1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቅዝቃዜ ማዕበል በአዉሮጳ

ማክሰኞ፣ የካቲት 20 2010

አዉሮጳን ላዳረሳት የቅዝቃዜ ማዕበል፤ "The Beast from the East" ማለትም «ከምሥራቅ የመጣዉ አዉሬ» የሚል ስያሜ ሰጥተዉታል የአዉሮጳ መገናኛ ብዙሃን። ለስያሜው መነሻ የሆነው የአካቢዉን የክረምት ወቅት ቅዝቃዜ ካለፉት ቀናት ወዲህ ያባባሰዉ በረዶ አዘል ቀዝቃዛ ንፋስ መነሻ በብርዱ የሚታወቀዉ ሳይቤሪያ በመሆኑ ነዉ።

https://p.dw.com/p/2tQPR
Italien Winter & Schnee in Rom | Petersdom
ምስል Reuters/M. Rossi

ከባዱ ቅዝቃዜ ለቀናት እንደሚዘልቅ ነዉ የተነገረው

 

 የሜትሪዎሎጂ ባለሙያዎች ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም የክረምት ወቅት ጀምሮ  ባልተለመደ መልኩ የወረደ ቅዝቃዜ በአዉሮጳ እና እስያ እንደሚከሰት አስቀደመው ነበር የጠቆሙት፤ አሁንም ዳግም እያሳሰቡ ነዉ። ይህ ከተለመደው በታች የወረደ ቅዝቃዜም በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን አቆጣጠር የካቲት ወር እስኪያልቅ ማለትም እስከ ነገ እና ከነገ ወዲያ እንደሚቀጥልም ይናገራሉ። በእነዚህ ቀናትም በተለይ በምሥራቅ አዉሮጳ እና በስካንዴኔቪያ ሃገራት እጅግ የበረታ ቅዝቃዜ ይጠበቃል፤ የአየር ሁኔታ ትንበያዉም ያንኑ ነዉ የሚያሳየው። ብሪታንያን ጨምሮም ከዜሮ በታች 10 እና 20 ዲግሪ ሴልስየስ ገደማ የሚደርሰዉ ቅዝቃዜ ሁኔታም ለቀጣይ ቀናት እንደሚቆይም የብሪታኒያ የአየር ሁኔታ ትንበያ መሥሪያ ቤት ገልጿል። ከወደ ምሥራቅ አዉሮጳ የሚነፍሰዉ ጠንካራ ቅዝቃዜ እና እጅግ የበረደዉ ነፋስም በምድረ እንግሊዝም ሆነ በአዉሮጳ ሃገራት በአመዛኙ በረዶን እንደሚያስከትል ተነግሯል። በትናንትናዉ ዕለትም በረዶው ሊያስከትል ይችላል የተባለዉን ችግር ለመቀነስ ተማሪዎች ባስቸኳይ ወደ የቤታቸዉ እንዲሄዱ መደረጉን የዘኢንዲፔንደት ምስልን ያስደገፈ ዘገባ ያስረዳል።

ዛሬ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በአንዳንድ አካባቢዎች እስከ ስምንት ሴንቲ ሜትር የተከመረዉ በረዶ የባቡር መጓጓዣዎችን አስተጓጉሏል፤ እንስቃሴዎችንም አደናቅፏል። በግጭት ምክንያትም ቢያንስ የሦስት ሰዎች ሕይወት አሳጥቷል። ፖሊስ አስቀድሞ ነበር በጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳሰበዉ። ኃይለኛዉን ቅዝቃዜ ተከትሎ ባልተለመደ ሁኔታ በረዶ የወረደባት ሮም ከተማም የባቡሮች እንቅስቃሴ ሳይቀር ተስተጓጉሎባታል። ቢያንስ የአራት ሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል። ዛሬ ከትናንቱ ይሻላል ቢባልም ከከተማዋ ዋና የባቡር ጣቢያ የሚነሱ መንደኞች ከ7 ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ባቡሮችን መጠበቅ ተገደዋል። ከመንገደኞች አንዱ፤

Schnee in Rom Italien
ምስል picture-alliance/Photoshot

«የትናንቱ የከፋ ነበር። ዛሬ የተሻለ ይሆናል ብዬ ነበር ሆኖም ግን እስካሁን በርካታ ባቡሮች ጉዞዎች ሲሰረዙ አይቻለሁ። አሁን እንዲያዉም ፈጣን እና የረዥም ርቀት ባቡሮችን ሁሉ መሠረዝ ጀምረዋል።»

ሮም ላይ ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 ወዲህ በረዶ ሲወርድ ይህ የመጀመሪያዉ ነዉም ተብሏል። የምድር ባቡር ባለስልጣናትም በከባዱ ቅዝቃዜ ምክንያት ባቡር ጣቢያዎች ጎዳና ላይ ለሚያድሩ ወገኖች በጊዜዊ መጠለያነት እንዲያገለግሉ ፈቅደዋል።

ፖላንድ ላይም የሰሞኑ ቅዝቃዜ የሁለት ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል። ፖላንድ ዉስጥ በዘንድሮዉ ክረምት ከብርዱ ጋር በተገናኘ እስካሁን የሞቱት ሰዎች ቁጥር 48 ደርሷል። በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ ባለንስ ከተማም አንድ ጎዳና ላይ የሚያድር ሰዉ እሁድ ዕለት ሞቶ ተገኝቷል። 

Russland Moskau kämpft gegen Schneemassen
ምስል picture-alliance/dpa/TASS/A. Geodak

ሳይቤሪያን አቅፋ በምትገኘው ሩሲያም የዘንድሮዉ ክረምት እጅግ የበረታ ቅዝቃዜ ይዞ እንደመጣ ነው የሚነገረዉ። ከትናንት በስተያ እሁድ ሌሊትም በዚህ ዓመቱ ክረምት ከፍተኛ መሆኑ የተነገረለት ብርድ በመላ ሀገሪቱ ተመዝግቧል፤ ከዜሮ በታች 20 ዲግሪ ሴልስየስ ። ጎዳና ላይ ለሚኖሩ ሰዎች እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ሞስኮ ከተማ ትናንት የሞቀ ምግብ የሚፈልጉ 150 ሰዎችን ማስተናገዳቸዉን ተናግረዋል። በያዝነዉ የካቲት ወር መጀመሪያ አንስቶ ሞስኮ እጅግ በርካታ በረዶ ወርዶባታል። እንደዉም ከወር በላይ የወረደዉ የበረዶ መጠን በአማካኝ ከፍተኛ በመሆኑ ለታሪክ ተመዝግቧል። ሜርሲ የተሰኘዉ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚረዳዉ ማዕከል ባልደረባ ፕሪስተ ኦልጋ።

«ድንኳናችን ከዳር እስከ ዳር በበረዶ ተሞልቷል። እርግጥ በክረምት ወቅት ብዙ ሰዎች ወደ እኛ ይመጣሉ። በበጋ ወቅት ዉጭ መሆን፣ ሳር ላይም መተኛት ይችላሉ። በክረምት ግን ዉጭ በሚገኙት አግዳሚዎች ላይ መተኛት አይሞከርም።»

የአየር ጠባይ ትንበያዉ ከፊታችን በሚመጡት የጎርጎሪዮሳዊዉ መጋቢት ወር የመጀመሪያ ቀናት ከዚህ በፊት በዚህ ወቅት ባልተለመደ መልኩ እጅግ የበረታ ቅዝቃዜ እንደሚኖር ከወዲሁ አስጠንቅቀዋል።

Moskau Winter Schneefall
ምስል picture-alliance/TASS/A. Geodakyan

በተመሳሳይ የቅዝቃዜ እና በረዶ ክምችት ዉስጥ የምትገኘዉ ሌላዋ ሀገር ኦስትሪያ ናት። ዋና ከተማ ቪየና ላይ የቅዝቃዜዉ መጠን ትናንት ጠዋት ከዜሮ በታች 13 ዲግሪ ተመዝግቧል። እንዲያም ሆኖ ምን እንኳን ቅዝቃዜዉ ቢበረታም በረዶ ባለመውረዱ ከዚያ ጋር የተዳመረ ቀዝቃዜ ንፋስ የለም ነው የተባለዉ። በምሽት ደግሞ በመላዉ ኦስትሪያ የቅዝቃዜዉ መጠን ከዜሮ በታች 20 ዲግሪ ይደርሳል። ቪየና አዉሮፕላን ማረፊያ ላይ የሚሠሩት ሚኻኤል ዛሳማሎቪትስ በዚህ ብርድ ዉስጥ የሥራ ዉሏቸዉን ሲናገሩ፤

«ዉጭ ስትሆን በጣም ይበርድሃል፤ አዉሮፕላኑን ለበረራ ማዘጋጀቱ አንድ ሰዓት ድረስ ይወስዳል፤ ደጋግሞ የመንቀሳቀስ ዕድሉ ስለሌለ ጣቶች ቆፈን ይይዛቸዋል።»

ይህ ቀዝቃዜ የአየር ሁኔታም ኦስትሪያ ላይ እስከመጪዉ ሳምንት ጠንክሮ እንደሚቀጥል ነው ከወዲሁ የአየር ሁኔታ ትንበያዉ ያመለከተዉ። ስዊዘርላንድም ቢሆን ቅዝቃዜዉ ከጠነከረባቸዉ ሃገራት አንዷ ናት። በወንዞች ዳርቻ ላይ ዉኃው የተጋገረ በረዶ ሠርቶ በተንቀሳቃሽ ምስልም ሆነ ፎቶ ይታያል። እንዲህ ያለዉ ገፅታም ከስዊዘርላንድ ሌላ በበርካታ አጎራባች የአዉሮጳ ሃገራት በየዕለቱ በመገናኝ ብዙሃን እየተገለፀ ይገኛል።

ከሰርቢያ የነፈሰዉ በረዷማ ንፋስ ተፅዕኖ ካሳረፈባቸዉ ሃገራት አንዷ ዴንማርክ ናት። የአየር ጠባይ ሁኔታ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ካሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ አንስቶ እጅግ የቀዘቀዘዉ አየር የሚያስከትለዉን ማንኛዉንም አጋጣሚ ለመቋቋም በሀገሪቱ የሚገኙ የድንገተኛ ጉዳይ ማዕከላት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጋቸዉ ተነግሯል። መጠኑ ከፍ ያለ በረዶ ይወርዳል ተብሎ በሚጠበቅባት ቦርንሆልም ከተማ በረዶዉን እየዛቁ መንገድ የሚከፍቱ ተሽከርካሪዎች ከእሁድ ጀምሮ አስቀድመው መዘጋጀታቸዉን በዴንማርክ የአስቸኳይ ጊዜ ተቋም የተጠቀሰችዉ ከተማ ባልደረባ ሻርሎቴ ብራን ተናግረዋል።

Bildergalerie Kältewelle Europa Kosovo
ምስል Getty Images/AFP/A. Nimani

«እኛ ራሳችን ሁለት የበረዶ መጋፊያ ተሽከርካሪዎች አሉን። እነሱ ሥራ ላይ ናቸዉ። በዚያም ላይ ኒስትቬድ ከሚገኘዉ የዴኒሽ የአስቸኳይ ጊዜ ተቋም ድጋፍ እያገኘን ነው። በተጨማሪ ደግሞ ሁለት በረዶ ጠራጊ ተሽከርካሪዎች ወደ ቦርንሆልም ዛሬ ጠዋት በመምጣት ላይ ናቸዉ።»

በሮማንያም ይኸዉ ቅዝቃዜ እና በረዶ ትምህርት ቤቶችን እና የመጓጓዣ እንቅስቃሴዉን አስተጓጉሏል። የአስቸኳይ ጊዜ ሠራተኞች ኅብረተሰቡን እንዲረዱ ትዕዛዝ የተላለፈ ሲሆን ትምህርት ቤቶቹ ቢያንስ ለሁለት ቀናት እንደተዘጉ ነዉ የተነገረዉ።

በአንድ ወገን የብርዱ መጠንከር ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን ጤና ቢያዉክም ይዞት የመጣዉ በረዶ ለበርካቶች መዝናኛ ሆኗል። በረዶዉ በገፍ በወረደባቸዉ አካባቢዎች ታዲያ የበረዶ ሸርተቴ ስፖርት አዘዉታሪዎች ትጥቃቸዉን ይዘዉ ተሰማርተዋል።

በኮሶቮ ዋና መዲና ፕሪሽቲና የበረደ ሰዉ የተሰኘዉ የክረምት ስፖርት ማኅበረሰብ የበላይ አስተባባሪ አርበን ኢስላሚ ሰዉነትን በሚያኮማትረው የክረምቱ ወራት በረዶ ሲወርድ ለስፖርት አዘዉታሪዎቹ ሰርግ እና ምላሽ አይነት ነዉ ይላሉ።

«ብዙ በረዶ በሚኖርበት ጊዜ ደስታችን ነው። ለበረዶ ሸርቴ ስፖርት የሚሆኑ ጥቂት ግሩም ቦታዎች አሉ። አሁን ከእነዚህ ቦታዎች አንዱ የሆነው ጎዳና ላይ ነው ሙከራ በማድረግ ላይ ነን። ወደሌላኛዉ ቁልቁለታማ ጎዳና ደግሞ እሄዳለን። እናም እየተደሰትን ነው።»

Pyeongchang 2018 Olympische Winterspiele | Freestyle Ski Cross
ምስል Reuters/I. Kato

ኮሶቮ ላይ የሙቀቱ መጠን ከዜሮ ዲግሪ ሴልስየስ በታች እጅግ ዝቅ ካለ ሁለት ሳምንታት አልፈዉታል። ዶቼ ቬለ ራዲዮ መቀመጫ በሆነችዉ ቦን ከተማ የክረምቱ ወራት ብርድ ከሌሎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይነት አልነበረም። ከሰሞኑ ግን አይሏል። የሙቀቱ መጠን ከዜሮ በታች ሆኖ ፀሐይ ወጥታ መታየቱ አንድ ነገር ቢሆንም ሙቀት ግን አይታሰብም። ጀርመንም ባጠቃላይ ከፍተኛ ከሚባሉ የክረምት ወራት ቀዝቃዛ ምሽቶች አንዱ የሆነዉን እያስተናገደ እንደሆነ ነው የሚነገረዉ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ብርዱ በሚጠናባቸዉ አካባቢዎችም ሌሊት ቅዝቃዜዉ ከዜሮ በታች 20 ዲግሪ ሴልስየስ ድረስ ይወርዳል። በዚሁ ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ ምክንያት በነገዉ ዕለት በርሊን ለሚገቡት የጋና ፕሬዝደንት ናና አኩፎ አዶ የታቀደዉ ወታደራዊ አቀባበል መሰረዙን የመራሂተ መንግሥቷ ጽሕፈት ቤት መግለፁን አሶሲየትድ ፕረስ ዘግቧል። ቅዝቃዜዉ ለቀጣይ ቀናትም እንደሚቆይ ነዉ ትንበያዎቹ የሚያመላክቱት።

ሳይንቲስቶች የዚህ ከባድ ቅዝቃዜ እና ከፍተኛ መጠን ያለዉ በረዶ መዉረድ ዋና ምክንያት በአርክቲክ አካባቢ ከመሬት በላይ 50 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ ያለዉ ከባቢ አየር ማለትም ስትራቶስፌር ላይ  የተፈጠረ ድንገተኛ ሙቀት ነው።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ