1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባየርን ሙኒክ እና ሪያል ማድሪድ የምሽቱ ግጥሚያ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2006

በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች፤ በተለይ የባየርን ሙኒክ እና ሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ዛሬ ማታ ከቴሌቪዥን ፊት ለፊት አይጠፉም።

https://p.dw.com/p/1Bqur
Karim Benzema Real Madrid
ምስል Getty Images

ጨዋታው በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ይጀምራል። የጀርመኑ ባየርን ሙኒክ ቡድን ለማሸነፍ ቆርጦ የተነሳ ይመስላል።ዛሬ ማታ የሚታየው የእግር ኳስ ግጥሚያ ከፍፃሜ ውድድር የማይተናነስ ነው። የጀርመኑ ኤፍ ሲ ባየርን ሙኒክ ቡድን በሀገሩ- ሙኒክ ከተማ የስፓኙን ሪያል ማድሪድ ቡድን ይገጥማል።ከሁለት ሰዓታት ገደማ በኋላ ለግማሽ ፍፃሜ ሻምፒዮና ሊግ የሚቀርቡት ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ሳምንት በማድሪድ ባካሄዱት ግጥሚያ አንድ ለባዶ ሲለያዩ ለባየርን ቡድን ሽንፈቱ ቀላል አልነበረም። ስለሆነም ዛሬ « በፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ጠንክረን እና በጥሩ ሁኔታ መጫወት አለብን።» ነው ያሉት አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ። ምንም እንኳን ቡድናቸው ባለፈው ግጥሚያ ይበልጥ ኳሷን ቢቆጣጠርም ጎል ለማስቆጠር ግን አልበቃም።

ያለፈው አመት የዋንጫ ባለቤት ባየርን ሙኒክ በዚህ አመትም ዋንጫ ባለቤት መሆን ይፈልጋል። ይሁንና የሚገጥመው ቡድን ተጫዋቾች በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እና ባልደረባው ጋሬት ቤል ቁስላቸው ድኗል። « ጥይታችንን ይዘናል እንዲሁም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን» ሲል ሮናልዶ፤ ቤል ደግሞ አከለበት « የማናሸንፍበት እና ለፍፃሜ የማንደርስበት ምንም ምክንያት የለም» አለ። የሪያል አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ግን ለሰጡት አስተያየት ትንሽ ቁጥብ ነበሩ። «ገና ሳንጫወት አልፈናል ብለን አንደመድምም» ነው ያሉት።

Real Madrid-Fan Ramon im Hofbräuhaus in München
የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎችምስል DW/T. Oelmaier

የሪያል ማድሪድ ምንም እንኳን ዛሬ በሀገሩ ላይ ባይጫወትም ጥሩ እድል አለው። ቡድኑ አንድ ግብ በሙኒክ ላይ ቢያስቆጥር ባየርን ሙኒክ ቢያንስ ሶስት ማስቆጠር ይኖርበታል። ስለሆነም የባየርን ቡድን በራሱ ከተማ ከሚካሄደው ጨዋታ፤ የህዝቡን እና የቡድኑን ድጋፍ ክፉኛ ያሻል። ተጫዋች ዳቪድ አላባ በዚህ ባለ ሙሉ ተስፋ ነው።

« ባለፈው ዓመት ከባርሴሎና ጋር በነበረው የሻምፒዎና ሊግ ተመልካች ምን ያህል ድጋፍ እንደሚሰጡ የተመለከትን መሰለኝ። ወዲያው ነው ወደ ስራችን የገባነው። ስለዚህ ደጋፊዎቻችን ወደ ፊት እንድንራመድ ይገፋፉናል ብለን እንተማመናለን።»

የዳቪድ አላባ ምኞት ኃላ ላይ እውን ከሆነ የባየርን ሙኒክ ቡድን ለ 3ኛ ጊዜ ለፍፃሜ ውድድር ሲያልፍ ፤ ሪያል ማድሪድ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ ከግማሽ ፍፃሜ ይሰናበታል ማለት ነው። ለነገሩ የዚህኛው የሻምፒዎና ሊግ ውድድሮች መካሄድ ከጀመሩ አንስቶ ስፓኞችን ቀንቷቸዋል። ጀርመናውያኑ አልተሣካላቸውም። ሻልከ 04 ቡድን ገና ከማጣሪያው ሲሰናበት ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ደግሞ ከሩብ ፍፃሜ ተሸንፏል።

Pep Guardiola PK 28.04.2014 München
የባየር ሙኒክ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላምስል Reuters

አሰልጣኝ አንቸሎቲ በመጀመሪያው የማድሪድ አመቴ ማሸነፍ ብንችል፤ እጅግ ጥሩ ነበር» ብለዋል። ግን ኤፍ ሲ ባየርንም ዋንጫውን ለማስጠበቅ ትልቅ ምኞት አለው። እንደ ቀድሞው የሪያል ማድሪድ ተጫዋች አርዬን ሮበን ከሆነ ቡድኑ ወደ ፍፃሜ ውድድር የማለፍ አቅም አለው። « እኛ ሁለት የፍፃሜ ውድድር ተካፍለናል። እና ቡድናችን ዳግም ታሪክ ለመፃፍ ዝግጁ ነው» ብሏል። አርዬን የቀድሞ ቡድኑን ግን አላጣጣለም።

« በራስ መተማመን ነው የሚመጡት። በዚህኛው የሻምፒዎና ሊግ ውድድር ጥሩ ይጫወታሉ። ነገር ግን ወደ ሙኒክ እንደሚመጡና እዚህ ደግሞ ቀላል እንደማይሆን ያውቁታል። ፍራቻ አላቸው ማለቴ ሳይሆን እንዳልተጠናቀቀ ያውቃሉ ማለቴ ነው። »

ከሁለት ሰዓታት ገደማ በኋላ የሚካሄደው የእግር ኳስ ግጥሚያ ምን ያህል በጉጉት የሚጠበቅ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። 880 ጋዜጠኞች ስለ ጨዋታው ከስፍራው ይዘግባሉ። እንደ ባየርን ቃል አቀባይ ማርኩስ ሆርቪክ ከሆነ ከሰሜን ኮርያ በቀር ጨዋታው በሁሉም ሀገራት በቴሌቪዥን ይተላለፋል።

ኦሊቫ ጌርስትንቤርገር

ልደት አበበ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ