1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቁስ አካል ምንጭ-«ሂግስ ቦሰን»

ረቡዕ፣ ሰኔ 27 2004

የፍጥረተ-ዓለም ምንጭ የሚሰኘው ፣የቁስ አካል ኢምንት ቅንጣት፣ የ«ሂግስ ቅንጣት» ፤«የእግዚአብሔርም ቅንጣት» የሚሉትም አሉ--እውን ፍንጩ ተገኝቷል? ፈረንሳይና እስዊትስዘርላንድ ድንበር የሚገኘው ፣ በአውሮፓ፣ 21 መንግሥታትን ያስተሣሠረው

https://p.dw.com/p/15RKQ
ምስል 1997 CERN

ያስተሣሠረው የአውሮፓውያን የኑክልየር ተመራማሪ ድርጅት ወይም የአውሮፓው የፊዚክስ ምርምር ማዕከል (CERN)፣ በዛሬው ዕለት ጀኔቭ ውስጥ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤

Schweiz Deutschland Forschung Rolf-Dieter Heuer CERN
ምስል 2012 CERN

ለረጅም ጊዜ ሲፈለግ ከነበረው «ሂግስ ቮሰን» ቅንጣት ጋር የሚገጥም፣ ልዩ ዓይነት የቁስ አካል ኢምንት ቅንጣት ፤ በቤተ ሙከራ መገኘቱን አስታወቀ። ያም ሆኖ የቤተ ሙከራው ምርምር ጉዳይ፣ ቃል አቀባይ «ጆ ኢካንዴላ»፣ «ውጤቱ ፣ ገና እንደ ጅምር እንጂ

የተሟላ ተብሎ የሚነገር አይደለም» ይላሉ። ይህን እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ያለማመሣከሪያ በቀጥታ ግኝት ነው ብሎ መግለጥ አስቸጋሪ ነውም ባይ ናቸው።

CERN ዛሬ መግለጫ ከመስጠቱ 2 ቀናት ቀደም ሲል ፤ የዩናይትድ እስቴትስ የፊዚክስ ሊቃውንት፤ ከቺካጎ ወጣ ብሎ ከሚገኘው ፈርሚ ብሔራዊ የምርምር ጣቢያ ስለሂግስ ቦሰን ፍንጫ አግኝተናል ሲል አስታውቆ ነበር።

የ CERN ዋና ሥራ አስኪያጅ ሮልፍ ሆየር ፤ «ስለፍጥረተ ዓለም እጅግ ጠቀሚ ግንዛቤ ከምናገኝበት አንድ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል» ሲሉ ተናግረዋል።

«እንደማንኛውም ተራ ሰው ያገኘነው ይመስለናል ነው ማለት የምችለው! ትስማማላችሁ?

ዛሬ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ የደረስንበት ዕለት ነው። ነገር ግን፣ ጅምሩ ላይ ነን ወደፊት ብዙ ሥራ ይጠብቀናል። አዲስ ምዕራፍ ነው። እንደሚመስለኝ ሁላችንም ልንኮራና ልንደሰት እንችላለን። ግን እንዳልኩት ጅምር ነው። ለወደፊቱ ዓለም አቀፍ ትርጓሜ ያለው ይሆናል። የተከናወነውም በትክክለኛው ጊዜ ነው። እናም እንደሚመስለኝ ብሩኅ ተስፋ ሊያድርብን ይገባል።»

CERN Teilchenbeschleuniger Higgs-Boson
ምስል dapd

እስኮትላንዳዊው ሳይንቲስት ፒትር ሂግስ እና ሌሎችም ስለቁስ አካል መገኘት ባሠፈሩት ነባቤ-ቃል፣ ቁስ አካል መግዘፍ ለቻለበት ክሥተት ምሥጢሩም ሆነ ምንጩ ፤ እጅግ ኢምንቱ የቁስ አካል ቅንጣት ነው ሲሉ ማሥፈራቸው እሙን ነው። «ሂግስ ቦሰን» የተባለውን ማለት ነው። የ CERN ሳይንቲስቶች፣ በቤተ ሙከራ የተገኘው ቅንጣት፤ ሂግስ በነባቤ ቃል የገለጸው ቅንጣት ነው አይደለም ሌላው የሚያነጋግራቸው ጉዳይ ሆኗል። የተገኘው፤ የአቶም ቅንጣት ንዑስ ክፋይ ከሆነና ከሂግስ ቅንጣት ትንሽም ቢሆን የተለየ ከሆነ፣ ይበልጥ የሚያስደንቅ ነው የሚሆነው። ምነው ቢሉ፣ ተጨማሪ ወይም እስካሁን ሊታይ ያልቻለውን ጽልመታዊ ቁስ አካል የሚያመላክት ይሆናልና። ጽልመታዊ ቁስ አካል የሚሰኘው የፍጥረተ ዓለም 96 ከመቶ መሆኑ ነው የሚነገርለት። ፍጥረተ ዓለም (UNIVERSE )

በተደጋጋሚ እንደሚባለው፤ ከ 13 ,7 ቢሊዮን ዓመት በፊት ነው በ«ታላቁ ፍንዳታ » (Big Bang) አማካኝነት በአንድ ሺህኛ ሴኮንድ ውስጥ ሊከሠት የቻለው ። ቁስ አካል ፤ እሳት የሚተፉ ከዋክብት፣ የራዱ ፕላኔቶች፤ ሁሉም የተገኙት በዚሁ እጅግ ኃይለኛ ፍንዳታ ሳቢያ መሆኑ ነው የሚነገረው። ለፍንዳታ ያበቃውን እሳት ማን ፣ ምን ጫረው? ለዚህ ጥያቄ ፤ ከሥነ ፍጥረት ጠበብት መልስ የማግኘቱ ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር የሚቀመር ፤ የሚሰላ፤ የሚኮሰል ጉዳይም አይደል!

Zuwachs im Sonnensystem
ምስል picture-alliance/dpa

ፍጥረተ ዓለም ፤ ሀድ የለውም ! ወርድና ስፋቱ የት እየሌሌ ነው። ከአድማስ -አድማስ የሆነው ሆኖ፤ በአሁኑ ጊዜ ርዝመቱ 40 ቢሊዮን የብርሃን ዓመት መሆኑ ነው የሚነገርለት! በብርሃን ዓመት በሚቆጠርበት ርቀት የሚገኙ ሌሎች ዓለማትን የማሳሱ ጉዳይ ህልም እንጂ ገሐዳዊ ሊሆን መቻሉ፣ እጅግ ነው የሚያጠራጥረው።

ፍጥረተ ዓለም ፤ ደርዝ፤ ሥርዓት፤ የራሱ ስሌት ያለው ነው። እርግጥ፤ ከኛ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እምብዛም ሊጣጣም የማይችል ፤ እጅግ በላቀ ሁኔታ የተወሳሰበ መሆኑ ነው የሚነገርለት። የተፈጥሮ ሳይንስ ጠበብት የሚሰጡት ትንታኔ ከሂሳብ ቅመራው አያፈነግጥም። በማይዳሰሰውም ሆነ በጭብጡ ዓለም ፤ ቀመሩ ፤ ብዙውን ጊዜ ከእውነታ

አይርቅም። እንዲያውም አንዳንድ የፊዚክስ ሊቃውንት ፍጥረተ ዓለም በአጠቃላይ የሂሳብ ቀመር ነው ባዮች ናቸው።

ያም ሆኖ ፣ አንዲት ኢምንት ቅንጣት፣ ለፍጥርተ-ዓለም መዘርጋት፤ ለፍጥረተ ዓለም ቁስ አካላት ግኝት፣ መሠረት ሆኗል የሚለው ነባቤ-ቃል፣ እስካሁን ሊቀ-ሊቃውንቱን ሁሉ ሲያስዳክር መቆየቱ የታወቀ ነው። እልባትም ገና አልተደረገለትም።

Venusdurchgang
Venusdurchgangምስል picture-alliance/dpa/dpaweb

በፈረንሳይና እስዊትስዘርላንድ ድንበር ላይ በሚገኘው በትኅተ-ምድር 100 ሜትር ጥልቀት ውስጥ በተገነባው 27 ኪሎሜትር ዙሪያ ጥምጥም መሿለኪያ ድልድይ መሰል ቦታ ላይ የሚገኘው የአውሮፓውያኑ የኑክልየር ምርምር ጣቢያ(CERN) ፤ ባለፈው መስከረም ወር 3ኛ ሳምንት ላይ የአቶም ንዑሳን ቅንጣቶች (ንውትሪኖስ)ከሞላ ጎደል ከብርሃን ፍጥነት በላቀ ሁኔታ እንደሚመጥቁ አስታወቆ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን ፤ ውጤቱ ፤መቶ- በመቶ በማያስተማምነበት አጠራጣሪ ሁኔታ መግለጫ መስጠቱ ትክክል እንዳልሆነ ያኔም ቢሆን የተቃወሙ ጠበብት እንደነበሩ ተመልክቷል።

ከብርሃን የሚፈጥን ምንም እንደሌለ ፣ የአእማቱም ሆነ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አይንሽታይን ፣ እ ጎ አ በ 1905 ዓ ም፤ የስበት ኃይል፤ ጊዜ ፤ የኃይል ምንጭና ቁስ አካል በተጣመሩበት ቅመራው ማረጋገጡ የታወቀ ሲሆን፣ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው፣ የአውሮፓው የኑክልየር ምርምር ጣቢያ(CERN)፣ ባለፈው መስከረም፤ ኢምንት የአቶም ቅንጣቶች «ኒውትሪኖስ» ከብርሃን ፍንጠቃ ፤ በ 60 ቢሊዮንኛ ሴኮንድ ፈጥነው ይንቀሳቀሳሉ በማለት ማስታወቁ ፤ በእርግጥም የተቻኮለ መግለጫ ነበር።

Albert Einstein Porträt
ምስል AP

ፍጥረተ ዓለም መጠኑ እጅግ እየሰፋና ፍጥነቱም እጅግ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ፤ በዚህ የምርምር ዘርፍ ላይ ያተኮሩ ጠበብት ይናገራሉ።

ፍጥረተ ዓለምን የሚያከንፈው፣ ከፍጥረተ ዓለም ዐበይት ምሥጢራት አንዱ መሆኑ የሚነገርለት፣ «ጽልመታዊ ኀይል (Dark Energy) የሚሰኘው ነው ። ይህ ደግሞ ፍጥረተ ዓለም ፣ መገመት በሚያዳግት ፍጥነት በሚጓዝበት የማያልቅ ጉዞ፣ ፕላኔታችን፤ ምድርና በውስጥዋና በላይዋ የሚኖረው ፍጡር ፤ ጸሐይና አጫፋሪዎቿ ፕላኔቶች፤ ጨረቃዎች፤ ስብርባሪ ከዋክብት ፤ በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ የሚገኙበት የኅዋ ቀጣና ፤ ፍኖተ ኀሊብ (MILKY WAY)በሰዓት 2,1 ሚሊዮን ኪሎሜትር ነው የሚከንፈው።

Schweiz CERN Forschung Schnelle Teilchen überholen Licht Sprecher Antonio Ereditato
ምስል dapd

የዓለም የነፋስ ኃይል ምንጭ ማኅበር ጉባዔ፣ በቦን፤

ከትናንት አንስቶ እስከ ነገ በዚህ በቀድሞዋ የጀርመን ፌደራል ሪፓብሊክ ርእሰ ከተማ በቦን፣ በጀርመን የነፋስ ኃይል ምንጭ ማኅበርና በዓለም የታዳሽ ኃይል ምንጭ ድርጅት ትብብር ዓለም አቀፍ የነፋስ ኃይል ነክ ጉባዔ በመካሄድ ላይ ነው።

የጀርመን ፌደራል መንግሥት፣ ጃፓን ውስጥ ፉኩሺማ ላይ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት መሆኑ ነው፤ በምድር ነውጥና በውቅያኖስ ማዕበል ሳቢያ አደገኛ የአቶም ኃይል አውታር ፍንዳታ ከደረሰ በኋላ ፣ በአማራጭ ኃይል ምንጭ ላይ ለማትኮር ታጥቆ መነሣቱ የሚዘነጋ አይደለም። ዐበይት ግምት ከተሠጣቸው አማራጭ ታዳሽ የኃይል ምንጮች መካከል አንዱና ምናልባትም ቀዳሚውን ቦታ የያዘው ፣ የነፋስ ኃይል ነው። ይህን የተፈጥሮ ኃይል ደግሞ ባግባቡ ለመጠቀም፤ሥነ-ቴክኒኩ ይበልጥ መሻሻል እንዳለበት በጥብቅ ይታመንበታል። ሥነ-ቴክኒኩ ብቻ ሳይሆን ፣ ከተፈጥሮ ይዞታ ባሻገር ፣ የተገልጋዩን ህዝብ ና የመንግሥትንም ጥቅም በማሰላሰል፣ መመሪያ ደንቦች ሊወጡ እንደሚገባ ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መ/ቤቶች ሳያስቡበት አልቀሩም።

የነፋስ ኃይል ጠቀሜታ እንዲህ ጎልቶ የሚነገርበት ምክንያት ምን ይሆን?

በመጀመሪያ ፤ ለተፈጥሮ አካባቢ ጠንቀኞች ካልሆኑት ታዳሽ የኅይል ምንጮች መካከል አንዱ በመሆኑ የሚመረጥ ነው። አንዳንዶች እንደሚገምቱት ፣ እንዲያውም ከሁሉም በአፋጣኝ ሥራ ላይ በመደረግ ላይ ያለው የነፋስ ኃይል ምንጭ ነው። ይህ የኃይል ምንጭ በዓለም ዙሪያ በቀዝቃዛም በሞቃትም አገሮች ሁሉ ፤ አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው። የፀሐይ ኃይል ምንጭ አብዛኛውን ጊዜ የሚገኘው የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት ዘወትርም ሆነ አያሌ ወራት ባላማቋረጥ በሚያገኙ አገሮች መሆኑ የሚታበል አይደለም። ነፋስ ግን ምንጊዜም በሁሉም ቦታ አለ። ባለፈው ዓመት፣ በዓለም ዙሪያ፣ ከነፋስ ኃይል ከሞላ ጎደል 140,000 ሜጋዋት ኤልክትሪክ ማመንጨት መቻሉ ታውቋል። ይህም፣ በግምት የ 240 ታላላቅ የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮችን ጉልበት የሚያጠቃልል መሆኑ ነው።

Schweiz CERN Forschung Schnelle Teilchen überholen Licht Globus
ምስል dapd

ጀርመን ፤ እ ጎ አ እስከ 2030 ፣ 15 ከመቶ የኤልክትሪክ ኃይል ምንጭን፣ በነፋስ ኃይል ፣ ከሚሽከረከሩ ረዣዥም የብረት ማማወች ለማግኘት ነው ያቀደችው። በአጠቃላይ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ፤ ከፀሐይና ከነፋስ በአሁኑ ጊዜ 20 ከመቶውን የኃይል ምንጭ የምታገኘው ጀርመን፤ እስከ 2020 መጠኑ ወደ 35 ከመቶ ከፍ እንዲል እቅድ አላት። እ ጎ አ በ 2050 ደግሞ ፤ 80 ከመቶውን የኃይል ምንች ፍልጎቷን ፤ ታዳሽ የኃይል ምንጮች እንዲያሟሉላት ለማድረግ ማቀዷን ነው፣ የረጅም ጊዜ የኃይል ምንጭ ስልቷ የሚያመላክተው። በሰሜን ባህር ከጠረፍ ገባ ብሎ በተተከሉ አውታሮች ፤ ከ 2 ዓመት በፊት፣ 200 ያህል ሜጋዋት ኤልክትሪክ ታመነጭ ነበር ። በረጅም ጊዜ እቅዷ ግን በዚያው በሰሜን ባህር በሚተከሉ አውታሮች 10 ሺ ሜጋዋት የኤልክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው የምትሻው። በእቅዱ መሠረት ፣ በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩት አውታሮች የሚተከሉትም ሆነ በመተከል ላይ ያሉት፤ ከጠረፍ ጥቂት ፈንጠር ብሎ በሰሜንና ምሥራቅ ባህሮች ላይ ነው።

Dänemark Offshore Windpark Windenergie
ምስል AP

መንግሥት፤ ከህዝብ በሚገኘው ቀረጥ በመተማማን፤ ኩባንያዎች ሊከተሏቸው ይገባል ያላቸውን ህግጋትንም ሆኑ ደንቦችን፣ በማውጣት ላይ እንደሚገኝም ታውቋል። የጀርመን የኤኮኖሚ ሚንስትር ፊሊፕ ሮዖዝለርና የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ሚንስትር ፔተር አልትማየር፤ ሥራቸው እንዳልሠለጠ የሚነገርለቸውን በባህር ላይ የተተከሉትን በነፋስ ኃይል ኤልክትሪክ የሚያመንጩ አውታሮች ተግባር በተኀድሶ ለውጥ የሚሻሻልበትን ሐሳብ አቅርበዋል።

ጀርመን ፤ በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚችሉ አውታሮችን የሚሠሩ ታዋቂ ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች አሏት። ከታወቁት መካከል ፣ «ኖርዴክስ» ፣ RWE (Rheinisch-Westfälische Elektrizitätswerke)እና Fuhrländer AG የተባሉት ይገኙበታል። ዮናስ ሙዑለር የተባሉት ፤ በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጨው ኩባንያ የፕሮጀክት ጉዳይ ኀላፊ፣ እንዲህ ይላሉ--

«እዚህ የምናየው፤ ውስጡ ክፍት በሆነው ግዙፍ የብረት ዓምድ ውስጥ የሚገባውን ሽቦ ነው። በአንድ በኩል ክብደቱ ቀላል ነው፤ ይሁን እንጂ ፍጹም ጠንካራና በነፋስ ኃይል ለሚሠራው አውታር በሚገባ የሚስማማ ነው።»

ቦን ውስጥ እስከ ነገ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ፤ ከነፋስ የሚገኝ የኃይል ምንጭ ለዜጎች የሚሰጠው ጠቀሜታ ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም፤ የሥነ-ቴክኒክ ምርምርና ኤኮኖሚ የሚመክርባቸው ጉዳዮች ናቸው።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ