1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡድን ስምንት ጉባኤ ማጠቃለያ

ዓርብ፣ ግንቦት 19 2003

ተቃዉሞ ሠልፈኛዉ ወደ ጉባኤዉ ሥፍራ እንዳይጠጋ የጉባኤዉ አስተናጋጅ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒካላ ሳርኮዚ የዚያችን ትንሽ ከተማ ዙሪያ ገባ በአስራ-ሁለት ሺሕ ፀጥታ አስከባሪ ማግረዋት ነበር።

https://p.dw.com/p/RQXL
ጉባኤተኞችምስል AP

ዶቪል-ፈረንሳይ ዉስጥ ለሁለት ቀን የመከረዉ የቡድን ሥምንት አባል ሐገራት አመታዊ የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ምምሻዉን ተጠናቀቀ።መሪዎቹ ከሱዳን ግጭት እስከ እስራኤል-ፍልስጤሞች ድርድር፥ አለም አቀፍ ባሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።ወስነዋልም።የኑክሌር ሐይል አጠቃቀምን ለመለወጥ፥ የአለም ገንዘብ ድርጅት መሪን ለመሰየም ተነጋግረዋል።የሊቢያዉን መሪ ለማስወገድ ዝተዉ፥ ግብፅና ቱኒዝያን ለመርዳት፥ የአረብ ሐገራት ሕዝባዊ አመፅን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።

የሙዚቃዉ ከበርቻቻ፥ የጉባኤተኞቹ ሳቅ ፈገግታ፥ ቀልድ-ጨዋታ የጉባኤዉን ሒደት፥ የአለምን ጉዞም ከዉጊያ-ጦርነቱ፥ ከአመፅ-ግድያ ዉዝግቡ ገለል-ቀለል ዘና-ላላ ያለ አስመስሎት ነበር።«ቦንዡር» አሉ ጀርመናዊቷ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል-ፈረንሳዊዉን ፕሬዝዳት በፈረንሳይኛ።
«መልካም ቀን» ወይም «እንደምንዋሉ» እንደማለት።ቀኑ ለጉባኤተኞቹ በርግጥ መልካም ነበር።የማያግባባ የሚባል ርዕሥ ብዙ አልነበራቸዉም።የቡድን ስምንት ጉባኤ በተደረገ ቁጥር የጉባተኞችን መርሕ የሚቋወሙ፥የድሆችና የመብት ተሟጋቾች ሠልፍ ጫጫታ፥ ዉካታም ብዙ አልነበረዉም።

ተቃዉሞ ሠልፈኛዉ ወደ ጉባኤዉ ሥፍራ እንዳይጠጋ የጉባኤዉ አስተናጋጅ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኒካላ ሳርኮዚ የዚያችን ትንሽ ከተማ ዙሪያ ገባ በአስራ-ሁለት ሺሕ ፀጥታ አስከባሪ ማግረዋት ነበር።ሳቅ ፈግግታ፥ ሠላም-ፀጥታ፥መግባባት የሰፈነበት ጉባኤ ጦርነት እንዲፋፋም ተበየነበት።የጉባኤዉ አስተናጋጅ ይሕን አረጋገጡ።«ሚስተር ቃዛፊ ሥልጣን መልቀቅ አለባቸዉ።ሊቢያዉያን ለወደፊት ዲሞክራሲ የመመስረት መብት አለቸዉ።»የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ደግሞ ሐያላኑ የጀመሩትን ለመጨረስ ዉጊያ መቁረጣቸዉን አስታወቁ።

«የሊቢያዉ ዘመቻችን ጥሩ ዉጤት ማምጣቱ አግባብቶናል።ይሁንና ቃዛፊ ሊቢያ ሆነዉ ጦራቸዉን በሊቢያ ሕዝብ ላይ እስካዘመቱ ድረስ ሰላማዊ ሰዎች ከአደጋ እንዲጠበቁ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳለፈዉ ዉሳኔ ገቢራዊ ሊሆን አይችልም።እና የጀመርነዉን ለመጨረሽ ቆርጠናል።»

ደግሞ በተቃራኒዉ የተጫረ ዉጊያ ተወግዞበታል።ጉባኤተኞች ባወጡት የአቋም መግለጫ የሰሜን እና የደቡብ ሱዳን ሐይላት በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉን የአብዬ ግዛትን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ዉጊያና ግጭት ባስቸኳይ እንዲያቆሙ አሳስበዋል።ከስልሳ ዘመን በላይ የሚነገር-የሚወራለት የእስራኤልና የፍልስጤሞች የሠላም ድርድርም የሐያላኑ ሐገራት መነጋገሪያ ነበር።

NO FLASH G8-Gipfel Deauville
ምስል picture alliance/dpa

ይሁንና እንደከዚሕ ቀደሙ ሁሉ ሌሎች ዉይይት ዉሳኔዎችን ከማድመቂያነት ወይም አሉ ከማስባል ባለፍ እየተጀመረ የሚቀረዉ ድርድር-ዳግም ተጀምሮ እንዳይቀር የሚጠቁም ሐሳብ ጨርሶ አልነበረም።እንዲያዉም የፍልስጤሞችና የእስራኤል የወደፊት ድንበር እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ከ1967ቱ የአረብ-እስራኤል ጦርነት በፊት በነበረዉ ወሰን ላይ ይመስረት የሚለዉን ሐሳብ በይፋ መጥቀስ አልፈለጉም።
ጉባኤተኞች የፍልስጤሞች የነፃ ሐገር መንግሥትነት፥ተስፋ የሌላ ዘመን ሌላ ደብዛዛ ተስፋነት እንዳይጨልም ጠጠቀስ አድረገዉ የመዝለላቸዉ እኩል በአደባባይ አመፅ አምባገነን ገዢዎቹን ካስወገደዉ ከቱኒዚያና ከግብፅ ሕዝብ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።ለሁለቱ ሐገራት ሃያ ቢሊዮን ዶላር ለመርዳትም ቃል ገብተዋል።

ጉባኤተኞች የኑክሌር ሐይል የሚያደርሰዉን ጉዳት ለማስወገድ አማራጭ የሐይል ምንጭ የመፈለጉን ጥረት እንደሚያጠናክሩ ቃል ገብተዋል።ትናንት በደስታ ፌስታ የተጀመረዉ ጉባኤ ትናንትናዉኑ ከቤልግሬድ የሰማዉ ደስታዉን የሚያጠናክር ወይዘሮ አንጌላ ሜርክል እንዳሉት ደግሞ ለብዙዎች የምሥራች ብጤ ነበር።የቦስኒያዉ ተጠርጣሪ የጦር ወንጀለኛ ራድኮ ሚላጂች ታሰሩ።

«የምላጂች መያዝ አንድ ጠቃሚ እናም አስቸኳይ ርምጃ ነዉ።ምክንያቱም ባሁኑ ወቅት ግጭትና ዉጊያ ባሉባቸዉ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች የጦር ወንጀለኞች ሠላቦች በመሆናቸዉ።ከእንግዲሕ የፍርዱን ሒደት መከታተል በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት የዩጎዝላቪያ ችሎት ፈንታ ነዉ።ይሕን ብዙ በጣም ብዙ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ለመጠበቅ ተገድደዉ ነበር።ለዚሕም ነዉ የምላዲች መያዝ ጥሩ ዜና የሚሆነዉ።»

ፈረንሳይ ያስተናገደችዉ ጉባኤ፥ በሴት መድፈር የተከሰሱት ፈረንሳዊ የቀድሞ የአለም ገንዘብ ድርጅት ሐላፊ በፈረንሳዊት እንዲተካ ፍላጎቱን ገልጧል።ግን ያዉ ለዲፕሎማዊ ወግ ዉሳኔዉ የራሱ የአለም ገንዘብ ድርጅት ቦርድ ነዉ-ይላል የአቋም መግጫዉ።

G8 Gipfel in Deauville Frankreich
ኦባማና ሳርኮዚምስል dapd

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ