1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቤምባ የክስ ሂደት በዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 14 2003

የቀድሞ የዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ምክትል ፕሬዝዳንት ዦን ፒየር ቤምባ በአምስት የወንጀል ዓይነቶች ክስ ተመስርቶባቸው ትላንት በዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀሎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

https://p.dw.com/p/QGJD
ምስል AP

እ.ኤ.አ ከጥቅምት 2002 እስከ መጋቢት 2003 ድረስ በጂያን ፒየር ቤምባ በግል የሚታዘዙ 1500 ወታደሮች ወደ መካከለኛ የአፍሪካ ሪፑብሊክ በመግባት የግድያና አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎችን በሰላማዊው ህዝብ ላይ ፈጽሟል ይላል ትላንት ሄግ ለተሰየመው ችሎት የቀረበው የክስ ፋይል። በዚህም ዦን ፒየር ቤምባ በቀጥታ ተጠያቂ መሆናቸውን የዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ገልጸዋል። ዋና አቃቤ ህግ ሉዊስ ሞሪኖ ኦካምፖ ዦን ፒየር ቤምባ ፈቅደውና አዘው ያስፈጸሙት ወንጀል ነው ይላሉ።

ትላንት የተሰየመው ዓለም ዓቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የቀድሞውን የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ምክትል ፕሬዝዳንት የተከሰሱበትን ወንጀሎች በሁለት ከፍሎ ነው እየተመለከተ ያለው። አንደኛው በሰውልጅ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ክራይም አጌይንስት ሂውማኒቲ ሲሆን በዚህ ዘርፍ ቤምባ ላይ ሁለት ክሶች ቀርበዋል። ሌላው የጦር ወንጀል ክስ ሲሆን ሶስት ያህል ፋይሎች ተከፍተውባቸዋል። የ48 ዓመቱ ዦን ፒየር ቤምባ የተያዙት እ.ኤ.አ በ2008 ቤልጂየም ላይ ነው። ቤምባ የቀረበባቸውን ክስ አልተቀበሉትም። ከህዝባቸው ድጋፍ እንደሚፈልጉና ሀገራቸው አዲስ ምዕራፍ እንድትጀምር እንደሚሹ ነው የሚገልጹት።

ድምጽ

«የኮንጎን ህዝብ ድጋፍ እየጠበኩ ነው። አዲስ ምዕራፍ በመጀመር ለኮንጎ አዲስ ፍልስፍና አዲስ አስተዳደርና አመራር እንዲያመጣ ድጋፉን እየጠበኩኝ ነው።»

በእርግጥ ትላንት የተሰየመው የሄጉ ችሎት ላይ አቃቤ ህግ የመሰረተው ክስ በግልጽ እንደሚስቀምጠው ዦን ፒየር ቤምባ መጠነ ሰፊ የሆነ ወንጀል አንዲፈጸም ቀጥተኛ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ መዲና ባንጉይ ብቻ 400 የአስገድዶ መድፈር ድርገቶች በቤምባ ወታደሮች ስለመፈጸማቸው በማስረጃ ተረጋግጧል። የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የቀድሞ መሪ አንጌ ፌሊክስ ፓታሴ ከተቃጣባቸው መፈንቅለ መንግስት እንዲያስጥሏቸው ነበር ዦን ፒየር ቤምባን የጠየቁት። ያን ጊዜም ቤምባ የሚመሯቸው 1500 ወታደሮች ፓታሴን ከመፈናቀል ለማዳን ገብተው አሁን ላይ ቤምባ ችሎት የቆሙባቸውን ወንጀሎች ፈጸሙ ይላል የዓለም ዓቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ክስ።

ዦን ፒየር ቤምባ ሀገራቸውን ጥለው የኮበለሉት እ.ኤ.አ በ2006 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ነው። ቤምባ በተለይ በምዕራባዊ የኮንጎ ግዛት ሰፊ ተቀባይነት እንዳላቸው ይነገራል። በ2006ቱ ምርጫም ከምዕራቡ ጋዛት ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላን በአብላጫ ድምጽ አሸንፈው ነበር። አብዛኛው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ህዝብ ቤምባ በመጪው ዓመት አጋማሽ ላይ በሚደረገው ምርጫ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላን መፎካከር የሚችሉ ጠንካራ መሪ ይሆናሉ ብሎ እንደሚያምኑ ዘገባዎች ያመላክታሉ። እንደ ፖለቲካው ታዛቢዎች አስተያየት ትላንት የተሰየመው የሄጉ ችሎት ቤምባን ከምርጫው ለማጥፋት የተደረገ ዘዴ ሳይሆን አይቀርም። ይህንን አስተያየትም የሚጋራ ሀሳብ ከቤምባ ጠበቃ ትላንት ተሰንዝሯል። ጠበቃው ክሶቹ መሰረት የሌላቸው ከጥርጣሬ ያለፈ ጭብጥ የማይገኝላቸው ሲሉ ትላንት ለችሎቱ ገልጸዋል። ሌላኛው ጠበቃቸው ኤሜ ኪሎሎም ወታደሮቹ በመንግስት የተላኩ እንጂ በቤምባ አይደለም ሲሉ ይሟገታሉ

በእርግጥ የዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ህግ ሉዊስ ሞሪኖ ኦካምፖ ቤምባ በወንጀሉ ተጠያቂ ስለመሆናቸው የሚጠራጠሩ አይደሉም። መጀመሪያ ላይ በወንጀሉ የመካከለኛው አፍሪካ የቀድሞ መሪ ፓታሴ እጃቸው እንዳለበት ነበር የተገመተው። ኦካምፖ እንዳሉት ማስረጃዎች ግን በቤምባ ቁጥጥር ስር ባለው ጦር የተፈጸመ በቀጥታም ቤምባ ያስፈጸሙት እንደሆነ ያሳያሉ።

የዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የህግ ባለሙያ ፈዲል አብደላህ እንደሚሉት የቤምባ የክስ ሂደት ማንም ወንጀል ቢሰራ እንደማያመልጥ የሚያሳይ ነው።

ድምጽ

ሄግ ላይ የተሰየመውና የቀድሞውን የዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፑብሊክ ምክትል ፕሬዝዳንትን ለፍርድ ያቀረበው ችሎት ዛሬም ቀጥሏል። ለመጪዎቹ ስድስት ወራትም የሚዘልቅ ነው። በቀጣዩቹ ጊዜያት የ759 ምስክሮች ቃል ይደመጣል። እንዚህ ምስክሮች በቤምባ ጦር የአስገድዶ መድፈርና ሌሎች ጥቃቶች የተፈጸመባቸው እንደሆኑ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

መሳይ መኮንን

ተክሌ የኋላ