1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የብሔራዊ ባንኩ ገዢ ምን እያሉ ነው?

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 6 2011

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የውጭ ምንዛሪ ግብይት በሒደት በገበያ ፍላጎት እና በአቅርቦት እንዲከወን የማድረግ ፍላጎት እንዳለ ጥቆማ ሰጥተዋል። እንዲህ አይነት ለውጥ የውጪ ንግዱን እና የአገር ውስጥ አምራቾችን ቢያበረታታም የዋጋ ግሽበት ሊፈጥር እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ

https://p.dw.com/p/3PQi9
Yinager Dessie Belay, äthiopischer Nationalplanungskommissar
ምስል picture-alliance/M.Kamaci

የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ላይ ሊደረግ የሚችሉ ለውጦች

ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በገበያው ፍላጎት መሠረት እንዲከወን የማድረግ ፍላጎት እንዳላት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጥቆማ ሰጥተዋል። በዝግታ በአቅርቦት እና በፍላጎት ወደሚከወን የውጭ ምንዛሪ ግብይት መሸጋገር እንደሚያስፈልግ የገለጹት የብሔራዊ ባንክ ገዢ «ሽግግሩ የሚኖሩትን ጠቀሜታዎች እና ፈተናዎች መመልከት አለብን። በመጪዎቹ ሶስት አመታት የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱን ላላ ማድረግ እንፈልጋለን» ሲሉ በአፍሪካ ላይ ያተኮረው የዓለም የኤኮኖሚ ፎረም በደቡብ አፍሪካ ባለፈው ሳምንት ሲካሔድ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

ለመሆኑ የብሔራዊ ባንኩ ገዢ ምን እያሉ ነው?

«በሶስት አመት ውስጥ በተወሰነ ደረጃ ለቀቅ እናደርገዋለን፤ ሙሉ በሙሉ ግን አንለቀውም የሚል አይነት መልዕክት ነው ያስተላለፉት» የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ «በአሁኑ ወቅት ያለው የግብይት ሥርዓት ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ እና በአቅርቦት እና በፍላጎት እንዳይወሰን ብሔራዊ ባንክ በተወሰነ ደረጃ ይቆጣጠረዋል። በዚያ ምክንያት የኢትዮጵያ ብር በተለይ ከዶላር [አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን] በየአመቱ በአምስት በመቶ ይወድቃል» ሲሉ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ለማሻሻል ጥናት ላይ መሆኗን የሚያስታውሱት አቶ አብዱልመናን እንኳን በሶስት አመት በአምስት አመታትም ቢሆን የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ ሙሉ በሙሉ በገበያው ፍላጎት እንዲመራ ይደረጋል የሚል ዕምነት የላቸውም። አቶ አብዱልመናን «ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ ውጪ የምትልከው ከሶስት ቢሊዮን ዶላር [በታች የሚያወጡ ሸቀጦችን] ነው። የምናስገባው ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር [የሚያወጡ ሸቀጦችን] ነው። የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱ ልቅ ቢደረግ ኖሮ የሚገኘው ዶላር እና የሚፈለገው ዶላር በጣም ስለማይመጣጠን የብር ዋጋ በአንዴ ነበር የሚወድቀው» ሲሉ ያክላሉ።

የግብይት ሥርዓቱ ለውጥ ጥቅም እና ዳፋ

Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

በኖርዌይ ሞልደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የፒኤችዲ ጥናታቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙት አቶ ጣሰው ዱፌራ እንደሚሉት በውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱ ላይ የሚደረግ ለውጥ በኢትዮጵያ ገበያ እና በምጣኔ-ሐብቱ ላይ አዎንታዊም አሉታዊም ተፅዕኖ ይዞ መምጣቱ አይቀርም።

«ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ዋጋቸው ይጨምራል። ይኸ ደግሞ በሁለት መልኩ አገሪቱን ይጠቅማል። መጀመሪያ ወደ አገሪቱ የሚገባው ነገር ስለሚቀንስ ለዚያ የምናወጣው የውጭ ምንዛሪ ይቀንሳል። ሁለተኛው ሀገር ውስጥ ያሉ አምራቾች ይበረታታሉ። የሚያመርቱት ምርት ተጠቃሚ ይኖረዋል። ይኸ ግን ሊሆን የሚችለው ሀገር ውስጥ ያሉ አምራቾች ከውጪ ከሚገባው ምርት ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ዕቃ በሚፈለገው መጠን እና በሚፈለገው ጥራት ሲያመርቱ ነው» ሲሉ ሊኖረው የሚችለውን ጠቀሜታ ያስረዳሉ። ባለሙያው እንደሚሉት «የመጨረሻ ውጤቱ  የወጪ እና ገቢ ንግዱን» ማመጠን ይሆናል።

የዓለም ባንክ ባለፈው ግንቦት ይፋ ያደረገው አንድ ሰነድ እንደሚጠቁመው ተወዳዳሪ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት የሚከተሉ አሊያም የመገበያያ ገንዘባቸው በተለይ ከዶላር አኳያ ያለውን የምዛሪ ተመን የሚያዳክሙ አገራት ጠንካራ እና ዘላቂ ምጣኔ-ሐብታዊ ዕድገት ይኖራቸዋል።

ይሁነኝ ብለው የመገበያያ ገንዘባቸውን የምንዛሪ ተመን የሚያዳክሙ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ፈጣን ምጣኔ-ሐብታዊ ዕድገት ይኖራቸዋል። ከእነዚህ መካከል ቻይና በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ እና ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡት ሸቀጥ ከሚሸምቱት እጅግ ለሚያንስባቸው አገራት ግን ይኸ ጣጣ ይዞ መምጣቱ አይቀርም። አቶ ጣሰው እንደሚሉት አንዱ ፈተና የዋጋ ግሽበት ነው።

«ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ውድ የሚሆኑበት ሁኔታ ስለሚፈጠር እሱን የሚተካ ምርት ሀገር ውስጥ ሳይመረት ተነስተን የመገበያያ ገንዘቡን አቅም የምናዳክም ከሆነ በተለይ ከተማ የሚኖሩ፤ ከገበያው ጋር የማይለዋወጥ ቋሚ ገቢ ያላቸው ሰዎች በጣም ይጎዳሉ» ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። ከዚህ ባሻገር በውጭ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓቱ ላይ የሚደረግ ለውጥ በመንግሥት ሥራዎች ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀርም። «ኢትዮጵያ ደሴት አይደለችም። በሁሉም ነገር ራሷን የቻለች አይደለችም። ምንም እንኳን ከውጭ የምናስገባውን ነገር ብንቀንስም የግድ ደግሞ በመንግሥት ደረጃ መሰረተ-ልማት ለመስራት፤ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን ለመስራት ልንሸምታቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ» የሚሉት አቶ ጣሰው «በአግባቡ ካልተያዘ የመንግሥት ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር ይችላል» ባይ ናቸው።

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

የኢትዮጵያ ምጣኔ-ሐብት በፖለቲካዊው ቀውስ ሳቢያ ባለፈው አንድ አመት የከፋ መንገራገጭ ገጥሞታል። ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ የገንዘብ ምኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት አገሪቱ ከውጭ ንግድ ያገኘችው ገቢ ከቀደመው አመት አኳያ 8.3 በመቶ አሽቆልቁሏል። የዋጋ ግሽበቱም እድገት እያሳየ ነው። አቶ አብዱልመናን እንደሚሉት በውጭ ምንዛሪ እጥረት እና በገቢ እና ወጪ ንግድ ሚዛን መጓደል የሚፈተነውን ምጣኔ-ሐብት ለመታደግ መንግሥት እግጅ በርካታ እና ውስብስብ የቤት ስራዎች አሉበት። የወጪ ንግዱን ማሻሻል፤ የበጀት ጉድለትን በማስተካከል እና የመንግሥት ወጪን በመቀነስ የዋጋ ንረት መቆጣጠር እና «ግብርናውን አንቆ የያዘውን የምርታማነት ችግር መፍታት» ያስፈልጋል።

አቶ ጣሰው ዱፌራ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ ሙሉ በሙሉ በገበያ ፍላጎት እንዲከወን ከመፍቀዷ በፊት ለፖለቲካዊው ውጥንቅጥ መፍትሔ እንድታበጅ ይመክራሉ። «እንግዲህ ከምርጫ በኋላ ምን አልባት ከተረጋጋ አላውቅም። መጀመሪያ ግን ፖለቲካው ሊረጋጋ ይገባል። ሲቀጥል አገር ውስጥ ያሉት አምራቾች የዜጎችን በአቅርቦት ለማስደሰት ዝግጁ መሆን አለባቸው» ብለዋል። «ዛሬውኑ የብርን ዋጋ ብናዳክም (devalue) የዋጋ ንረት ሳይሆን ሃይፐርኢንፍሌሽን (hyperinflation) የሚባለው እነ ዚምባብዌ ያጋጠማቸው ወደኋላ መቀልበስ የሚያስቸግረው የኑሮ ውድነት ሊከሰት ይችላል» ሲሉ አቶ ጣሰው ያስጠነቅቃሉ።

እሸቴ በቀለ