1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀድሞዉ የእስራኤል ፕሬዝደንት ሞት

ረቡዕ፣ መስከረም 18 2009

የእስራኤል ሕዝብ በቀድሞ ፕሬዝደንቱ በሺሞን ፔሬስ ሞት የተሰማዉ ሐዘን ሲገልፅ ነዉ የዋለዉ። ከአንድ ሳምንት በፊት ጭንቅላታቸዉ ዉስጥ ደም በመፍሰሱ በሕክምና ሲረዱ የቆዩት ፔሬስ ትናንት ለዛሬ አጥቢያ ነዉ ያረፉት።

https://p.dw.com/p/2Qhyf
Israel Schimon Peres
ምስል Reuters/File Photo/A. Cohen

 

93 ዓመታቸዉ ነበር። የፔሬስ ልጅ ቻሚ ፔርስ የአባታቸዉን ሞት ሲያዉጁ ዛሬ እንዳሉት፤ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ እስራኤል እንደ ሐገር ከመመሥረቷ አስቀድሞ የአይሁዶች ፍላጎትና ጥያቄ እንዲሳካ ዕድሜ ልካቸዉን የታገሉ ፖለቲከኛ ናቸዉ።«አባቴ ከእስራኤል መሥራች አባቶች አንዱ ነበር። የእስራኤል መንግሥት ከመመሥረቱ በፊት ጀምሮ ለሕዝቡ ሲታገል ፤ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላም እስከ መጨረሻዉ ዕለት ድረስ ሲያገለግል ነበር። ሰባ ዓመታት ባስቆጠረ አገልግሎቱ የሐገሪቱ ዘጠነኛ ፕሬዝደንት፤ ጠቅላይ ሚንስትር፤ መከላከያ ሚንስትር እና በሌሎችም የኃላፊነት ሥፍራዎች ሐገሩን በታማኝነት አገልግሏል። አባቴ፤«የአንተ ትልቅነት እንደቆምክለት ዓለማ ትልቅነት የሚወሰን ነዉ» ይል ነበር። እስከ መጨረሻዉ እስትንፋሱ ድረስ የሚያምንበትን እና የሚያፈቅረዉን የእስራኤልን ሕዝብ ከማገልገል ሌላ፤ ሌላ ፍላጎት አልነበረዉም።»

Israel 2013 - Benjamin Netanjahu & Schimon Peres in Jerusalem
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Hollander

የእስራኤል ሕዝብ ዛሬ ዉሎዉን የወትሮ እንቅስቃሴዉን አቋርጦ ወይም ቀንሶ በአንጋፋዉ ፖለቲከኛዉ ሞት የተሰማዉን ሐዘን በተለያየ መንገድ እየገለጠ ነዉ።

የእስራኤሉ የረጅም ዘመን ፖለቲከኛ ሞት ለተለያዩ ሐገራት መሪዎች፤ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ አዋቂዎችም አሳዘኝ አጋጣሚ ነዉ የሆነዉ። ፔሬስ በተለይ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1990ዎቹ ጀምሮ ያራምዱት የነበረዉ የሁለት መንግሥታት መርሕ ልዩ መታወቂያቸዉ፤ በምዕራባዉያን ፖለቲከኞች ዘንድ የሚደነቁበት ምክንያት ሆኗል። ከዩናይትድ ስቴትስሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እስከ ቀድሞዉ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን፤ ከፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድ እስከ ቀድሞዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ያሉ የዓለም መሪዎችና ፖለቲከኞች የፔሬስን መርሕ እያነሱ አወድሰዋል። ፔሬስ ባንድ ወቅት እንዲሕ ብለዉ ነበር።«የሁለት መንግሥታት ፤ ማለት የእስራኤልና የፍልስጤም መንግሥታት መፍትሔ ካልተገኘ ወደነበርንበት አሐዳዊ መንግሥትነት ነዉ የምንመለሰዉ። (ሥለዚሕ) እስራኤል አይሁዳዊት፤ ዴሞክራሲያዊት መንግሥት መሆንዋን ለማስመስከር ጠንካራ ዉሳኔ ማሳለፍ አለብን።»

Israel Sonya Peres & Schimon Peres
ምስል picture-alliance/dpa/H. Chanania

ይኽ መርሐቸዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በነበሩበት እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር በ1994 የዓለምን የሰላም ሽልማት ኖቤልን ከቀድሞዉ የሐገራቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር ይትሳቅ ራቢንና ከቀድሞዉ የፍልስጤም መሪ ያሲር አረፋት ጋር አሸልሟቸዋል። እስካሁን ድረስም ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎላቸዋል። መርሐቸዉ ግን እስካሁንም ገቢራዊ አልሆነም። ዓርብ ይቀበራሉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ