1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቢን ላደን አማች የክስ ሒደት

ማክሰኞ፣ የካቲት 25 2006

የተያዘበት የወንጀል ጭብት ከተረጋገጠ እስክ እድሜ ልክ እስራት ሊፈረድበት ይችላል።የክሱ ጭብት አሜሪካኖችን ለመግደል፥ ለማሸበርና ለማወክ ማሴር፥ ከአሸባሪዎች ጋር መተባበር እያለ ይቀጥላል።የአሜሪካ ፖለቲከኞች በግለሰቡ ላይ ከተያዘዉ የክስ ጭብጥ፥ከሚፈረድበት ቅጣት ምንነት ይልቅ በክሱ ሒደት ላይ እየተከራከሩ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1BJZo
ምስል picture-alliance/AP

የኒዮርክ ወረዳ ፍርድ ቤት በአሸባሪነት የተከሰሰዉን የኦስማ ቢን ላደንን አማች (የልጅ ባል) የክስ ሒደት ትናንት መመርመር ጀመረ።ኩዌታዊዉ ሱሌይማን አቡ ጋይት አሜሪካኖችን ለመግደል በማሴር፥ ከአሸባሪዉ ቡድን ከአል-ቃኢዳ አባላት ጋር በመተባበር ተከሷል።የቀድሞዉ የአል-ቃኢዳ መሪ ቃል አቀባይ በመሆን ያገለግል የነበረዉ አቡ ጋይት በአሜሪካ ምድር እና በአሜሪካ የሲቢል ፍርድ ቤት ሲከሰስ ከፍተኛዉ የአል-ኢዳ አባል ነዉ። የዶይቸ ቬለ ጌሮ ሽሊሰ ከዋሽንግተን እንደዘገበዉ አቡ ጋይት በሲቢል ፍርድ ቤት መዳኙ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ክርክር አስነስቷል።


አርባ ስምንት ዓመቱ ነዉ።ሱሌይማን አቡ ጋይት።የተያዘበት የወንጀል ጭብት ከተረጋገጠ እስክ እድሜ ልክ እስራት ሊፈረድበት ይችላል።የክሱ ጭብት አሜሪካኖችን ለመግደል፥ ለማሸበርና ለማወክ ማሴር፥ ከአሸባሪዎች ጋር መተባበር እያለ ይቀጥላል።የአሜሪካ ፖለቲከኞች በግለሰቡ ላይ ከተያዘዉ የክስ ጭብጥ፥ከሚፈረድበት ቅጣት ምንነት ይልቅ በክሱ ሒደት ላይ እየተከራከሩ ነዉ።

ወግ አጥባቂዉ የሳዉዝ ካሮላይና ሴናተር ሊንድሴይ ግራሐም «አሁን የምናደርገዉ ኋላ የምንቆጭበትን ነዉ» በማለት ክሱ በሲቢል ፍርድ ቤት መታየቱን አጥብቀዉ ተችተዋል።ሌሎች ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞችም አቡ ጋይት እንደ ከዚሕ ቀደም ተጠርጣሪ አሸባሪዎች ሁሉ ሁዋንታናሞ ጦር ፍርድ ቤት መቅረብ ነበረበት ባዮች ናቸዉ።

«ሑዩማን ራይትስ ፈረስት» የተሰኘዉ ተቋም የሕግ ባለሙያ ዳፍን ኢቫይተር እንደሚሉት ግን አቡ ጋይት ጦር ፍርድ ቤት ሊያቀርበዉ የሚችል ምንም አይነት መረጃ የለም።

«ማለት የምችለዉ የጦር ፍርድ ቤት ማቅረብ አይችሉም ነዉ።ምክንያቱም ማሴርም ሆነ ለአሸባሪዎች ቁሳቁስ ማቀበል በወታደራዊ ኮሚሽን ክስ ለመመስረት ዋጋ የላቸዉም።ምክንያቱም ነገሮች በልማዱ እንደ ጦር ወንጀል አይቆጠሩም።ወታደራዊ ኮሚሽን የሚመለከተዉ ደግሞ የጦር ወንጀልን ነዉ»

አቃቢ ሕግ አቡ ጋይት፥ በሁለት ሺሕ አንድ ከሚያሚ ወደ ፓሪስ ይበር የነበረዉን የመንገደኞች አዉሮፕላን ለማጋየት ሲሞክር ከየተያዘዉ ከሪቻርድ ሪድ ወንጀል ጋር ግንኙነት አለዉ ባይ ነዉ።አቃቤ-ሕግ ለዚሕ ክሱ እንደመረጃ ያቀረበዉ ግን ሪድ አደጋዉን ለመጣል ሙከራ ከማድረጉ በፊት አቡ ጋይት አዉሮፕላን ላይ አደጋ እንደሚጣል በቪድዮ መልዕክት አስተላልፎ ነበር የሚል ነዉ።

በቪዲዮ የታየና የሚታወቀዉ ግን ኒዮርክ እና ዋሽግተን በአሸባሪዎች የተመቱ ሠሞን አቡ ጋይት ከቢን ላደን ጎን ሆኖ ጥቃቱን «ተገቢ» ማለቱ እና በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዲጣል ጥሪ ማድረጉ ነዉ።

ግለሰቡ ኢራን ዉስጥ በሁለት ሺሕ ሁለት ታስሮ ጥር ሁለት ሺሕ አስራ-ሠወስት ሲለቀቅ ወደ ቱርክ ተሻገረ።ቱርኮች ይዘዉ ለዮርዳኖሶች፥ ዮርዳኖሶች ደግሞ ለአሜሪካኖች አሳልፈዉ ሰጡት።የክሱ ሒደት የተወሳሰበ እንደሚሆን ይጠበቃል።የኒዮርክ ፍርድ ቤቶች ግን የተጠርታሪ አሸባሪዎችን ክስ በመመርመር ልምድ እንዳላቸዉ የሕግ ባለሙያ ኢቪያተርንና ብጤዎቻቸዉ ይመሰክራሉ።

ኬንያና ታንዛኒያ የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲዎችን በማጋየት የተከሰሰዉ አሕመድ ጋይላኒ እድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት እዚያዉ ኒዮርክ ነዉ።ተጠርጣሪ አሸባሪዎችን ኒዮርክን በመሰሉ የሲቢል ፍርድ ቤቶች መዳኘት፥ የዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት የሑዩማን ራይትስ ዋች የሕግ ባለሙያ አንድሪያ ፕርሶዉ እንደሚሉት ተገቢ ነዉ።

«ተጠርጣሪ አሸባሪ ከሁዋንታናሞ ይልቅ በፌደራላዊ ፍርድ ቤቶች በቀረበ ቁጥር ተገቢ ሒደት መሆኑን የሚያስታዉስ ነዉ።»

ኒዮርክና ዋሽግተን ባሸባሪዎች በተጠቁ ማግስት ተጠርታሪ አሽባሪዎች ሁዋንታናሞ-ኩባ እንዲታሰሩ እና በጦር ፍርድ ቤት እንዲዳኙ ያየዙት የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ ናቸዉ። እስካሁን ድረስ የጦር ፍርድ ቤቱ ብይን የሰጠዉ በሰባት ጉዳዮች ላይ ነዉ። የተጠርታሪዎቹ ይዞታ፥የሚፈፀምባቸዉ ምርመራም ሆነ የፍርዱ ሒደት የፍትሕና የመብት ተሟጋቾች እንደተቃወሙት ነዉ።

የአቡ ጋይት የክስ ሒደትም ከሑዋንታናሞ ጋር መገናኘቱ አይቀርም።የተከሳሽ ጠበቆች የመስከረሙን የሽብር ጥቃት አቀነባብሯል ተብሎ ኩዋንታናሞ የታሰረዉን ኻሊድ ሼክ መሐመድን በመከላከያ ምስክርነት ሊያቀርቡ ይፈልጋሉ።ግን ካሊድ ራሱ ያለበት ሥፍራና ሁኔታ ግልፅ አይደለም-እንደ ፕራሶዉ።«ኻሊድ ሼክ መሐመድ ራሱ ኹዋንታናሞ ሚስጥራዊ ሥፍራ ነዉ ያለዉ።የተፈፀመበትን ግፍና ድብደባ በዝር ዝር ይናገራል ተብሎ ሥለሚፈራ አሁን በይፋ እንዲነጋር አይፈቀድለትም። የተፈፀመበትን ግፍ ማንም ሰዉ እንዲያዉቅ የአሜሪካ መንግሥት አይፈልግም።»

Symbolbild Justitia Justizia
ምስል picture-alliance/dpa
Symbolbild Gericht Gesetz Waage und Hammer
ምስል Fotolia/Sebastian Duda

ጌሮ ሽሊስ

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ