1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተጠናቀቀው ቡድን 20 ጉባኤ እና የገጠመው ተቃውሞ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 1 2009

በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለድሀ ሀገር ሴቶች፣ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጀርመኗን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን በማወደስ ነው የቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ሁለተኛ ቀኑን ዛሬ የጀመረው። ቡድኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ሰልፍም ገጥሞት ተጠናቋል።

https://p.dw.com/p/2gCHQ
G20 Gipfel in Hamburg | Trump & Merkel
ምስል Getty Images/U. Michael

ዛሬ በተጠናቀቀው የ ቡድን 20 ጉባኤ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሀገራቱ ጥሩ ውሳኔ ላይ በድረሳቸውን ገለፁ። ምንም እንኳን የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትን ቢቃወሙም ቀሪ የቡድን 20 ጉባኤ ተሳታፊ ሀገራት ስምምነቱ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። ሀገራቱ በመግለጫቸው "የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ሥምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ያለንን ጠንካራ ዝግጁነት እናረጋግጣለን"  ማለታቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በቡድን 20 ሀገራት ጉባኤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፓሪሱ ስምምነት መሰረት ሀገራቸው ግዴታዋን እንደምታከብር ተናግረዋል። 
ከዚህም ሌላ የቡድን 20 አባላቱ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ሴቶችን ለማበረታታት ተስማምተዋል። ለዚህም የሚውል በጠቅላላው 325 ሚሊዮን ዶላር መድበዋል። ጀርመን ሀምቡርግ ከተማ ትናንት በጀመረው እና ዛሬ በተጠናቀቀው ጉባኤ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ይህ ማበረታቻ በድሀ ሀገር ያሉ ሴቶች የወደፊት እጣ ፋንታቸውን ራሳቸው እንዲወስኑ ይረዳቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። ገንዘቡን የሚያቀርበው የዓለም ባንክ ይሆናል። ሜርክል ሌላው ወሳኙ ውይይት የአለም ንግድን የሚመለከተው ነበር ብለዋል።« ገበያዎች ነፃ መሆን እንዳለባቸው መነጋገራችን አስደስቶኛል። ፍትሀዊ ያልሆነ ንግድ እንዲቆም። በአለም የንግድ ድርጅቶች ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ሁሉም አባል ሀገራት ተስማምተዋል።»

በሌላ በኩል የ ቡድን 20 ጉባኤ ከመቼውም የበለጠ ተቃውሞ ገጥሞታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተቃውሟቸውን ለማሰማት ዛሬም አደባባይ ወጥተዋል። በሀምቡርግ ከተማ ዳይሽቶር በተባለው ቦታ ቁጥራቸው 20 000 የሚደርሱ ተቃዋሚዎች ተገኝተዋል። ተቃውሞው ድህነትን፣ ጦርነትን እና የስደት መንስኤዎችን የሚቃወም እንደሆነ ተንፀባርቋል። ፖሊስ የዛሬው ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ አደባባይ ፊታቸው ላይ ጥቁር ጭንበል አድርገው በወጡ ሰዎች ሱቆች ተዘርፈዋል፣ ንብረቶች ወድመዋል፣ መኪኖች ተቃጥለዋል። ከ 200 በላይ የሚሆኑ ፖሊሶች ደግሞ ቆጥለዋል። 

Hamburg G20 Gipfel - Proteste
ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በሀምቡርግ ከተማ በርካታ መኪናዎች ተቃጥለዋል።ምስል picture-alliance/dpa/M. Scholz
Deutschland, Hamburg, G 20
በተቃውሞ ሰልፉ እስከ 100 000 ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።ምስል Reuters/H.Hanschke

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ