1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

በመድን ዋስትናው ላም፤በሬ፤ፍየል፤በግ እና ግመልን ያካትታል

ረቡዕ፣ ሰኔ 28 2009

የዓለም የምግብ ድርጅት ድርቅ ለሚያሰጋቸው 5,000 አርብቶ አደሮች የቤት እንስሳት የመድን ዋስትና ሊሰጥ በዝግጅት ላይ ነው። ድርጅቱ የመድን ዋስትናውን ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች ጋር ሥምምነት ፈርሟል። በመርኃ-ግብሩ በሶማሌ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች 100,000 አርብቶ አደሮችን ለመጥቀም እቅድ ተይዟል።

https://p.dw.com/p/2fzaL
Pastoralisten Somalia Kamel
ምስል DW/J.Jeffrey

የቤት እንስሳት የመድን ዋስትና መርሐ-ግብር

 ከአራት ወራት በኋላ የቀብሪ ድሐር፤አዳድሜ እና ምዕራብ ኢሚ ወረዳ ነዋሪ 5,000 አርብቶ አደሮች ለግመሎቻቸው፤ፍየል እና በጎቻቸው በሬ እና ላሞቻቸው የመድን ዋስትና ሽፋን ያገኛሉ ተብሏል። የሶስቱ ወረዳ ነዋሪዎች በደረቅ እና ከፊል ደረቅ ሥነ-ምሕዳሮች እንደሚኖሩ አርብቶ አደሮች ሁሉ ለአስከፊ ድርቅ ተጋላጭ ናቸው። ምሥራቅ አፍሪቃን ብሎም ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ የሚጎበኛት እያንዳንዱ ድርቅ የአርብቶ አደሮች የኅልውና መሰረት ለሆኑት የቤት እንስሳት ሞት ዋንኛው ምክንያት ነው። የዓለም የምግብ ድርጅት የመድን ዋስትናውን ከሚያቀርቡት አራት ኩባንያዎች ጋር ሥምምነት ፈፅሟል። ኦሮሚያ፤ኒያላ እና አፍሪካ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለአርብቶ አደሮቹ የመድን ዋስትናውን ለማቅረብ ሥምምነት የፈጸሙ ኩባንያዎች ናቸው። ለመርኃ-ግብሩ የመጀመሪያ ዓመት 69.6 ሚሊዮን ብር የመደበው የዓለም የምግብ ድርጅት ኩባንያዎቹ ለሚያቀርቡት የመድን ዋስትና ክፍያ ሲፈፅም አርብቶ አደሮቹ በበኩላቸው በኢትዮጵያ መንግስት የምግብ ለሥራ መርኃ-ግብር የጉልበት ሥራ ያበረክታሉ።

በሶስቱ ወረዳዎች የሚጀመረው የቤት እንስሳት የመድን ዋስትና መርኃ-ግብር ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። መርኃ-ግብሩ አርብቶ አደሮች የድርቅን ሥጋት ተቋቁመው የቤት እንስሶቻቸውን ከሞት እንዲታደጉ ያግዛቸዋል። አርብቶ አደሮች ዋስትና የሚከፈላቸው የተከሰተው ድርቅ አስከፊነት ከአስራ አምስት አመታት የአየር ጠባይ መረጃ ጋር ተነፃጽሮ ነው።

Pastoralisten Somalia
ምስል DW/J.Jeffrey

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ በአየር ጠባይ መረጃ ላይ መሰረት አድርጎ የሚሰጠው የቤት እንስሳት የመድን ዋስትና መርኃ-ግብርን ለቦረናና የምዕራብ ጉጂ ዞን አርብቶ አደሮች ያቀርባል። ኩባንያው በቅርቡ ለቦረናና እና የምዕራብ ጉጂ ዞን ከ1400 በላይ ለሚሆኑ አርብቶ አደሮች ወደ 1.6 ሚሊዮን ብር ካሳ ከፍሏል። አቶ ጌታነህ ኢረና በኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከፍተኛ የቤት እንስሳት የመድን ዋስትና ባለሙያ ናቸው።

የዓለም የምግብ ድርጅት በሶማሌ ክልል ሶስት ወረዳዎች የሚጀምረው መርኃ-ግብር ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ እና የመክፈል አቅም የሌላቸውን ለይቶ ያካትታል። በመጪው ጥቅምት ወር በ5000 አርብቶ አደሮች ይጀመር እንጂ በሒደት ወደ 100,000 እንዲያድግ እቅድ ተይዞለታል። አርብቶ-አደሮቹ በመርኃ-ግብሩ ውስጥ ለመካተት ፈቃደኛ መሆን እንደሚጠበቅባቸው የሚናገሩት አቶ እዝጊመለስ የግድ ውስብስቡን አሰራር ማወቅ እንደማይጠበቅባቸው ያስረዳሉ።

በጃፓኑ የሶፊያ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ካዙሺ ታካሐሺ በአየር ጠባይ መረጃ ላይ መሰረት አድርጎ የሚሰራው የቤት እንስሳት የመድን ዋስትና መርኃ-ግብር ድርቅ ለሚፈትናቸው የደቡብ ኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ሁነኛ መፍትሔ ነው ባይ ናቸው። ጃፓናዊው ምሁር ባለፈው ዓመት ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ባጠናቀሩት ጥናታዊ ጽሁፍ ይኸው መርኃ-ግብር ከሌሎች የግብርና የመድን ዋስትና አይነቶች በተለየ አርብቶ አደሮችን ይጠቅማል ሲሉ ፅፈዋል። አቶ እዝጊመለስ ተክለዓብ እንደሚሉት የዓለም የምግብ ድርጅት በመጪው ጥቅምት ሥራ ላይ የሚውለውን መርኃ-ግብር አስቀድሞ ሞክሮታል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ