1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን ሀያ ጉባኤ እና አፍሪቃ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 5 2009

ቡድን 20 በመባል የሚታወቀው በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ጠንካራ ኤኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ስብስብ የዘንድሮ ጉባኤ አስተናጋጅ ጀርመን በአጋጣሚው ለአፍሪቃ ተጨማሪ እርዳታ ለማስገኘት እንደምትጥር አስታውቃለች ።ይሁን እና ጉባኤው የሚካሄድበት ጊዜ እየተቃረበ ቢሆንም እስካሁን ይህን ማሳካት የሚያስችል በቅጡ የተቀናጀ የጋራ ስልት አልቀረበም።

https://p.dw.com/p/2bDcV
Deutschland EineWelt-Zukunftsforum Entwicklungsminister Gerd Müller und Angela Merkel
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

G20 Afrika - MP3-Stereo

 

የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ጌርድ ምዩለር ጥድፍያ ላይ ናቸው ። ሚኒስትሩ በርሊን በተካሄደው  አፍሪቃ ውስጥ የሚሰሩ የጀርመን ኩባንያዎች ማህበር  እና የቬስተርቬለ ተቋም ባዘጋጁት የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ ያተኮረ ጉባኤ ላይ እንግዳ ነበሩ ። ምዩለር በጎርጎሮሳዊው 2017ን ጀርመን በአፍሪቃ ላይ ለማተኮር በማቀዷ ደስተኛ ናቸው ። በአፍሪቃ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ የጀርመን ባለሀብቶች

« 2017 ለአፍሪቃ ትኩረት የሚሰጥበት ዓመት በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ። አፍሪቃ በዓመቱ ትኩረት እንዲሰጣት ማድረጉ ስለተሳካልን ተደስቻለሁ ። እዚህ ሰፊ ድጋፍ አለን ። የፌደራል የገንዘብ ሚኒስትር ከኔ ጋር ናይሮቢ የነበሩት የፌደራል የኤኮኖሚ ሚኒስትር እንዲሁም አሁን ደግሞ አፍሪቃን ዋነ ኛ አጀንዳ ማድረግ የሚፈልጉት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ድጋፍ አግኝተናል ።»

Deutschland | G20 Finanzminister Gipfel in Baden-Baden
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

ጀርመን ለአፍሪቃ ትኩረት እሰጣለሁ ባለችበት በ2017 በፕሬዝዳንትነት በምትመራው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ማሰባሰብ ትፈልጋለች ። የተለያዩ የጀርመን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ይህን ማሳካት ያስችላሉ ያሏቸውን የተለያዩ ሀሳቦች አቅርበዋል አንዳንዶቹም እያዘጋጁ ነው  ። የልማት ተራድኦ ሚኒስትሩ ምዩለር ለዚሁ ዓላማ ይረዳል ያሉትን «የአፍሪቃ የማርሻል እቅድ» የሚል ስያሜ የሰጡትን ሀሳብ አቅርበዋል ። የጀርመን የገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ ከሌሎቹ የቡድን ሀያ አባል ሀገራት ጋር «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ» የሚል ስያሜ የሰጡትን ሀሳብ እያዳበረ ነው ። ባለፈው ታህሳስ የጀርመን የልማት እና የኤኮኖሚ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣በአፍሪቃ ተጨማሪ ንግድ እና የመዋዕለ ንፋይ ፍሰት ለማካሄድ የጋራ ስልት ያቀፈ ሰነድ አቅርበዋል ። በማይንዝ እና በላይፕሲሽ ዩኒቨርስቲዎች የአፍሪቃ ጉዳዮች አጥኚ ሄልሙት አሼ  የጀርመን መንግሥት ለአፍሪቃ ትኩረት ለመስጠት የፈለገበትን አዲሱን  እንቅስቃሴ አድንቀዋል ሆኖም መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ ይላሉ ።

«ሀሳቡ በጣም ትልቅ ነገር ነው።በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች መካከል የተሻለ ሊኖር የሚገባው ቅንጅት የተሻለ ሊሆን ይችል እንደነበረ የአደባባይ ሚስጥር ነው።ይህን አፍሪቃውያን አጋሮቻችንም አላጡትም »

አሼ እንደሚሉት ሚኒስትሮቹ አሁን ይህን እየተገነዘቡ መጥተዋል ። ሆኖም እስካሁን  ከጀርመን ፌደራል መንግሥት በኩል ለቡድን ሀያ የሚቀርብ አንድ የተቀናጀ የጋራ ስልት ይጎድላል ። የማርሻል እቅድንም ሆነ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ በተባሉት ሀሳቦች ላይም መልስ ያላገኙ ብዙ ጥያቄዎች አሉ ።ለምሳሌ ለሁለቱ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገው ገንዘብ እንዴት ሥራ ላይ የሚውለው የሚለew ግልጽ አይደለም ። የቡድን 20 የገንዘብ ሚኒስትሮች በቅርቡ ባካሄዱት ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የወጡት መግለጫ ዓላማው ተለይተው በተመረጡ የአፍሪቃ ሀገራት የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ይበልጥ ማስፋፋት መሆኑ ተገልጿል ። ይሁን እና የጀርመን ፌደራል መንግሥት ጊዜው እያለቀበት ነው ።የተቀናጀው ስልት እስከ መጪው በጋ መጠናቀቅ አለበት ። አፍሪቃ ላይ ያተኮረው የቡድን ሀያ ጉባኤ በርሊን ውስጥ በሰኔ ወር ነው የሚካሄደው ። የቡድን ሀያ አባል ሀገራት የመራህያነ መንግሥታት እና የርዕሳነ ብሔራት ጉባኤ ደግሞ ሐምሌ ውስጥ በሀምቡርግ ያካሄዳል ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ጀርመን ውስጥ የምርጫ ዘመቻ ይጀመራል። ከመስከረሙ የጀርመን የምክር ቤት ምርጫ በኋላ ደግሞ ሪ,አዲስ መንግሥት ምሥረታ ድርድር ይጀመራል ። እናም የጀርመን ፌደራል መንግሥት በተፈላጊው ጊዜ አፍሪቃ ላይ ያተኮረ አንድ የጋራ ሀሳብ ይዞ መቅረብ መቻሉ እያጠያየቀ ነው። አሼ ይህ መሳካቱን ይጠራጠራሉ ሆኖም መንግሥት ሳናስበው አሳክቶ ሊያስደምምመንም ይችል ይሆናል ብለዋል ። ክሪስቶፍ ካነንጊሰር አፍሪቃ ውስጥ የሚሰሩ የጀርመን ኩባንያዎች ማህበር ሊቀ መንበር ደግሞ ወደ ተግባራዊው እንቅስቃሴ እንዲገባ ያሳስባሉ

Volkswagen in Südafrika
ምስል picture-alliance/dpa

«የጀርመን ፊደራል መንግሥት አፍሪቃን ዋነኛ አጀንዳው እንደሚያደርግ ማስታወቁ በራሱ ያሳደረው ተጽእኖ አለ ። አሁን መሆን ያለበት ጉዳዩ ከዐርዕስተ ዜናነት አልፎ ተጨባጭ ነገሮች የሚታዩበት እንዲሆን  ማድረግ ነው ።»

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ