1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበደዊ ግርፋትና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት

ዓርብ፣ ጥር 8 2007

በእስር ላይ የሚገኘው የሳውዲ አረቢያው የኢንተርኔት አምደኛ ራይፍ በደዊ ህዝብ በተሰበሰበት ዛሬ ሊገረፍ የተያዘው ቀጠሮ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን መንግሥት አስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/1ELsD
Pictureteaser Free Raif

በበደዊ ላይ የተበየነበት የግርፋት ቅጣት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተቃውሞ ቢቀርብበትም ከተወሰነበት 1 ሺህ የግርፋት ቅጣት 50ው ከአንድ ሳምንት በፊት ተፈጽሞበታል። ዛሬ ደግሞ ለሁለተኛው ጊዜ ህዝብ በተሰበሰበት 50 ጊዜ ይገረፋል ተብሎ ነበር ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የጀርመን መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ትናንት ጥሪ አቅርበው ነበር ።
ነጭ ካናቴራ የለበሰው እሥረኛ ቀጥ ብሎ ቆሟል ። ከፊት ለፊቱ በርካታ የፖሊስ መኮንንኖች ይታያሉ ። ከበስተኋላው የቆመ አንድ የፖሊስ መኮንን ያለማቋረጥ ጀርባውን ይገርፈዋል ። 50 ጊዜ ከገረፈው በኋላ በስፍራው የሰበሰቡት ሰዎች እያጨበጨቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው «አላህ ወ አክበር » «እግዚአብሔር ታላቅ ነው» ሲሉ ያሳይል ራይፍ በደዊሲገረፍ በድብቅ ሳይቀረፅ እንዳልቀረ በተገመተው ቪድዮ ላይ ። ባለቤቱ ኤንሳፍ ሃይዳር ላይ ጥር 1 2007 ዓም በበዳዊ ላይ ያረፈው እያንዳንዱ ጅራፍ እኔንም ገድሎኛል ስትል ለCNN ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግራለች ። ግርፋቱ ዛሬም በ31 ዓመቱ ራይፍ በደዊ ላይ ይቀጥላል ተብሎ ነበር ። ሆኖም መንግሥት ዛሬ ከሰዓት በኋላ እንዳስታወቀው ግርፋቱ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል ።ሳውዲ አረቢያ የኢንተርኔት አምደኛውን በዳዊን « ነፃ ለዘብተኞች» በተሰኘው አምዱ እስልምናን ዘልፏል ስትል የ10 ዓመት እስራት ና 1ሺህ ግርፋት አንድ ሚሊዮን የሳውዲ ሪያል ወይም 266,666 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ፈርዳበታለች ።በውሳኔው መሠረት ከዛሬ ሁለት ዓመት ከ6 ወር ወዲህ በእስር ላይ የሚገኘው በደዊ ለሚቀጥሉት 19ና ከዚያም በላይ ለሚሆኑ ሳምንታት በየሳምንቱ 50 ጊዜ ይገረፋል ነው የተባለው ። የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፍርዱን ከባድ የመብት ጥሰት ወንጀል ብሎታል።የድርጅቱ ባልደረባ ሩት ዩትነር


« ይህ ታላቅ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነው ። እነዚህ ግርፋቶች ሰዎችን ቁም ስቅል ከማሰየት ጋር የሚስተካከሉ ናቸው ። ቅጣቱ እንዲቆምና ራልፍ በደዊ ከእሥር እንዲፈታ እንጠይቃለን ።»
ዩትነር ከሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋር ይህንኑ ጥያቄአቸውን በርሊን በሚገኘው በሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ትናንት በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አቅርበዋል ።አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለኤምባሲው ከ50 ሺህ በላይ የተቃውሞ ደብዳቤዎችን ሰጥቷል ።በዚሁ ሰልፍ ላይ በደዊ ጀርባ ላይ መግረፊያው ሲያርፍ የሚሰማው ድምፅ በድምፅ ማጉሊያ ተሰምቷል ።ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች በፖላንድ በዩናይትድ ስቴትስ በፊንላንድ በኖርዌይ እና በብሪታኒያ ተካሂደዋል ። ከሶስት ልጆቻቸው ጋር ካናዳ በስደት የምትኖረው የበደዊ ባለቤት ስለበዳዊ የጤንነት ሁኔታ ለዩንተር እንደነገረቻቸው አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው ።
«በህመሙ እየተሰቃየ ነው ። ግርፋቱ ህዝብ ፊት መንገድ ላይ የሚካሄድ በመሆኑ ህመሙ አካላዊና ስነ ዐዕምሮአዊም ጭምር ነው ።
የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኖርበርት ላሜርት አሸባሪዎች በፓሪስ ያደረሱትን ጥቃት ባነሱበት በትናንት ንግግራቸው ስለ በደዊ ጉዳይም አውስተው ነበር ።
« በመንግሥት ሙሉ ሥልጣን የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት የሰብዓዊነት መለስተኛ መለኪያዎችም ሳይቀር ከነአካቴው እየተጣሰ ነው ።»

Ensaf Haidar Frau vom Blogger Raif Badawi beim Protest in Montreal 13.01.2015
ምስል picture alliance/empics


እንደ ሌሎቹ ሃገራት ሁሉ ሳውዲ አረቢያ የፓሪስ ጥቃት ብታወግዝም ከሁለት ቀናት በኋላ ግን በደዊን በግርፋት ቀጥታለች ። ላሜርት ይህ እርምጃ ለሳውዲ አረቢያ ውጤት የሚያስገኝ አይሆንም ይላሉ ።
«ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ያለአንዳች ጥርጥር ያላቸው ግትር አቋምና ነቀፌታ እድገትንም ሆነ ነፃነትን የሚያስገኝ አይደለም ።ስለሆነም የሃሳብና የኪነ ጥበብ ነፃነት በተጨማሪም ፕሬሱ በዴሞክራሲያዊ ህገ መንግሥት በሚተዳደሩ ማህበረሰቦች የኑሮ ሁኔታ ላይ እጅግ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ አላቸው ።»
ዩንተር በበደዊ የደረሰው በሳውዲ አረቢያ ነፃነታቸው ከሚጣስባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አንዱ መሆኑን ያናገራሉ ።ዩንተር እንዳሉት የበዳዊ ጠበቃ ዋሊድ አቡልክህየርን ጨምሮ የሳውዲ ባለሥልጣናት በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን አስረዋል ።አቡልክህየር 15 ዓመት ተፍርዶበት ወህኒ ነው ያለው። ይህ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ ውይይት ሊካሄድበት የሚገባ መሆኑ ይታመናል ። ይሁንና ዩንተርም ሆነ ሌሎች በዚህ ረገድ የጀርመን መንግስት የኤኮኖሚም ሆነ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራው ቡድን ላይ የሚካሄደው ውጊያ አጋር የሆነችውን ሳውዲ አረቢያን ላለመጣት የተለሳለሰ አቋም በማራመድ ይተቻሉ ።በጀርመን ፓርላማ የግራዎቹ ፓርቲ የሰብዓዊ መብት ፖለቲካ ጉዳዮች ቃል አቀባይ አኔተ ግሮ በሰጡት አስተያየት የጀርመን መንግሥት ከአካባቢው ሃገራት እጅግ ኋላቀር ኢ ዲሞክራሲያዊ ና ለአሸባሪዎችም ዋነኛ የገንዘብ ድጋፍ ሰጭ ያሉትን የሳውዲን መንግሥት ነው የሚደግፈው ሲሉ ተችተዋል ።

Demo gegen die Auspeitschung des Bloggers Raif Badawi in Den Haag
ምስል Beekman/AFP/Getty Images

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ