1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡሩንዲ ፕሬዚደንት 100ኛ የሥራ ቀን

ሐሙስ፣ መስከረም 14 2013

ከሦስት ወራት በፊት ሥልጣን የያዙት የቡሩንዲ ፕሬዚደንት  ኤቫስት ኤንዳዬሺሚዬ እስካሁን ድረስ በሀገሪቱ ይኽ ነው የተባለ ለውጥ እንዳላመጡ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ቃል የተገባው ለውጥ እንዲኖርም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይፈልጋል።

https://p.dw.com/p/3iuAa
Burundi Präsident Evariste Ndayishimiye
ምስል Tchandrou Nitaga/AFP

«ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ነኝ»

የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ኤቫሪስት ኤንዳዬሺሚዬ ባለፈው ዓመት ሰኔ 11 ቀን ነበር የቡሩንዲ አዲሱ ርእሰ ብሔር ኾነው የተመረጡት። ፕሬዚደንቱ ባለፉት 100 ግድም የሥራ ቆይታቸው ይኽ ነው የተባለ ለውጥ እንዳላመጡ ስለ ብሩንዲ በቅርበት የሚያውቊ ይናገራሉ። የፓሪዘር ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተቋም የቀድሞ ባልደረባ እና የቡሩንዲ ጉዳይ ዐዋቂ ለኾኑት ቲዬሪ ቪርኩሎ ፕሬዚደንቱ እስካሁን ከተገበሯቸው ድርጊቶች ሊጠቀስላቸው የሚችለው አንዱ ርምጃ ብቻ ነው።
«ፕሬዚደንቱ እስካሁን ከተገበሯቸው ለውጦች በእውነቱ ሊጠቀስ የሚችለው የኮሮና ተሐዋሲን ለመከላከል የወሰዱት ርምጃ ብቻ ነው። ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ በፊት የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ጉዳይ አጨቃጫቂ ነበር። ወረርሽኙ በሀገሪቱ አልተከሰተም የሚሉም ነበሩ። ኤቫሪስት ኤንዳዬሺሚዬ ግን ያን ቀይረዋል። መንበረ-ሥልጣን በጨበጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጸረ-ኮሮና ተሐዋሲ ዘመቻ በአገሪቱ አስጀምረዋል። ይህ ዘመቻ የጀመረው በዋና ከተማዋ ነበር። ከዚያም  በሀገሪቱ የተለያዩ አውራጃዎች ተተግብሯል። በተሐዋሲው የተጠቊ ሰዎች አኹን ምርመራ ይደረግላቸዋል። እንግዲህ ፕሬዚደንቱ ቡሩንዲ ውስጥ ከተመረጡበት ጊዜ አንስቶ አንድ ይኽ ነው የሚባል ያደረጉት ነገር ቢኖር ይኸው ዘመቻ ነው።»

የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ኤቫሪስት ኤንዳዬሺሚዬ
የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ኤቫሪስት ኤንዳዬሺሚዬምስል Evrard Ngendakumana/Xinhua/Imago Images

ባለፈው ዓመት ሰኔ 1 ቀን፣ በድንገት ያረፉት የቡሩንዲ የቀድሞ ፕሬዚደንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ የኮሮና ተሐዋሲ እና የወረርሽኙ ሥርጭት ለመኖሩ ከሚጠራጠሩት ውስጥ ዋነኛው ነበሩ።  በእርግጥ የኅልፈታቸው ሰበቡ እበይፋ ሲነገር የልብ ኅመም ነው ቢባልም፤ እንደባለቤታቸው ኹሉ እሳቸውም በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተው ነበር የሚሉ አሉ። 

አዲሱ ፕሬዚደንት በተቃራኒው ወረርሽኙን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለመከላከል የወሰዱት ርምጃ ይጠቀስላቸዋል። ኮሮናን «የቡሩንዲ ቀንደኛ ጠላት» በማለትም ነበር ከቀዳሚያቸው ፕሬዚዳንት በተቃራኒው ዘመቻ የከፈቱት። ከዚያ ባሻገር ግን የቀድሞው ጄኔራል በፕሬዚደንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ሥልጣን ዘመን 

«ኤቫሪስት ኤንዳዬሺሚዬ ለዓመታት በቀድሞው መንግሥት አባልነት ሠርተዋል።  የዲሞክራሲ ኃይላት ተከላካይ ብሔራዊ ምክር ቤት (CNDD-FDD) ፓርቲን በቅርብም በሩቅም ኾነው አገልግለዋል። የፒዬር ንኩሩንዚዛ ጨቋኝ መንግሥት የፖለቲካ አገዛዝን ደግፈዋል፤ አብረው ሠርተዋል። ይኽ የፖለቲካ አገዛዝ በቀደመው መንግሥት የነበረ፤ አኹንም ሳይቀየር እንደቀድሞ የቀጠለ ነው።»

የዲሞክራሲ ኃይላት ተከላካይ ብሔራዊ ምክር ቤት (CNDD-FDD) ፓርቲ ደጋፊዎች
የዲሞክራሲ ኃይላት ተከላካይ ብሔራዊ ምክር ቤት (CNDD-FDD) ፓርቲ ደጋፊዎች ምስል AFP/Getty Images

የሰብአዊ መብት ጥሰት ቡሩንዲ ውስጥ ከቀድሞው አገዛዝ የአኹኑ የተቀየረ ነገር እንደሌለ ተንታኞች ይናገራሉ። መቀመጫውን ብራስልስ ውስጥ ባደረገው ግሪፕ (GRIP) የተሰኘው ተቋም የግጭቶ ተንታኙ ዦን ዣክ ዎንዶ ዖማንዩንዱ በአዲሱ መንግስት ለውጥ አልመጣም ብለዋል።

«ኤቫሪስት ኤንዳዬሺሚዬ በሀገሪቱ የሚታየውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስተካከል በእውነቱ ፍላጎት እንዳላቸው ዕውቅና መስጠት ያሻል። ለተቺዎቻቸው ይኼን ነው የምለው።  በእርግጥም በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ የምር ለውጥ ያመጡ እንደኹ ለማየት ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ነኝ። እስከዚያ ድረስ ግን እንደ ዓለም አቀፍ ታዛቢ ነገሮችን እጅግ በጥርጣሬ መከታተል ያሻል። ኤቫሪስት ኤንዳዬሺሚዬ ከተቃዋሚዎቻቸው በተለይ ምን ተጨባጭ ርምጃ ይወስዳሉ የሚለውን መከታተል ያስፈልጋል። እናም ክትትሉ ፖለቲካቸውን ለዲሞክራሲ ክፍት ያደርጉ እንደኹ ማየቱ ላይ ነው።» 

የብሩንዲ ደተኞች በጎረቤት ታንዛኒያ
የብሩንዲ ደተኞች በጎረቤት ታንዛኒያምስል Tchandrou Nitaga/AFP/Getty Images

ፕሬዚደንት ኤቫሪስት ኤንዳዬሺሚዬ በሀገሪቱ ከልብ የኾነ አስቸኳይ እርቀ ሰላም እንዲወርድ፤ ጥፋተኞችም የእጃቸውን የሚያገኙበት የፍርድ ሒደት እንዲቀላጠፍ መፈለጋቸውን ዐሳውቀዋል። ከሳቸው ቀደም ሲል የነበሩት ፕሬዚደንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ከሀገሪቱ ሕገ መንግሥት በተጻራሪ ለሦስተኛ ዙር የሥልጣን ዘመናቸው ለመወዳደር መነሳታቸው በብሩንዲ ብጥብጥ እና ኹከት እንዲነግስ አድርጎ ነበር። 

ላለፉት አምስት ዓመታት በሀገሪቱ በተከሰተው ቀውስ የተነሳም እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ 1,700 ሰዎች ተገድለዋል። ከ338.000 በላይ ብሩንዲያውያንም ወደ ጎረቤት ሃገራት ለስደት ተዳርገዋል። ይኽ ሁሉ ውጥንቅጥ በአዲሱ የብሩንዲ ፕሬዚደንት ኤቫሪስት ኤንዳዬሺሚዬ ዘመነ ሥልጣን ይሻሻል ይኾናል ሲል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተስፋ አድርጓል።  

አንቶኒዮ ካሽካሽ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ