1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በርሊን፤ የቡድን 20 እና የአፍሪቃ ጉባኤ ተጀመረ

ሰኞ፣ ሰኔ 5 2009

ድህነት እና የስደተኞችን ፍለሰት ለመቀነስ ያለመዉ የቡድን ሃያ ሃገራትና የአፍሪቃ ሃገራት ጉባኤ ዛሬ በጀርመንዋ ዋና መዲና በርሊን ተጀመረ። የጉባኤዉ ዋና አላማ ማሻሻያዎች ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ የአፍሪቃ ሃገራት እና በዓለም ትልቅ ኤኮኖሚ ያላቸዉ ሃገራት በመተባበር፤ የግል ባለሃብቶች ንግድና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ነዉ።

https://p.dw.com/p/2eYOd
Deutschland G20 Afrika Treffen
ምስል Getty Images/AFP/J. Macdougall

xxxxxxM M T / Q & A- (G20 Africa Partnership meeting)- Berlin - MP3-Stereo

 እንዲያም ሆኖ አብዛኛዉን ጊዜ በአህጉሪቱ የሚታየዉ አለመረጋጋት እና ሙስና የዉጭ ኩባንያዎችን እንደሚያሰጋቸዉ ነዉ የተገለጸዉ። ጉባኤዉን የሚያስተናግዱት የቡድን ሃያ የወቅቱ ፕሬዝደንት የሆነችዉ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ቀደም ሲል በአፍሪቃ የተለያዩ ሃገራት ጉብንት ባደረጉበት ወቅት የተረጋጋች አፍሪቃ ለጀርመን ወሳኝ ተጓዳኝ እንደምትሆን ማሳሰባቸዉ ይታወሳል። የአፍሪቃ የልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪኒዋሚ አዴሲና የበለፀጉት ሃገራት ለአፍሪቃ ትኩረት መስጠታቸዉ አስደስቷቸዋል፤

« ተደስቻለሁ ምክንያቱም ይህ ማለት ቡድን ሃያ አፍሪቃን በተለየ አተያይ መመልከት ጀምሯል። አፍሪቃን ይመለከት የነበረዉ ከልማት አኳያ ብቻ ነበር፤ ይህም በእርግጥ ጠቃሚ ነዉ። ነገር  ግን አሁን አፍሪቃን የሚያይበት አተያይ ወረትን ከመወረት አኳያ ነዉ፤ ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ የአመለካከት ለዉጥ ነዉ። ይህ የአመለካከት ለዉጥ ለምን በጣም አስፈላጊ ሆነ? አፍሪቃ ዉስጥ እየሆነ ላለዉ ነገር ምላሽ በመሆኑ ነዉ።»

እሳቸዉ ይህን ይበሉ እንጂ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከአፍሪቃ፤ ደቡብ አፍሪቃ ብቻ በአባልነት የምትገኝበት ቡድን ሃያ፤ ለአህጉሩ ያን ያህል ትልቅ የሚባል የገንዘብ ድጋፍ ባለማቅረብ፤ እና ዓለም አቀፍ ንግድ የሚባለዉም የአፍሪቃን ገበሬዎች እና አምራቾች ይጎዳል በሚል ይተቻሉ። ዛሬ በርሊን ላይ በተጀመረዉ ጉባኤ እንዲገኙ የተጋበዙት የግብጽ፣ የጋና፣ የኮትዴቩዋር፣ የማሊ፣ ኒዠር፣ የሩዋንዳ፣ ሴኔጋል እና ቱኒዚያ መሪዎች ሲሆኑ፤ የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የአፍሪቃ ኅብረት ኃላፊዎችም እንደሚገኙ የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘገባ ያመለክታል። ጉባኤዉ እስከ ነገ ይዘልቃል።

Deutschland G20 Afrika Treffen
ምስል picture-alliance/dpa/K. Nietfeld

ጀርመን በመጪው ሰኔ 30 እና ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም በሐምቡርግ ከተማ የሚካሄደውን የቡድን 20 ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው፡፡ ለጉባኤ መንደርደሪያ ነው የተባለ አፍሪካ ላይ ያተኮረ የሁለት ቀን ስብሰባ ዛሬ በርሊን ከተማ ላይ ተጀምሯል፡፡  የበለጸጉ ሀገራት ስብስብ የሆነው ቡድን 20 በአፍሪካ የውጭ የግል መዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ለማበረታት እና የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር የነደፈው አዲስ እቅድ በዛሬው ስብሰባ ላይ መነጋገሪያ ይሆናል ተብሏል፡፡ በዛሬው ስብሰባ ላይ የግብጽ እና የጊኒ ፕሬዝዳንቶች እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡ በስብሰባው ስለሚነሱ አንኳር ጉዳዮች እና ስለጀርመን አቋም የበርሊኑ ወኪላችንን ይልማ ኃይለሚካኤልን አነጋግሬው ነበር፡፡ 

ይልማ ኃይለሚካኤልን

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ