1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበሰለ ምግብ ከደንበኞች ደጅ የማቅረብ እቅድ

Eshete Bekeleሐሙስ፣ ጥቅምት 25 2008

በአግባቡ የተሰየመና ቁጥር የተሰጠው ጎዳና በሌላት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በስሎ ለገበታ የተዘጋጀ ምግብን ወደ ደንበኞች የመኖሪያ ቤት የማድረስ ሥራ በርካታ እንቅፋቶች ስላሉበት አልተጀመረም። ዴሊቨር አዲስ የተሰኘው አዲስ አገልግሎት አቅራቢ ግን ከተማዋ ላሉባት ችግሮች መፍትሄ አግኝቻለሁ እያለ ነው።

https://p.dw.com/p/1H0gt
Neue Lebensmittel Lieferservice
የምግብ ቤት ባለቤቱ አቤል ወንደሰንና የዴሊቨር አዲስ መስራች ፈለገ ጸጋዬምስል James Jeffrey

[No title]

በአካፑልኩ ሜክሲኮ ግሪል ኤንድ ባር አንድ ደንበኛ ስልክ ደውለው ምግብ እንዳዘዙ የዶሮ ስጋ ተጠባብሶ ባሪዮት የተሰኘው የሜክሲኮ ምግብ መዘገጃጀት ተጀመረ። በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ዝግጁ ሆኖ ከዴሊቨር አዲስ ምግቡን የሚያደርሰውን ሞተር ብስክሌተኛ እየተጠባበቁ ነው። አልቆ የተዘጋጀ ምግብን ከደንበኞች በራፍ የሚያደርሰው ዴሊቨር አዲስ የተሰኘ አገልግሎት አቅራቢ የተጀመረው በዩናይትድ ስቴትስ ተወልዶ ባደገው ኢትዮጵያዊ ፈለገ ጸጋዬ ነው።

Neue Lebensmittel Lieferservice
ምስል James Jeffrey

«ከሶስት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ በአካባቢዬ ያሉት የምግብ ቤቶች ሰለቹኝ። አምሽቼ ወደ ቤቴ ስገባ በኢንተርኔት ምግብ ማዘዝ እፈልግም ነበር። ባለፈው መጋቢት ወር እንዴት ሊሰሠራ እንደሚችል መሞከር ጀመርኩ። በፍጥነት ድረ-ገጽ ሠርቼ የተወሰኑ ምግብ ቤቶችን በማነጋገር ሞተር ብስክሌት ከተከራየሁ በኋላ ሰላሳ የሚሆኑ ጓደኞቼ እንዲጠቀሙበት አደረኩ። ሰነፍ መሆን ነበር የፈለኩት። ማታ ምግብ ከማብሰል ይልቅ እንዲህ ለማዘዝ። ምላሹ ግን በጣም የከፋ ሆነና በሕይወቴ በሥራ ብዛት የተወጠርኩበት ጊዜ ሆነ። ከመጋቢት ጀምሮ ያለ ምንም አድራሻ 1,500ትዕዛዝ ላይ ደርሰናል።»

በአዲስ አበባ እንዲህ አይነት አገልግሎት በተለያዩ ምክንያቶች የለም። ከተማዋ በአግባቡ የተቀየሰ የጎዳና አድራሻ የላትም። አብዛኞቹም የጎዳናዉን ስያሜ የሚያመለክት ምልክት የላቸውም። በፖስታ የሚላኩ መልዕክቶችም በቀጥታ የሚያመሩት ወደ ፖስታ ቤት ነው። በከተማዋ የሚገኝ አንድ ሕንጻን ለማግኘት በአካባቢው የሚገኙ ምልክቶችን በመጠቀም ግራ አጋቢ ፍለጋ ማካሄድን ይሻል። ብዙዎቹ በርካታ ስያሜ ያላቸው ናቸው።

አብዛኛው ምግብ በቤት የሚዘጋጅ በመሆኑ እንዲህ አይነቱ የምዕራባውያን አገልግሎት የተለመደ አይደለም። ብዙ ሰዎች ገቢያቸው አነስተኛ በመሆኑ ጊዜ ቆጣቢ የሆነውን ይህን አገልግሎት የመጠቀም ፍላጎታቸው አናሳ ነው። ይሁንና አዲስ አበቤዎች ዘመናዊ አኗኗር በመላመዳቸዉና የ26 ዓመቷን ሽሚ ንጉሴን የመሳሰሉ በውጭ አገራት ይኖሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት መመለስን በመምረጣቸው ተቀባይነት እያገኘ ነው።

Neue Lebensmittel Lieferservice
ምስል James Jeffrey

«ከአንድ ዓመት በፊት ከዩናይትድ ስቴትስ ከመጣሁ ጀምሮ ምግብ ለማስመጣት የኮንትራት ታክሲዎችን እጠቀም ነበር። ምግብ ቤቱን ሊያውቁት ካልቻሉ አድራሻውን መናገር ይኖርብኛል። ሥራ ከበዛባቸው ደግሞ ከነ ጭራሹ ምግቡም አይገኝም። ወደ ኢትዮጵያ መመለስ በጣም ጥሩ ቢሆንም በየቀኑ እንጀራ ብቻ ልመገብ አልችልም። የታይላንድ ወይም የጃፓን ምግብ ልፈልግ እችላለሁ። በዚህ ደረጃ አዲስ አበባ እኛ በታክሲ አሽከርካሪዎች የጀመርንው ዓይነት የራሷን የበሰለ ምግብ አቅራቢ ትሻለች።»

ዴሊቨር አዲስ አሁን ተንቀሳቃሽ ስልክና የአቅጣጫ ጠቋሚ ሶፍትዌር የሚጠቀሙ በአራት የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ከተመረጡ 12 አጋር ምግብ ቤቶች ጋር አብሮ ይሠራል። ከምግብ ቤቱ በአራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለሚገኙ ደንበኞች ስልሳ ብር የሚያስከፍል ሲሆን ርቀቱ ከጨመረ ክፍያው 75 ብር ይደርሳል።

ከዩናይትድ ስቴትስ ከአንድ ዓመት በፊት የተመለሰው አቤል ወንድወሰን የሜክሲኮ ግሪል ኤንድ ባር ባለቤት ነው።

«ፈለገ ከዝርዝር ውስጥ ለመካተት ፈቃደኝነታችንን ሲጠይቅ በፍጥነት ነበር እሺ ያልንው። ከጥቂት ቀናት በኋላ ትዕዛዞች መምጣት ጀመሩ። ይህ በየሳምንቱ በርካታ ምግቦችን በመሸጥ ተወዳዳሪነታችንን ያሳድጋል። አዲስ አበባ እንዲህ አይነት የበሰለ ምግብ አቅራቢ ቢያስፈልጋትም ሥራው ቀላል አይደለም።»

Neue Lebensmittel Lieferservice
ምስል James Jeffrey

አቤል የከተማዋ ውስብስብ የመንገድ አጠቃቀም አንድ ችግር መሆኑን ይናገራል። ትኩስ ምግብ ሳይበርድ ለደንበኛው ማድረስና አመኔታ ማግኘትም አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁሟል። ቢሆንም ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል እምነት አለው። ዴሊቨር አዲስ በርከት ያሉ ደንበኞች ለማግኘት ራሱን እያስተዋወቀ ነው። በአዲስ አበባ ለአራት ዓመታት የኖረው የ30 ዓመቱ ሳም ሬይ አሁን የተጀመረውን የዴሊቨር አዲስ አገልግሎት ለመልመድ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ያምናል።

«ገና ስለመለመዱ እርግጠኛ አይደለሁም። ከመኖሪያ ቤቴ ሳልወጣ ምግብ ማዘዝ እችላለሁ ብሎ ለማመን ጊዜ ይወስዳል። ከቤቴ መውጣት በማልፈልግበት አንዳንድ ምሽት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። ዓርብ ምሽት ሁላችንም ሲደካክመን ከቤት ሳንወጣ ቴሌቭዥን መመልከት እንፈልጋለን። ለእራት መውጣት ካልፈለግን ምግባችንን ቤት በማዘዝ እንሞክረዋለን።»

ለፈለገ ጸጋዬና ኩባንያው ዴሊቨር አዲስ የጀመሩት አዲስ ሥራ ዓላማ ገንዘብ ብቻ አይደለም። ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም እድሎችን መፍጠር ዋንኛ ትኩረታቸው ነው። «ማንም ሰው በዚህ ደረጃ ሞክሮት አያውቅም። ምክንያቱም በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። ዓላማዬ ትርፍ ብቻ ቢሆን ኖሮ በዩናይትድ ስቴትስ በቆየሁ ነበር። ልጅ ሆኜ በ2000ዓ,ም ወደ ኢትዮጵያ በመጣሁበት ወቅት እንደ እኔ ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልዩ ፍላጎት ያደረባቸው ሰዎች ተዋውቄ ነበር። ቢሆንም ዕድሉን ባለማግኘታቸውና የሚያበረታታቸው ባለመኖሩ እንደ ሙያ አልቀጠሉበትም። የዛን ጊዜ አንድ ቀን ተመልሼ በመምጣት ዕድሉን ለመፍጠር ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር። ይኸው እያደረኩት ነው።»

የዴሊቨር አዲስ ደንበኞች የከተማዋን ውስብስብ ችግሮች ባይዘነጉም ጅማሮውን አድንቀዋል። የሚገጥሙትን እንቅፋቶች ተቋቁሞ ስኬታማ ሊሆን እንደሚችልም ተስፋ አላቸው።

ጄምስ ጄፍሪ/እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ