1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዉዝግብና በከፊል የተሰረዘዉ የዘንድሮዉ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 6 2011

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዉዝግብና የትምህርት ምንስቴር የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ዉጤትን በተመለከተ የሰጠው  መግለጫ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ በርከት ያለ አስተያየትና ትችት የቀረበባቸዉ ጉዳዮች ነበሩ።

https://p.dw.com/p/3PBlk
Logos App Twitter Facebook Google
ምስል picture-alliance/xim.gs

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 

በየጊዜዉ አንዳች መወያያ ጉዳይ በማያጡት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰሞኑን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን ለማቋቋም የሚንቀሳቀስ ኮሚቴ ያወጣዉ መግለጫ ብዙ እያነጋገረ ነዉ። መግለጫዉን እንደተሰማም ከቤተ ክርስቲያኒቱ  እዉቅና ዉጭ የተሰጠና ድርጊቱም ህገ ወጥ ነዉ በሚል  መንግስት  ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆም የሚጠይቅ መግለጫ  በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መሪዎች መዉጣቱ ደግሞ ጉዳዩ የቤተ ክርስቲያኗ የዉስጥ ጉዳይ ቢሆንም በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ሳይቀር  ጎራ ለይቶ ሲያነጋግር ነዉ የሰነበተዉ። የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን  ስለማቋቋም የተሰጠው መግለጫ አንዳንዶች በቋንቋ ከመገልገል መብት አንፃር ሲመለከቱት አንዳንዶች ደግሞ «ቤተክርሲቲያኒቱን ለመከፋፈል የተደረገ ሴራ ነዉ» በሚል ይቃወሙታል።

ሳባ ተሰማ «ሰላምን መስበክ የሚገባቸዉ የሃይማኖት አባቶች ሰላም አጥተዉ ሲጋጩ ማየት ምንኛ ያሳዝናል። ሀገሪቱ በቂ ችግር አላት እባካችሁ አባቶች ተወያይታችሁ ችግሩን ፍቱ።» ሲሉ፤ መቅደስ  ተስፋዬ ደግሞ  «ሃይማኖት ብሔር የለውም፡፡ ኦሮሞውም፣ አማራውም፣ ትግራዩም ወዘተ.. ለሃይማኖቱ ቀናኢ ነው፡፡ ፖለቲከኞችን በተማመኑ ግለሰቦች ቤተእምነቶች ሲፈርሱ አይገባም» በማለት ተችተዋል።

አሌካሳንደር የተባሉ  አስተያየት ሰጪ ደግሞ«  ይህንን እኮ በቤተክርስቲያኒቱ  መዋቅር  ስር ሆነዉ ችግሩ እንዲፈታ መጠየቅና መስራት ይችሉ ነበር። ከቤተክርስቲያኒቱ  እዉቅና ዉጭ በጀርባ መግለጫ መስጠት ግን እንድነጠራጠር አድርጎናል። በተለይ ከኮሚቴዎቹ መካከል አንዱ አባት የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄ ከቤተክርስቲያን  ችግር ጋር አዳብለዉ ማቅረባቸዉን ስንመለከት የጥያቄዉ መነሻ ሃይማኖታዊ  ነዉ ለማለት እንድነቸገር አድርጎናል።» ብለዋል።

Äthiopien Orthodoxe Kirche Patriarch Matias
ምስል DW/G.T.Hailegiorgis

ባይሴ  የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ  በበኩላቸዉ «ከመካከል አንድ ሰዉ ሊሳሳት ይችላል ኮሚቴዎቹ ያነሱት ችግር ግን በአብዛኛዉ በኦሮሚያ ክልል ባሉ ቤተክርስቲያናት የሚታዩ ናቸዉ። መፍትሄም የሚያስፈልጋቸዉ ናቸዉ። ምዕመኑ በቋንቋዉ ሃይማኖቱን ሊማር ይገባል።»በማለት ፅፈዋል።

ዓለም ኃይሌ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ደግሞ  «በቤተ ክርስቲያኒቱ ያለዉ የአገልጋዮች እጥረትና  የቋንቋ ችግር በኦሮሚያ ብቻ የሚታይ አይደለም ። ችግሩ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ያለ ችግር ነዉ። ስለዚህ ይህንን ችግር በቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር መሰረት በሁሉም አካባቢ ችግሩን ለመፍታት መሞከር እንጅ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት በማቋቋም አይፈታም። ይህ ቤተክርስቲያኒቱን ከመክፈልና ችግሩን ከማባባስ ዉጭ መፍትሄ አይሆንም። በአብዛኛዉ የቤተክርስቲያን መፃህፍትና አገልግሎትም  በግዕዝ  መሆኑንም አትርሱ።» ሲሉ ፅፈዋል።

አሊ ሁሴን የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ግን « ጥያቄያቸው በቋንቋችን እናምልክ አሉ እንጂ እንገንጠል አላሉ ጉዳዩን ከብሄርና ከፖለቲካ ጋር የምታያይዙ ሰዎች ትገርማላችሁ  ይህ የቤተክርስቲያኒቱን  ችግር በመሸፋፈን ወደ ዉድቀትና መዳከም እንድታመራ ያደርጋታል እንጅ አይጠቅማትም ። ሲሉ ተችተዋል።

«የነ ቄስ በላይ ደጋፊዎችም ነቃፊዎችም ፖለቲከኞች እና ቁማርተኞች ናችሁ፤ ቁማርተኞች እጃችሁን ከቤተክርስቲያን ላይ አንሱ!»ሲል በፌስቡክ ገፁ የፃፈዉ ደግሞ ጋዜጠኛ አበበ ቶላ ነዉ።

ዓለማየሁ ዘበነ «አሁን ጥያቄው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ቅዱስ ሲኖዶስ የህግ ማስከበር ጥያቄ መንግሥት ለምን ቸል አለው የሚለው ነው፡፡ የሠላም ሚኒስትር አቋቁሞ ጠዋት ማታ ስለሠላምና መረጋጋት የሚዘምር መንግሥት የሚታይ ግልጽ አደጋን ሰምቶ እንዳልሰማ የሚሆነው በምን ምክንያት እንደሆነ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ » ሲሉ ፤ ሀረግ ዘለቀ ደግሞ «በእርግጥ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ሊገባ ይችላልን ? መንግሥትና ሃይማኖት እኮ የተለያዩ ናቸዉ።» በማለት የአቶ ዓለማየሁን ሀሳብ ተችተዋል።

Äthiopien Addis Ababa - Orthodoxe Kirche hält Generalversammlung
ምስል DW/G. Tedla

አስቴር መንግሥተአብ «እንዲህ ዓይነት መፈንቅለ ሃይማኖት፣ መፈንቅለ ሲኖዶስ በቀጣይ አደገኛ ግጭትና የጸጥታ መደፍረስ ስለማስከተሉ ለመናገር ሳይንቲስት መሆን አይጠይቅም፡፡»

ፈረጃ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ «ከምንም በላይ ደግሞ መንግሥት ለማንም ሳይሆን ለራሱ ሲል ለሀገር ሰላም ሲል ጉዳዩ በሰላም እንዲቋጭ ማድረግ አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትራችን በኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ለዓመታት የነበረውን አጥር በእርቅ እንዲፈርስ ያደረጉት፤ በመጅሊስ መካከል የገባውን ንፋስ ያስተነፈሱት ከመበታተን ይልቅ አንድነት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ጭምር ያለውን ዋጋ አስቀድመው በመረዳታቸው ይመስለኛል።» ብለዋል።

አፈንዲ ሙተቂ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕርሳቸዉ በደግነት የሚያዉቋቸዉ ብዙ ሰዎችን ያፈራች መሆኗን ጠቅሰዉ «እነዚህ ደጋግ ሰዎችን ያፈራችው ቤት እንድትከፋፈል አልመኝም። በሁለቱም ወገን ያሉት አባቶች ችግሩን በውይይት ቢፈቱት ይሻላል ባይ ነኝ። ኸላስ!!»ብለዋል።

አዲስ ባወጣዉ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ- ካርታ ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተዉ የኢትዮጵያ የትምህርት ምንስቴር በዚህ ሳምንትም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ዉጤትን በተመለከተ ያወጣዉ መግለጫ እያነጋገረ ነዉ። የትምህርት ሚኒስቴር  ከፍተኛ የሥራ  ኃላፊዎችና  ስድስት የክልል የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ/ም  ተስማምተናል ብለዉ በጋራ  በሰጡት  መግለጫ  በዚህ ዓመት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና  የወሰዱ ተማሪዎች ዉጤት በተፈጥሮ  ሳይንስም ይሁን  በማህበራዊ  ሳይንስ  የትምህርት  መስኮች  ከአራት አራት  የትምህርት  ዓይነቶች ዉጭ የሌሎቹ መሰረዙን ገልፀዋል።

ዉሳኔዉ የተላለፈዉ  ሰኔ 9 እና 10 ቀን 2011 ዓ/ም በተሰጡ  ፈተናዎች ከሚጠበቀው በላይ ውጤት የተመዘገበባቸዉ ወይም «የጋሸበ ውጤት« ስለተገኜ  መሆኑንም ት/ት ሚንስቴር ጨምሮ ገልጿል። በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ እና ስነ-ዜጋ ፈተናዎች  በማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ደግሞ የታሪክ፤ ኤኮኖሚክስ እና ስነ-ዜጋ ፈተና ውጤቶች ውድቅ ሆነዋል መባሉ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በእጅጉ መነጋገሪያ ሆኗል

ምንዳዬ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ «ዉሳኔዉ ዳግም የመኮራረጅ ችግር እንዳይፈጠር ትምህርት የሚሰጥ ነዉ»ሲሉ 

Äthiopien  Dr. Tlaye Gete Bildungsminister
ምስል DW/Y. Geberegziabhe

አለሙ በለጠ «የባዮሎጅ ውጤት ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የሥነ-ዜጋ እና የታሪክ ውጤት ደግሞ ለማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ያላቸውን ዋጋ ያልተረዳ ዉሳኔ ነዉ።» ሲሉ ነቅፈዋል።

ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ « ጥሩ ይሰሩ የነበሩና ዩኒቨርሲቲ እንገባለን ብለው በተስፋ ሲጠባበቁ የነበሩ ተማሪዎችን  በአሰራር ችግር ከዩኒቨርስቲ ማስቀረት ተገቢ አይደለም። ኃላፊነት የሚሰማችሁ ከሆነ ሁሉንም በአንድ ከመጨፍለቅ ግሽበት የታየባቸውን ትምህርት ቤቶች ለይታችሁ እርምጃ ዉሰዱ።» ብለዋል።

አላጀ ወዲ ቀሺ የተባሉ ሰዉ ደግሞ «ከመጀመርያ ቀን ጀምሮ የዘንድሮ ማትሪክ ስርቆትና ማጭበርበር ብቻ ሳይሆን የወረደ የዘመኑ ፖለቲካ እንደገባበት ፅፈናል። ፈተናው እንደገና መፈተንና በአጠፉ ሰዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ሲገባው በየጊዜዉ ጥገናዊ ለውጦች ማካሄዳቸው አግባብ አይደለም።» ብለዋል።

እጅጉ አበበ ባይሳ «ድሮ እህል ነበር ማሳ ላይ ጋሸበ የሚባለዉ! አሁን የዋጋ ግሽበት አልበቃ ብሎ የፈተና ዉጤትም መጋሸብ ጀመረ! ወይ ዘንድሮ ።» ሲሉ፣ አበበ ተመስገን  ከአንድ ወዳጀ ገፅ አገኜሁት ብለዉ ያጋሩት መልዕክት ደግሞ «ጠንካራ የትምሕርት ስርዓት የሌለው ማኅበረሰብ እና ቀፎው የፈረሰበት የንብ መንጋ አንድ ናቸው። ሁለቱም፦ በስልት ሳይኾን፤ በግርታ የሚነዳ መንጋ ከመፍጠር አይተርፉም። »ብለዋል።

Schulprüfung unter spezielle Militär Garde
ምስል DW/M. Hailesilase

ቴዎድሮስ  አባተ «ግልፅና አሳማኝ ምክንያት ባላስቀመጡበት ሁኔታ በተማሪዎች ህይወት እና ወላጆች ላይ መፍረድ ነውር ነው።»ሲሉ ጽፈዋል።

አለማየሁ ካሳሁን ደግሞ ጉዳዩ በሕግ መታየት አለበት የሚል እምነት አላቸዉ። «ይህ ውሳኔ በምንም መልኩ ተቀባይነት አለው ብዬ አላምንም። ዝምታ በፍፁም መፍትሄ አይሆንም እናም ጉዳዩ ወደ ሕግ ሊቀርብ ይገባዋል። የመኮራረጅ እና መሰል የውጤት ማጭበርበሮች ካሉ በግልፅ ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን ለይቶ ውጤት እስከ መሰረዝ እና በሕግ ተጠያቂ የማድረግ እርምጃ መውሰድ እንጂ እንዲህ  ውሳኔ ተቀባይነት አይኖረውም። እንደ እኔ እምነት በዚህ ውሳኔ በጅምላ ተጎጂ የሆኑ ተማሪዎች መብታቸዉን በህጋዊ መንገድ ለማስከበር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መዉሰድ አለባቸዉ።»ብለዋል።

Schulprüfung unter spezielle Militär Garde
ምስል DW/M. Hailesilase

አብርሃም ይስሃቅ «በልጆች እጣፈንታ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እንዲህ ቀላል ነገር ሆነ? "የሰረቁ" የተባለውን ለይቶ እርምጃ መውሰድ ይቀላል ወይስ በጅምላ መቅጣት።  በሂሳብና በፊዚክስ እምብዛም የሆኑ ነገር ግን በንባብ ጎበዞች ታሪክ፣ ባዮሎጂ፣ ሲቪክስ ወዘተ በደንብ ተዘጋጅተው የሰሩ ተማሪዎች በዚህ የጅምላ ቅጣት የዩኒቨርስቲ እድላቸው መምከኑ ቀላል ነገር ተደርጎ መወሰዱን ማሰብ በጣም ይጨንቃል - ምቾት ይነሳል። ተማሪዎችን በጅምላ የጦስ ዶሮ እንዳደረጓቸው ይሰማኛል።»ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ