1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባፓል እልቂት የሃያ-አምስተኛ አመት

ሐሙስ፣ ኅዳር 24 2002

በየዕለቱ፥ በየሥፍራዉ ትናንሽ ግን ብዙ ቦፓሎች አሉ።ሚሊዮኖችን-ለሞት ወይም ለእድሜ ልክ በሽታ ያጋለጣሉ።

https://p.dw.com/p/Kpk5
ምስል Pia Chandavarkar

03 12 09

ማዕከላዊ ሕንድ ቦፓል ከተማ የሚገኘዉ የዩናይትድ ስቴትስ የተባይ ማጥፊያ ፋሪካ ፈንድቶ በርካታ ሰዎች የገደለበት ሃያ-አምስተኛ አመት ዛሬ እየታሰበ ነዉ።ከፋብሪካዉ የወጣዉ መርዛማ ጢስ አደጋዉ በደረሰበት ወቅት ከሰወስት ሺሕ በላይ ሰዎች ሲገድል፥ ከአደጋዉ በሕዋላ ደግሞ ከያ-ሁለት ሺሕ በላይ ሰዎች ሞተዋል።አደጋዉ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብን አካል አጉድሏል ወይም የድሜ ልክ በሽተኞች አድርጓቸዋል።መዘዙ እስከ ዛሬም አልተወገደም።የቦፓሉ አደጋ ዛሬ ሲዘከር የሰብአዊ መብት እና የተፈጥሮ ተሟጋቾች፥ በየሥፍራዉ ትናንሽ ቦፓሎች እየተከሰቱ ነዉ-ይላሉ።ፕሪያ ኤሰልቦርንና ፒያ ቻንዳርቫራካር የዘገቡትን ነጋሽ መሐመድ አጠናክሮታል።

እሱ-«ኑሮ ካሉት---» ብሂልን ለሚያጤን እድለኛ ነዉ።-ኢርሻድ ዓሊ።ያኔ አስራ-አንድ አመቱ ነበር።ስድስት ቤተሰቡን ቀብሯል።ዛሬ የስድስት ልጆች አባት ነዉ።ባጃጁን-ያንኮራኩራል።
ወንበሩ አጠገብ አንዲት ትንሽ ነገር ተንጠልጥላለች።አረንጓዴ ነች።ነጭ ተሸልሞባታል።ባጃጁ-እንጀራዉ- «ዳቦ፥ ወይስ ሩዝ ይሆን? የሚሉት እነሱ።ብቻ አንዱ ነዉ።ያቺ ነገር ደግሞ እስትንፋሱ።።

«ብዙ ጊዜ ትንፋሽ ያጥረኛል።ሳንባዬን ያቃጥለኛል።ደንገዝገዝ ሲል ማየት አልችልም።ግን መንዳት አለብኝ፥ አለበለዚያ ገንዘብ አላገኝም።በተሽከርካሪዎች በተጨናናቀ መንገድና ጢስ ባለበት አካባቢ ሳልፍ ደግሞ በጣም እሰቃያለሁ።በዚች ነዉ-የምተነፍሰዉ።ሐኪሙ ባጃጅ እንዳልነዳ ከልክሎኝ ነበር።ግን ቤሰቤን ምን አበላቸዋለሁ።»
ኢረሺድና ብጤዎች በትንሽ ግምት መቶ-ሺዎች ናቸዉ።የሰብአዊ መብትና የተፈጥሮ ሐብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ግን በየዕለቱ፥ በየሥፍራዉ ትናንሽ ግን ብዙ ቦፓሎች አሉ።ሚሊዮኖችን-ለሞት ወይም ለእድሜ ልክ በሽታ ያጋለጣሉ።

«ቦፓል ዉስጥ ያን ያሕል ትልቅ አደጋ ከደረሰ በሕዋላ እንኳን እስካሁን ድረስ አደጋ እንዳይደርስ ምንም አይነት ዋስትና የለም።ባሁኑ ወቅት ሕንድ ዉስጥ በየዕለቱ ብዙ ትናንሽ ብሆፓሎች ይከሰታሉ።ዕለት በዕለት አንድ-ወይም ሁለት አደጋዎች መድረሳቸዉን እንሰማለን።በማግስቱ ምናልባት አራት ሠራተኞች መሞታቸዉን እንሰማለን።»

ሕንዳዊዉ የተፈጥሮ ሐብት ተሟጋች ቻንድራ ቡሻን።ሕንድ ብቻ አይደለም።ከባንግላዴሽ እስከ ኢንዶኔዢያ፥ ከፓኪስታን እስከ ናጄሪያ ሌላም ጋ ለአዉሮጳ-አሜሪካ ገበያ ጨርቃ-ጨርቅ፥ ቆዳ፥ ነዳጅ ዘይት፥ መድሐኒት ወይም ሌላ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች-የሚለቁት መርዛማ ኬሚካል በርካታ-ሰዉ፥ እንሰሳ፥ የተፈጥሮ ሐብት እየጎዳ ነዉ።

Flash-Galerie Giftgaskatastrophe Bhopal
ምስል AP

ኩባንዮቹ እስያን ወይም አፍሪቃን ሲመርጡ ርካሽ ጉልበት፥ጥሬ እቃ ማግኘታቸዉን እንጂ-በየሐገሩ ሕዝብና የተፈጥሮ ሐብት ላይ ሥለሚደርሰዉ ጥፋት አያስቡም።ኮርፖሬት አካዉንቴብሊቲ እንተርናሽናል-የተሰኘዉ የመብት ተሟጋች ተቋም ባልደረባ ኒክ ገሮፍ-እንደሚሉት ደንበር ዘለሎቹ ኩባንዮች ከትርፍ ባለፍ በርግጥም የሚያስቡ-የሚጨነቁበት ምክንያትም የለም።

«የቦፓሉ ታላቅ እልቂት የሚያስታዉሰን አሳሳቢ ጉዳይ (ኩባንዮቹ) ዉጪያዊ ምክንያት ለመስጠት መሞከራቸዉን ነዉ።ባለኢዱስትሪዎቹ ለሕጎች መከበርና ለመሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች መጠበቅ ደንታ የላቸዉም።የሲቢል ማሕበረሰብ ተቋማት ጥያቄ የሚያስጠብቅ፥ ወይም የሰዎችን መብት የሚያስከብር ሕግ ያለመኖሩን አጋጣሚ እርካሽ ምርት ለማግኘት ያዉሉታል።ጠቀም ያለ ትርፍ ለማግኘት።»

ያም ሆኖ ነገሮች በነበሩበት-እንደሌሉ ሁሉ ወደፊት ባሉበት አይቀጥሉም።ኩባንዮቹ ብቻ ሳይሆን ለኩባንዮቹ ፍቃድ የሚሰጡ መንግሥታት ወይም ሹማምንት-ለሚደርሰዉ ጥፋት መጠየቃቸዉ አይቀርም።እንደገና ገሮፍ፣-

«እንደሚመስለኝ ቦፓል የደረሰዉን አደጋ አስከፊነት ሥናስታዉስ ዛሬም ከሃያ አምስት አመታት በሕዋላ እንኳን እነዚሕ ግዙፍ ኩባንዮች መስጠት የሚገባቸዉን ያሕል ትኩረት አለመስጠታቸዉን እንገነዘባለን።ይሁንና የሚፈፀመዉ በደል የትም-ይላኩት የትም፥ምክንያቱን ዉጪያዊ ለማድረግ ያሻቸዉን ያክል ቢክሩም፥ በየደረሱበት ከሲቢል ማሕበረሰብ ተቋማት ጥያቄ፥ ዋና መስሪያ ቤታቸዉ በሚገኝበት ደግሞ ከሕግ ተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም።»

መቼና-እስከ መቼ አይታወቅም።ኢርሻድ ዓሊ-ባየር እጦት እንደቃተተ፥ በዘመዶቹ ሞት ሐዘን እንደባተተ ሠላሳ ስድስተኛ አመቱን ደፈነ።

Priya Esselborn:Pia Chandarvarkar

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ