1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቤንች ማጂ ዞን ፈርሶ እንደ አዲስ ተዋቀረ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 3 2011

የቤንች ማጂ ዞን የደቡብ ክልል በሰራው የመዋቅር ማሻሻያ መሰረት ፈርሶ እንደ አዲስ ተዋቀረ። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የምዕራብ ኦሞ እና የቤንች ሸኮ የሚባሉ ሁለት ዞኖች ተመስርተው ሥራ መጀመራቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

https://p.dw.com/p/3ILjx
Äthiopien - Mizan Teferi
ምስል DW/S. Wegayehu

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የሚገኘው የቤንች ማጂ የዞን መስተዳድር በይፋ መፍረሱን የዞኑ ምክር ቤት አስታወቀ። መስተዳድሩ የፈረሰው በክልሉ መንግስት የተካሄደው የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት ለዞኑ ምክር ቤት ጉባኤ ቀርቦ ውሳኔ በማግኝቱ ነው።  የቤንች ማጂ ዞን ለሁለት ተከፍሎ የምዕራብ ኦሞ እና የቤንች ሸኮ በተባሉ ሁለት ዞኖች መተካቱን እና ዞኖቹም በዚህ ሳምንት ሥራ መጀመራቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።  

ከጋምቤላ ክልላዊ መንግስትና ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ጋር የሚጎራበተው የቤንች ማጂ ዞን በደቡብ ክልል ነባር ከሚባሉት የዞን መዋቅሮች አንዱ ነበር። ይሁንና የዚሁ ዞን መስተዳድር መዋቅር ከያዝነው ሳምንት ጀምሮ በይፋ መፍረሱን የቤንች ማጂ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የነበሩት ወይዘሪት ወርቅነሽ ባዴት አስታውቀዋል።

"የክልሉ ምክር ቤት ለክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ምክር ቤት በሰጠው ውክልና መሰረት፤ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ምክር ቤት ጥናት አጥንቶ ባገኘው የጥናት ውጤት መሰረት፤  በቤንች ማጂ ዞን አራተኛ ዙር ስድስተኛ አመት የስራ ዘመን ስድስተኛ አስቸኳይ ጉባኤ ተደርጎ በዚያ ጉባኤ የቀድሞ ቤንች ማጂ ዞን ለሁለት መከፈሉን ምክር ቤቱ ይፋ አድርጓል" ሲሉ አፈ-ጉባኤዋ ተናግረዋል።

በክልሉ መንግስት ተዘጋጀቷል የተባለው የመዋቅር ማሻሻያ ለምክር ቤት ውሳኔ ከመቅረቡ በፊት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉን የጠቆሙት ወይዘሪት ወርቅነሽ በሕዝቡ ፍላጎት መነሻነት ነባሩን የቤንች ማጂ ዞን መዋቅር በማፍረስ በምትኩ የምዕራብ ኦሞ እና የቤንች ሸኮ በተባሉ ሁለት ዞኖች መዋቀሩን ተናግረዋል። አፈ ጉባኤዋ "እስከ ቀበሌ ያለው ሕዝብ በጥናት ውጤቱ ላይ ሰፊ ውይይት እና ክርክር ከተደረገ በኋላ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በተስማማበት የቤንች ሸኮ ዞን እና የምዕራብ ኦሞ ዞን ተብሎ ለሁለት ተከፍሏል" ብለዋል።  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ ክልል በአይነትም በመጠንም እየጨመሩ የሚገኙት የአስተዳድር መዋቅር ጥያቄዎች ላይ አዎንታዊም አሉታዊም አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ።

በርካቶች የአስተዳድር መዋቅር ጥያቄዎቹ ከመንግስት የሚቀርቡ የማህበራዊ አገልግሎቶችን በቅርበት ለማግኘት ያስችላል ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ አስተዳደራዊ ወጪዎችን በማናር የልማት በጀቶችን ከመሻማት የዘለለ ፋይዳ የላቸውም ሲሉ ይሞግታሉ።

Äthiopien - Ato Deyamo Dale
ምስል DW/S. Wegayehu

በደቡብ ክልል መስተዳድር ፅህፈት ቤት የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ደያሞ ዳሌ "በእኔ እይታ የምዕራብ ኦሞ ዞን መመስረት ተገቢ ነው። የቤንች ማጂ ዞን በጣም ሰፊ ነበር። በአርብቶ አደር አሰፋፈር ምክንያት አገልግሎት ለማድረስ የሚያመች አልነበረም" ሲሉ የአዋቃቀር ለውጡ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል። አቶ ደያሞ በመዋቅር ጥያቄዎች ዙሪያ ጥቂቶች መሰረታዊ የሚባሉ አሳማኝ ምክንያቶች ቢኖራቸውም አብዛኞቹ ግን የመንግስት መዋቅሮችን በማስፋት የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር ካላቸው ፍላጎት የሚመነጩ ናቸው ሲሉ ይተቻሉ።

የሕዝቡን ፖለቲካዊ ንቃትና ማህበራዊ ፍላጎቶችን ተከትለው ለሚነሱ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የጠቆሙት የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ደያሞ ይሁን እንጂ አፈፃጸሙ በጥናት፣ በፖሊሲ እና በአዋጅ ሊደገፍ ይገባል ብለዋል። "ማንነትን ለመግለፅ የግዴታ አስተዳደር ያስፈልጋል ካልን 85 ክልል ያስፈልገናል። እንደዚያ አይነት መስፈርት የለንም። ስለዚህ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ፣ ቋሚ መስፈርት ተበጅቶ፣ ተጠንቶ በፌደራልም ይሁን በክልል ምክር ቤት ተወስኖ፣ ወጥ በሆነ መንገድ ተግባራዊ መደረግ አለበት" ሲሉ ባለሙያው አሳስበዋል። "ለግማሹ ተሰጥቶ ለግማሹ መከልከል ማግለል ይሆናል። አመጽ እየቀሰቀሰ ነው፤ ቅሬታ ይቀሰቅሳል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል። 

የደቡብ ክልል ምክር ቤት በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ አካሂዶት በነበረው መደበኛ ጉባኤ ሶስት ዞኖች እና 44 ወረዳዎችን በአዲስ መልክ ለማዋቅር የሚያስችለውን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ተስፋለም ወልደየስ