1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን ሃያ ጉባኤና አፍሪቃ

ሐሙስ፣ መጋቢት 24 2001

የበለፀገዉ አለም ለአፍሪቃ ከአንድ ትሪ ሊዮን ዶላር የሚበልጥ ርዳታ ሰጥቷል። ርዳታዉ ግን እንደሚሉት ለአሐጉሪቱ ብዙም አልፈየደም። እንዲያዉም በተቀራኒዉ የአፍሪቃዉያንን የመስራትና የተነሳሽነት ስሜትን እያሽመደመደዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/HOya
የቡድን ሃያ ጉባኤተኞችምስል AP

ዛሬ ለንደን ብሪታንያ የተሰየመዉ የቡድን ሃያ ጉባኤ የአለም ምጣኔ ሐብትን ከኪሳራ ለማዉጣት ሲመክር በኪሳራዉ ድርብ ችግር የገጠማቸዉ የአፍሪቃ ሐገራት እንዳይዘነጉ የሚደረገዉ ጥሪና ጥያቄ እንደቀጠለ ነዉ።ለአፍሪቃ ልማት አዲስ ተሻራኪነት በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ NEPAD የተሰኘዉ ተቋም የወቅቱ ሊቀመንበር የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዉ ከጉባኤዉ ጎን በሚደረግ ዉይይት ላይ እንዲካፈሉ ቢጋበዙም በዋናዉ ጉባኤ የምትሳተፈዉ አፍሪቃዊት ሐገር ደቡብ አፍሪቃ ብቻ ናት።አፍሪቃ በቂ ዉክልና በማጣትዋ እንዳትዘነጋ የሚጠይቁት ወገኖች ሐብታሞቹ ሐገራት የገቡትን የርዳታ ቃል እንዳያጥፉም እያሳሰቡ ነዉ።አንዳድ አፍሪቃዉያን ግን እርዳታ አያስፈልግም ይላሉ።ማርክ ኤንገልሐርት የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደገመተዉ በያዝነዉ የአዉሮጳዉያን አመት ከሚሰጠዉ የልማት ርዳታ ብቻ በትንሹ አራት ቢሊዮን ዶላር ተኩል ይቀነሳል።በቡድን ሃያ-ጉባኤ ከአፍሪቃ የተወከለችዉ ደቡብ አፍሪቃ እርዳታዉ ሲሆን እንዲጨመር ይሕ ቢቀር እንዳይቀንስ-ከፍተኛ ግፊት እያደረገች ነዉ።በኬንያ የብሪታንያዉ ግብረ-ሠናይ ድርጅት የኦክስፋም ተጠሪ ማይክል ኦ ብሪያ እንደሚሉት ደግሞ ድርጅታቸዉና ብጤዎቹ የበለፀገ አለም የገባዉን የርዳታ ቃል ማጠፍ የለበትም የሚል አቋም አላቸዉ።

Kgalema Motlanthe, Präsident von Südafrika
በዋናዉ ጉባኤ የተካፈሉት ብቸኛዉ የአፍሪቃ መሪ-ሙትላንቴምስል picture-alliance / dpa

«ከአጠቃላይ አመታዊ ሐገራዊ ገቢያቸዉ 0.7 በመቶዉን ለመርዳት የገቡትን ቃል ማክበር አለባቸዉ።ይሕ ከአመታት በፊት የተገባ ቃል ነዉ።የአፍሪቃ ሐገራት እነዚሕን ርዳታዎች አሁን ይፈልጓቸዋል።»

አንዳድ አፍሪቃዉያን የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች ግን የእስካሁኑ የለጋሽ-ተለጋሾች ግንኙነት ሥልት ሒደት መበጠስ አለበት ይላሉ።አለምን የገጠመዉ የምጣኔ ሐብት ኪሳራ አፍሪቃን ከዉጪ ርዳታና ድጋፍ ጥገኛነት ለማላቀቅ ጥሩ አጋጣሚ ነዉ ብለዉም ያምናሉ።ኬንያዊዉ የምጣኔ ሐብት አዋቂ ጄምስ ሺክዋቲ ከነዚሕ አንዱ ናቸዉ።እሳቸዉ እንደሚሉት ርዳታ አፍሪቃዉያን በሁለት እግራቸዉ እንዳይቆሙ እያሽመደመዳቸዉ ነዉ።

«መርዳት-ቃሉ ክፋት የለዉም።ክፋቱ የርዳታዉ ዉጤትና መዘዝ ነዉ።በተለይ የርዳታ አሰጣቱ ሥልት ተረጂዎችን ወደ ከፋ ድሕነት መግፋቱ ሲታወቅ፥ የምንቃወመዉ ሥልቱን ነዉ።መርዳቱን አይደለም።የሚረዳዉ ወገን ለችግር የተጋለጠበትን መሠረታዊ ምክንያት ሳታስወግድለት ርዳታ ብቻ የምትሰጠዉ ከሆነ ለዘላለም እርዳታ እንደሰጠሕ ትኖራለሕ።እና በረጅም ጊዜ የኛ የአፍሪቃዉያን አይነት ሕዝብ ትፈጥራለሕ።ችግራችዉን ራሳቸዉ መፍታት አይችሉም ተብለዉ-የሚታሰቡ፥ እራሳቸዉም የሚያሰቡ ሰዎችን።»

ሺክዋቴ እንደሚሉት አፍሪቃ ምጣኔ ሐብቷን በራስዋ ለመምራት በቂ ቅምጥ ሐብት አላት።ባለፉት ሐምሳ አመታት የበለፀገዉ አለም ለአፍሪቃ ከአንድ ትሪ ሊዮን ዶላር የሚበልጥ ርዳታ ሰጥቷል። ርዳታዉ ግን ሺክዋቴና የአስተሳሰብ ተጋሪዎቻቸዉ እንደሚሉት ለአሐጉሪቱ ብዙም አልፈየደም። እንዲያዉም በተቀራኒዉ የአፍሪቃዉያንን የመስራትና የተነሳሽነት ስሜትን እያሽመደመደዉ ነዉ።

ኬንያ ዉስጥ አመቱን በሽያጭ ተወዳዳሪ ያልተገኘለትን «ማንም መክበር ይችላል» የተባለዉን መፅሐፍ ያሳተሙት የአክስዮን ገበያ አዋቂ አልይ-ካሕን ሳትቹ በበኩላቸዉ አፍሪቃን ከድሕነት ማዉጣት የሚችሉት ራሳቸዉን አፍሪቃዉያን ብቻ ናቸዉ ይላሉ።

«አፍሪቃዉያን በተፈጥሯቸዉ ነጋዴዎች ናቸዉ።በየሥፍራዉ ገበያ አላቸዉ።ሁሉም የዋጋን ምንነት ያዉቃሉ።የመሽጥ-መለወጥ፥ መግዛትን ሥልት ይረዱታል።የሚያስፈልጋቸዉ የእድሉ መመቻቸት ብቻ ነዉ።»

ሳትቹ እንደሚያምኑት ባለኢንዲስትሪዎቹ ሐገራት የገንዘብ ቀዉሱን ለማስወገድ የሆነ የማርሻል እቅድ አይነት መርሕ ለአለም ማዉጣት ነዉ-የሚጠበቅባቸዉ።የተቀረዉን ግን አፍሪቃ ብቻዋን ትወጣዋለች። የልማት ርዳታዉን የማይቀበሉት ሺክዋቲና ብጤዎቻቸዉ ሳይቀሩ አፍሪቃ ረሐብ፥ በሽታ፥፥ሙስና የባለሙያ እጥረት ቀይዶ እንደያዛት ያምናሉ።አብነቱ ግን ይላሉ፥ ሥለችግሩ ማሰብ ሳይሆን ከችግር መዉጣት የመቻል አጋጣ መኖሩን ማሰብ-መጠቀም ነዉ።

Premierminister Zenawi Meles von Äthiopien
ከጉባኤዉ ጎን በሚደረገዉ ዉይይት የተካፈሉት የኢትዮጵያ ጠሚና የኔፓድ ሊቀመንበር መለስምስል AP Photo

«የቡድን ሃያ ይሁን፥ የቡድን ሥምንት ስብሰባ በተደረገ ቁጥር ተመሳሳይ ነገር ነዉ-የምንሰማዉ።ርዳታ፥ እርዳታ።እንደሚመስለኝ አፍሪቃ አሁን ማቶከር ያለባት የምጣኔ ሐብቱ ሥርዓት በአፍሪቃ ራስዋን የማልማት አቅም ላይ ያሳደረዉን ተፅዕኖ በማጤኑ ላይ ነዉ።እኛ መጠበቅ ያለብን ደቡብ አፍሪቃ ግፊት ማድረግ አለባት ብዬ የማስበዉ፥ አፍሪቃዉያን በአለም ምጣኔ ሐብት በቀጥታ የሚሳተፉበት አዲስ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲፈጠር ነዉ።»

ሺክዋቴ የባለ ኢንዲስትሪዎችን ጥቅም ለማስከበር የቆመ የሚሉት የአለም ባንክን አፍሪቃ ራስዋን እንዳትችል ትልቅ እንቅፋት ነዉ-ይላሉ።የቡድን ሃያ ጉባኤ ለባንኩ ተጨማሪ ገንዘብ ይሰጥ የሚለዉን ሐሳብ ማስወገድ አለበት ባይ ናቸዉ።

ማርክ ኤገልሐርት/ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ፣

►◄