉም እስከ መጨረሻዉ እፋለማለሁ አሉ።

ይሕን ቃል ኮሎኔል መንግሥቱ ሐይለ ማርያም ካንዴ በላይ ብለዉት ነበር።በመጨረሻዉ ሰዓት ሐራሪ ተገኙ።ሳዳም ሁሴን ብዙ ጊዜ ብለዉት ነበር።ከጉርጓድ ተመዘቁ።እንደ ደሐ ቆለኛ ልጅ በረሐ፥ እንደ ወታደር ምሽግ፥ እንደ መሪ ቤተ-መንግሥት የኖሩት ቃዛፊ-ምኞታቸዉ የአፍሪቃ ንጉሰ-ነገስትነትን ዘዉድ መጫን ነበር።

ትልቅ ሆነዉ ሌላ ትልቅ እንዳሰቡ እንደ ትንሽ ወታደር ሲዋጉ ከተወለዱባት ትንሽ ከተማ ተገደሉ። ቃላቸዉን ግን አከበሩ።ሙዓመር መሐመድ አቡሚኒያር አል-ቃዛፊ።አለቀ ደቀቀ።ስልሳ-ዘጠኝ አመታቸዉ ነበር።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ