1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን ሃያ-ጉባኤና አፍሪቃ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 22 2001

ባንድ በኩል የበለፀገዉ አለም የሚሰጠዉ ርዳታ በመቀነሱ-ወይም ይቀንሳል በመባሉ፥ በሌላ በኩል የሽቆጦች ዋጋ በመርከሱ ወትሮም በምቧሁ የሚድኸዉን የአፍሪቃን ምጣኔ-ሐብት ባፍጢሙ እንዳይደፋዉ ነዉ-ጭንቁ

https://p.dw.com/p/HNfe
የቡድን 20 አርማምስል AP / CC_Marcin n_nc

ለንደን-ብሪታንያ ላይ የሚሰየመዉ የቡድን ሃያ-አባል ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ክፉኛ የከሰረዉ የአለም ምጣኔ ሐብት የሚያንሰራራበትን ዉሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።ሐሙስ የሚሰበሰቡት የሃያዎቹ ሐገራት መሪዎች በምጣኔ ሐብቱ ኪሳራ ድርብ ጉዳት የደረሰባት አፍሪቃን እንዳይዘነጓት የተለያዩ ወገኖች እየጠየቁ ነዉ።የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች፥የርዳታ ድርጅቶችና የአለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች እንደሚሉት የምጣኔ ሐብቱ ኪሳራ ወትሮም ያልጠናዉን የአፍሪቃን ልማት እያወከዉ ነዉ።የዶቸ ቬለዋ ኡተ ሼፈር እንደፃፈችዉ በአፍሪቃ ባለፉት ጥቂት አመታት የታየዉ የልማት-ብልፅግና ጅምር ገና ካሁኑ እያሽቆለቆለ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ አሰባስቦታል።

ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ሲያገኙ ለነበሩት አንጎላና ናይጄሪያን ለመሳሰሉት ሐገራት «ወፍራም« ገቢያቸዉ የትዝታ ያክል እየረቀ ነዉ።ነዳጅ-ዘይት ረከሰ፥እድገታቸዉም ቀረ።በማዕድን ሐብት የበለፀገችዉ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የሐብቷ እዉነተኛ ተጠቃሚ ለመሆን ሠላም ለማስፈን ደፋ ቀና ስትል-የዉጪ ባለሐብቶች የሚሳተፉባቸዉ 48 የማዕድን ጉርጓዶች-አፋቸዉን ከፍተዉ ቀሩ።-የእርሻ ምርቱ ሻጭ ሐገራት ኪሳራ ደግሞ ከነዳጅ-ማዕድኑ የባሳ ነዉ።
ባንድ በኩል የበለፀገዉ አለም የሚሰጠዉ ርዳታ በመቀነሱ-ወይም ይቀንሳል በመባሉ፥ በሌላ በኩል የሽቆጦች ዋጋ በመርከሱ ወትሮም በምቧሁ የሚድኸዉን የአፍሪቃን ምጣኔ-ሐብት ባፍጢሙ እንዳይደፋዉ ነዉ-ጭንቁ።ባለፉት ጥቂት አመታት የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት በአመት ባማካኝ እስከ ስድስት በመቶ እድገት አሳይቶ ነበር።የአለም የገንዘብ ድርጅት (IMF-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) እንደሚለዉ ቻይና፥ ብራዚልና ሕንድን የመሳሰሉት አዳዲስ ባለፀጎች አፍሪቃን መቃኘት ከጀመሩ ጀምሮ አፍሪቃ ዉስጥ የሚወረተዉ የዉጪ ሐብት መጠን በቅርቡ 53 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር።
ይሕ የወረት መጠን በ1992 ከነበረዉ ጋር ሲነፃፀር በአምስት እጥፍ-መቻረሩን ይነግረናል-IMF። የአፍሪቃ ልማት ባንክ ሐላፊ ዶናልድ ካቤሩካ እንደሚሉት የልማት ወረቱ ያፍታ እድገት በቅፅበት የቁል ቁሊት እየተንደረደረ ነዉ።
«የገንዘብና የምጣኔ ሐብት ቁዉሱን ነጣጥለን ማየት አለበን።እስካሁን ድረስ አንድም የአፍሪቃ ባንክ አልከሰረም።ምጣኔ ሐብቱ ግን ተቃዉሷል።የ2009 ኙ አማካይ እድገት በጣም ቢበዛ 4 እና 4.5 ይሆናል ብለን እንጠብቃለን።በቃ።ይሕም ራሱ ሊቀንስ ይችላል።»
ካቤሩክ እንደሚሉት በአፍሪቃ ሐገራትም መካካል ሐብታምና ዶሆች አሉ።በድሆቹ ላይ አለቅጥ የበዛዉን ችግር ለማቃለል ባንካቸዉ ካፒታልን ካንዱ የአፍሪቃ ሐገር ወደ ሌላዉ ማገለበጥን እንደ አንድ መፍትሔ ያየዋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሐ-ግብር ምክትል ዋና ፀሐፊ ኤዲ ሜልኬርት እንደሚሉት ደግሞ የቡድን ሃያ ጉባኤተኞች የአፍሪቃን ድርብ ችግር በቅጡ ሊያጤኑት ይገባል።
«አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለሌላ ትልቅ ጉባኤ ለቡድን ሃያ ለንደን ሲሰበሰብ፥ የሚነጋገርበት አለም አቀፍ ጉዳይ አፍሪቃን የሚያጠቃልል መሆን እንዳለበት ሊያረጋግጥ ይገባል።ምክንያቱም ቀዉሱ አለም አቀፍ በመሆኑ መፍትሔዉም አለም አቀፋዊ መሆን አለበት።»
እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር እስከ 2015 ባለዉ ጊዜ ድሕነት፥ ማይምነትንና በሽታን በግማሽ ለመቀነስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቀደዉ የአመአቱ ግብ ገቢራዊነት ወትሮም አጠራጣሪ ነበር።የበለፁጉት ሐገራት በራሳቸዉ የምጣኔ-ሐብት ቀዉስ በመጠመዳቸዉ የሚሰጡትን ወይም ለመስጠት ቃል የገቡትን ድጋፍ ይቀንሳሉ መባሉ ወትሮም ያላማረበትን እቅድ ጨርሶ እንዳያዉከዉ እያሰጋ ነዉ።
የአለም አቀፉ ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ ሜልኬርት ግን ከአመአቱ ግብ የተሻላ አማራጭ የለም ይላሉ።የለንደኑ ጉባኤም ይሕን ያጤነዋል-የሚል ተስፋ አላቸዉ።
«ትላልቆቹ፥ ሐብታሞቹ ሐገራት በለንደን የቡድን ሃያ ጉባኤ ጠቃሚ ዉይይት ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለኝ። አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ አሜሪካ ተጨማሪ ድጋፍ እንድትሰጥ ተገቢዉን ይወስናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።የአዉሮጳ ሐገራት የሚሰጡትን የልማት እርዳታ ለማሳደግ የገቡትን ቃል ያከብራሉ የሚል ተስፋ አለኝ።»
የጉባኤዉ አስተናጋጅ የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራዉን በቅርቡ የአፍሪቃ መሪዎችን አነጋግረዋል።እና ሌላ ተስፋ።