1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባካሲ ልሳነ ምድር በካሜሩን ቁጥጥር መዋሉ

ዓርብ፣ ነሐሴ 10 2005

ካሜሩን በደቡቡ የሀገርዋ ከፊል የሚገኘውን የባካሲ ልሳነ ምድር ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረች። ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ካሜሩንን እና ናይጀሪያን እአአ ከ1993 ዓም ወዲህ በይገባኛል ጥያቄ ሲያወዛግብ የነበረው ይኸው አካባቢ

https://p.dw.com/p/19RCC
ምስል AFP/Getty Images

ለካሜሩን እንዲመለስ የወሰነው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር። ብይኑ ናይጀሪያ ግዛቱን ለካሜሩን ሙሉ በሙሉ የምታስረክብበት የአምስት ዓመት ጊዜ ሰጥቶ ነበር። ይኸው የጊዜ ገደብ ትናንት አብቅቶዋል።
ናይጀሪያ እአአ በ1993 ዓም በደቡብ ካሜሩን የሚገኘውን የባካሲ ልሳነ ምድር ከያዘች በኋላ ለ15 ዓመታት ከካሜሩን ጋ በግዛት የይገባኛል ጥያቄ ደም አፋሳሽ የድንበር ውዝግብ ማካሄዷ የሚታወስ ነው። የአከራካሪው የባካሲ ልሳነ ምድር ጉዳይ ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ ግዛቱ ለካሜሩን ይገባል ሲል ብይን ያሳለፈው እአአ ነሀሴ 2008 ዓም ነበር። በይፋ ያስረከበችው ነበር። ናይጀሪያ ግዛቱን ለካሜሩን ቀስ በቀስ እንድታስረክብ ፍርድ ቤቱ ያስቀመጠው የአምስት ዓመት የጊዜ ገደብ ትናንት አልፎ ግዛቱ ሙሉ በሙሉ በካሜሩን ቁጥጥር ስር ውሏል። ሂደቱ ለካሜሩን ትልቅ ትርጓሜ ቢይዝም ፣ ዕለቱ በሀገሪቱ ያን ያህል ሰፊ ሽፋን አልተሰጠውም። ምክንያቱን የራድዮ ካሜሩን የፖለቲካ ክፍል ዋና አዘጋጅ አሹንየንቲ ሲያስረዱ፣
« ካሜሩን ብልህ ርምጃ በመውሰድ በአንድ ጎረቤት ሀገር፣ ማለትም፣ በናይጀሪያ ላይ ትልቅ ድል ማግኘቷን ከማሳየት ተቆጥባለች። የካሜሩን መንግሥትም በዚሁ ድል አልተኩራራም። ምክንያቱም የተረሳ ስሜትን ለመቀስቀስ እና እንዲድን የተተወን ቁስል እንደገና ለመነካካት አልፈለገም።። »
ካሜሩን በባካሲ ሰበብ የተፈጠረውን ውዝግብ ለዓለም አቀፉ የድንበር ጉዳይ ተመልካች ፍርድ ቤት የወሰደችበት ዲፕሎማሲ ሊያገረሽ የነበረ ጦርነትን ማስወገድ መቻሉን ብዙ የካሜሩን ዜጎች ያምናሉ። የ35 ዓመቱ አንድሬ ጆን ባካሲ ፍርድ ቤቱ ብይኑን ባሳለፈበት ጊዜ ናይጀሪያን ይመሩ የነበሩት ፕሬዚደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንዦ እና የካሜሩን አቻቸው ፖል ቢያ የፍርድ ቤቱን ብይን መቀበላቸው መልካም እንደሆን ገልጾዋል።

Nigerianischer Soldat auf der Halbinsel Bakassi
ምስል AP

« ለውዝግቡ መፍትሔ የተፈለገበት አካሄድ የሚሞገስ ነው። በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ድርድር ባይካሄድ ኖሮ አስከፊ ደም አፋሳሽ ግጭት በተፈጠረ ነበር። ድርድሩ ከሁሉም የተሻለ አማራጭ ነበር። »
በባካሲ 40,000 ስው ሲኖር ብዙዎቹ የናይጀሪያ ዜጎች ናቸው። እነዚሁ የናይጀሪያ ዜጎች በካሜሩን ወታደሮች ብዙ ግፍ እንደደረሰባቸው ነው የሚናገሩት። እንዲያውም ፣ ከሁለት ወር በፊት አንዳንድ ናይጀሪያውያን ነጋዴዎች እና የካሜሩን ቀረጥ ሰብሳቢዎች መካከል ግችት ከተፈጠረ በኋላ ያካባቢው አስተዳደር የሰዓት እላፊ ማወጅ ግድ እንደነበረበት ተገልጾዋል። የመብት ተሟጋቾች በባካሲ የሚኖሩ ናይጀሪያውያን አድልዎ እንደሚያሰጋቸው አስጠንቅቀዋል። በዚሁ በነዳጅ ዘይት ሀብት በታደለው ግዛት ውስጥ የባካሲ ግዛት መቆየት የመረጡ ናይጀሪያውያን የሀገሪቱን ሕግ ማክበር እንዳለባቸው የባካሲ ዋና አስተዳዳሪ ኦካሊያ ቢላይ አስረድተዋል።
« የሚኖሩት በካሜሩን ግዛት ውስጥ መሆኑን ግልጽ አድርገንላቸዋል። ስለዚህ ፣ አንድም ፣ ከእንደ የካሜሩን ዜጋ ወይም ከእንደ የውጭ ሀገር ዜጋ የሚጠበቀውን ማሟላት አለባቸው። የውጭ ዜጋ ከሆኑ የመኖሪያ ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል፣ መስጠት ያለባቸውም ክፍያ አለ። ማክበር ያለባቸው ሕጎች እና ደንቦችም እንዳሉ ማወቅ አለባቸው። »

Halbinsel Bakassi zwischen Nigeria und Kamerun
ምስል AP


በባካሲ ልሳነ ምድር መቆየት የመረጡ ናይጀሪያውያን አንድም የካሜሩንን ዜግነት ማግኘት አለባቸው ወይም ቪዛ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ካሜሩን ባባካሲ ያሉትን የብዙኃኑን ናይጀሪያውያን ተዋህዶ መኖርን ለማፋጠን የሚያስችል ኮሚሽን ማቋቁሙንና ኮሚሽኑ አዎንታዊ ውጤት ማስመዝገቡን የኮሚሽኑ ሊ ቀ መንበር ወይዘሪት ዶቤታ ባርካታ ገልጸዋል።
በተመድ ቁጥጥር እና በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ብይን መሠረት፣ ካሜሩን የባካሲ ልሳነ ምድር ሙሉ ዉጥጥር ከመረከብዋ በፊት በዚያ የሚኖሩትን ብዙኃኑን የናይጀሪያ ዜጎች መሠረታዊ መብት እንደምታከብር ዋስትና መስጠት ነበረባት።

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ