1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታኒያ ሕዝበ-ውሳኔ ተፅዕኖ

ረቡዕ፣ ሰኔ 29 2008

ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ለመውጣት ያሳለፈችው ውሳኔ መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን ባይታወቅም ጫናው ግን እዚህም እዚያም እየተሰማት ነው። በለንደን የከተሙ ጀማሪ ኩባንያዎች ህዝበ-ውሳኔው የባለወረቶችን ውሳኔ ያስቀይራል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/1JKDh
Fahne von Großbritannien mit zerrissener EU-Fahne
ምስል picture alliance/chromorange/C. Ohde

የብሪታኒያ ሕዝበ-ውሳኔ ተፅዕኖ

ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ለመውጣት በሕዝበ-ውሳኔ ያሳለፈችው ውሳኔ በኢኮኖሚ ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞች ዘንድ የከረረ ውዝግብ አልፎም ስጋት ፈጥሯል። ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ትውጣ የሚለውን መፈክር አንግበው የአገሪቱን ዜጎች የቀሰቀሱት ፖለቲከኞች ግን የጀመሩትን ሳይጨርሱ ሹልክ ብለዋል። የዴቪድ ካሜሮንን መንበር ለመረከብ ሽር ጉድ ይሉ የነበሩት ቦሪስ ጆንሰን ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት እንደማይወዳደሩ አስታውቀዋል። ናይጅል ፋራጅም ቢሆኑ የፖለቲካ ሕይወቴ አብቅቷል ብለዋል። ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ለመውጣት ረጅም ግን ደግሞ ውስብስብ ድርድር ማድረግ ቢጠበቅባትም ድርድሩን ጨክኖ የሚያስጀምረው ፖለቲከኛ ማንነት ለጊዜው አልታወቀም። በፖለቲከኞቹ ግፊት የተወሰነው ውሳኔ ግን እዚህም እዚያም ጫና እየፈጠረ ነው።

በዓለም ሁለተኛ ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ የሆነው ቮዳፎን ዋና መቀመጫውን ከለንደን ለመቀየር እያሰበ መሆኑን አስታውቋል። ቮዳፎን ለንደንን ከለቀቀ የጀርመኗ ዱስልዶርፍ አማራጭ ልትሆን ትችላለች። ጀርመን የቮዳፎን ትልቅ ገበያ ከመሆኗም ባሻገር ኩባንያው በዱስልዶርፍ ከተማ ወደ 5,000 ገደማ ሰራተኞች አሉት።

የብሪታንያውያን ውሳኔ ጫና የፈጠረው ግን በግዙፍ ኩባንያዎች ላይ ብቻ አይደለም። የብሪታኒያ ዋና ከተማ ለንደን በምታቀርባቸው ዘመናዊ የፋይናንስ አገልግሎቶች ለጀማሪ ኩባንያዎች ተመራጭ ሆና ቆይታለች። መቀመጫቸውን በለንደን ያደረጉ በርካታ ጀማሪ ኩባንያዎች ግን የብሪታኒያ ውሳኔ መጪውን ጊዜ በጥርጣሬ እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል። ውሳኔው ጀማሪ ኩባንያዎቹ አጥበቀው የሚፈልጓቸውን ባለወረቶች ሊያሳጣቸው ይችላል የሚል ስጋት አለ። በሕዝበ-ውሳኔው የለንደን አብላጫ ድምጽ ሰጪዎች በአውሮጳ ኅብረት መቆየትን ነበር የመረጡት። ወጣቱ ፓውል ሮይተር ዜሊክስ የተሰኘ ኩባንያ መስራች ነው
«በግሌ እጅግ ተከፍቻለሁ። እኔ ብሪታኒያ በአውሮጳ ኅብረት መቆየቷን እመርጥ ነበር። እኔ ነፃ አሳቢ የሆነውን ወጣት ትውልድ እወክላለሁ። በአውሮጳ ኅብረት ሁሉም ነገር መልካም ባይሆን እንኳ የተገነጠለ ደሴት ከመሆን ግን እጅግ የተሻለ ነበር። በውጤቱ እጅግ ተከፍቻለሁ።»

Großbritannien Zentrale von Vodafone in Newbury
ምስል Getty Images/AFP/M. Hayhow

መቀመጫቸውን በለንደን ያደረጉ ጀማሪ ኩባንያዎች ሰፊ የፋይናንስ አማራጭ እና ለዓለም አቀፍ ገበያ ቅርብ ናቸው። ስራ ፈጣሪዎቹ በለንደን የተሰባሰቡት ባለወረቶች ወደ ፊት ገንዘባቸውን ወደ ሌሎች አገሮች ያዘዋውራሉ የሚል ስጋት አላቸው። ፓውል ሮይተር መጪው ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ ባለማወቁ ስጋት ገብቶታል።

«ይህ ሰፊ የጥርጣሬ ጊዜ ነው። በአሁኑ ወቅት ምን እንደሚፈጥር የሚያውቅ የለም። ፍርኃቱ ይህ ነው። በአውሮጳ ኅብረት ጥሩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደምናገኝ ይሰማኛል። አሁን ግን በርካታ የማይታወቁ ነገሮች እየመጡ ነው። ከአውሮጳ ኅብረት ለመውጣት ረጅም እና ውስብስብ ሒደት ከፊታችን ይጠብቀናል። ሒደቱንም ይሁን ውጤቱን ምንም አናውቅም።»

አሜሪካዊቷ አይሊን በርቤጅ በጀማሪ ኩባንያዎች እና ባለወረቶች መካከል አማካሪ ሆነው ያገለግላሉ። መቀመጫቸውን በለንደን ያደረጉት አይሊን አዋጪ እና አዲስ የሥራ ኃሳብ ይዘው ብቅ ያሉ ኩባንያዎችን በመለየት ባለወረቶች በገንዘብ እንዲደግፏቸው ይወስናሉ። ፓሽን ካፒታል የተሰኘው ኩባንያቸው 60 ሚሊዮን ፓውንድ ያንቀሳቅሳል። አይሊን በርቤጅ ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር የምትደራደርባቸው ሁለት አመታት ለጀማሪ ኩባንያዎች ፈተና ሊፈጥሩ ቢችሉም እድገቱን ግን እንደማይገታው ያምናሉ።

«ያለፉት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ያሉ ወራት ለጀማሪ ኩባንያዎች የስጋት ጊዜያት ነበሩ። ሥጋቱ አሁንም አልቆመም። ምርጥ የሥራ ፈጣሪዎች እና ጀማሪ ኩባንያዎችም ፈተና ገጥሟቸዋል። ብሪታኒያ 27 አባል አገራትን ካቀፈው የአውሮጳ ኅብረት ጋር የምትደራደርባቸው የሚቀጥሉት ሁለት አመታት ለእነዚህ ኩባንያዎች ተመራጭ ጊዜ አይደለም። ቢሆንም ምንም ነገር ማቆም አይችልም። የጀማሪ ኩባንያዎች እድገት ይቀጥላል።»

የብሪታኒያ ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት በብሪታኒያ እና 27ቱ የአውሮጳ ኅብረት አባል አገራት ላይ የሚኖረው ትርጉም ዛሬም ግልጽ ብሎ አልታወቀም። ነገር ግን ከሁለት አመታት ድርድር በኋላ የሚወሰነው ውሳኔ የሰራተኛ ገበያውን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚቀይረው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይስማማሉ። በርካታ የአውሮጳ ኅብረት አባል አገራት ዜጎች በብሪታኒያ ተቀጥረው ይሰራሉ። የፋይናንስ ኢንደስትሪው ብቻውን ከ350,000 በላይ ብሪታኒያዊ ያልሆኑ የአውሮጳ ኅብረት ዜጎችን ቀጥሯል። ማርክ ዌደን ሪሰርች ፕሮፐርቲ ፓርትነርስ የተሰኘ ኩባንያ ኃላፊ ናቸው።

«ከሌሎች የአውሮጳ አባል አገራት ወደ ብሪታኒያ መጥተው የሚሰሩ እና የሚኖሩ ሰዎች ጉዳይን ስትመለከት አሰራሩ በአንዴ ሲቀየር አስቸጋሪ ይሆናል። ነገር ግን የአውሮጳ ኅብረት ውስብስብ ሆኗል። ምን አልባት ትክክለኛ መሪዎችን ካገኘን እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የመሪነት ሚና ካገኙ ይህን እድል ትልቅ ነገር ለማሳካት ልንጠቀምበት እንችላለን።»

የብሪታኒያ ሕዝበ-ውሳኔ ከመካሄዱ በፊት የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ውጤቱ የሚኖረውን ተጽዕኖ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል። ፓውንድ ከዩሮ አንጻር የነበረውን የምንዛሬ ዋጋ አጥቷል። ከብሪታኒያ ኢኮኖሚ የ8% ድርሻ ያለው የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ከአውሮጳ ኅብረት የወጥ ገበያ ሥርዓት ያለው ተሳትፎ መገደቡ የሚቀር አይመስልም። አሁንም ማርክ ዌደን

Großbritanien Brexit-Gegner demonstrieren gegen EU-Austritt des Landes
ምስል Reuters/D. Martinez

«ፓውንድ ለተወሰነ ጊዜ ሊዋዥቅ ይችላል። ይህ የንግድ ሥርዓቱን በተለይም ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጫና ያሳድራል። በአንጻሩ ምርቶችን ወደ ውጪ የሚልኩ ነጋዴዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ምን አልባት ለንብረት ግብይትም መልካም እድል ይፈጥር ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ከአውሮጳ ኅብረት ውጪ ያሉ ባለወረቶች ወደ አገራችን መጥተው ንብረት እንዲገዙ ይጋብዛል።»

ዛሬም ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት መውጣቷን የሚደግፉ ፖለቲከኞች ውሳኔው ለአገራቸው ኤኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይሰጣል በሚለው ክርክራቸው ጸንተዋል። ከአውሮጳ ኅብረት ጋር ብቻ ሳይሆን እንደ ሕንድ እና አውስትራሊያን ከመሰሉ ከቀድሞ የብሪታኒያ ቅኝ-ተገዢዎች ጋር የጠበቀ የንግድ ግንኙነት ሊኖር ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ። ጀርመናዊው የኤኮኖሚ ባለሙያ ሚሼል ቬልገሙት ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ወጥ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ስለሚኖራት ተጠቃሚነት ለመናገር የሁለቱን ዓመታት ድርድር መጠበቅ ግድ ይላል ባይ ናቸው።»

«በብሪታኒያ እስከ 300 ሚሊዮን የሚደርሱ የሥራ እድሎች ከአገሪቱ የንግድ ሥርዓት ጋር የተቆራኙ ናቸው። ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ከወጣች በኋላ የግብይት ሥርዓቱ በአንድ ጊዜ የሚቆም አይደለም። የግብይት ሥርዓቱ ምን አልባት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መቀጠሉ አይቀርም። ሁኔታዎቹ የሚወሰኑት ብሪታኒያ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር በሚኖራት የንግድ ውል ላይ ነው። ይህ ዛሬ በግልጽ አይታወቅም። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የውሳኔውን ተጽዕኖ ለመገመት መሞከር አይከፋም ቢሆንም እጅግ አስቸጋሪ ነው።»

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኩባንያዎች በአውሮጳ ኅብረት የወጥ ገበያ ሥርዓት መሰረት ያለምንም ችግር በአባል አገራት ዘንድ ይሰራሉ። የብሪታንያዋ ለንደን ብርቱ ተፎካካሪዎች ቢኖሯትም የአህጉሩ የፋይናንስ ማዕከል ሆና ቆይታለች። ከብሪታኒያ ሕዝበ-ውሳኔ በኋላ የጀርመኗ ፍራንክፉርት የለንደንን ቦታ ለመረከብ የተዘጋጀች ይመስላል። ሚሼል ቬልገሙት ለንደን በአውሮጳ ኅብረት የወጥ ገበያ ሥርዓት ተጠቃሚነቷን ካጣች ህይወት ከባድ ይሆናል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

England Jaguar Land Rover Autofabrik in Solihull
ምስል picture-alliance/dpa/D. Jones

«በአውሮጳ ግብይት ውስጥ ለመሳተፍ ወጥ የገበያ ሥርዓቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አበርክቷል። አንዳንድ የለንደን ሰዎች የኛ ገበያ የዓለም ገበያ ነው፤ለመላው ዓለም የፋይናንስ ግብይት ማዕከል መሆን እንፈልጋለን፤ አውሮጳ ያን ያክል ጠቀሚ አይደለም ሲሉ ይደመጣል። ነገር ግን የአውሮጳ ገበያ እጅግ ግዙፍ እና ጠቃሚ ነው። ለንደን በዚህ ገበያ ውስጥ የመጠቀም እድል ከተነፈገች እጅግ ከባድ ይሆንባታል።

ብሪታኒያ ለጊዜው ለገጠማት የፖለቲካ አመራር ቀውስ መፍትሔ በማፈላለጉ ላይ ያተኮረች ይመስላል። በሕዝበ-ውሳኔው ጉልህ ሚና የነበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፤ቦሪስ ጆንሰን እና ናይጅል ፋራጅ ሽንጣቸውን ገትረው በተከራከሩ ማግስት ዘወር ማለታቸው እያስተቻቸው ነው። የሌበር ፓርቲ መሪው ጄሮሜ ኮብሪን በአመራሮቻቸው የመተማመኛ ድምጽ ቢነፈጉም መንበሬን አለቅም ብለዋል። የፖለቲካ እሰጥ አገባው ጋብ ብሎ ቀጣዩ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲመጣ ግን ብራስልስ ከከተመው የአውሮጳ ኅብረት ጋር ውስብስብ ድርድር ማካሄድ ይጠበቅበታል።

እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ