1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታንያ ነገሥታት ቤት አብዮት

ሰኞ፣ ጥር 11 2012

የንግሥቲትዋ የልጅ ልጅ ልዑል ሄሪ እና ባለቤቱ ሜጋን፤ እዚህ ሃገር የነገሥታት ሥራ የሚባለዉን ሥራቸዉን በከፊል ለማቋረጥና በግማሽ እየሰሩ የግላቸዉን ሥራ መስራት መፈለጋቸዉ ኑሮአቸዉንም ካናዳ ግማሹን ጊዜ ደግሞ ብሪታንያ ለማድረግ በመፈለጋቸዉ ግርምታን ፈጥሮአል። «ታሪክ ራሱን እንዳይደግም እሰጋለን» የልዑላኑ መልስ ነዉ

https://p.dw.com/p/3WKGU
Großbritannien Kind von Prinz Harry und Meghan Markle in Berkshire
ምስል Reuters/D. Lipinski

በዉሳኔያቸዉ ጀግኖች ያልዋቸዉንያ ያህል ታሪክ አጠልሽተዋል ያሉም ጥቂት አይደሉም


«በቅርቡ በብሪታንያ ነገሥታት ቤተሠቦች መካከል የተከሰተዉ አዲስ አና አስገራሚ ነገር፤ የንግሥቲትዋ የልጅ ልጅ ልዑል ሄሪ እና ባለቤቱ ሜጋን፤ እዚህ ሃገር የነገሥታት ሥራ የሚባለዉን ሥራቸዉን በከፊል ለማቋረጥ እና በግማሽ እየሰሩ የግላቸዉን ሥራ መስራት መፈለጋቸዉ እንዲሁም ግማሹን ኑሮአቸዉን ካናዳ ግማሹን ኑሮአቸዉን ደግሞ ታላቅዋ ብሪታንያ ዉስጥ ማድረግ በመፈለጋቸዉ ነዉ። ይህን ጥያቄያቸዉን ለማንም ሳይናገሩ፤ የነገሥታቱን ቤት ሕግና እና ሥርዓቶች ሳይከተሉ፤ ይፋ በማድረጋቸዉ ዜናዉ ለእንጊሊዝ ሕዝብ እንግዳ ሆኖበት ነዉ የሰነበተዉ ፤ ለዝያ ነዉ። »     
ወ/ሮ ትዝታ ሽመልስ በብሪታንያዉያኑ ነገሥታት ቤት አብዮት የመሰለዉ ርምጃ ምክንያትን ሲገልፁ ከተናገሩት የተወደ ነዉ። የብሪታንያ ነገሥታት ቤት ዉዝግብ ሰሞኑን የእንጊሊዛዉያኑን ብዙኃን መገናኛ ብቻ ሳይሆን የምዕራባዉያኑን ሚዲያ ያጨናነቀ ዋንኛ የመነጋገርያ ርዕስ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ። በብሪታንያ መዲና ለንደን ከተማ ላይ በምህንድስና ሞያ በማገልገል ላይ የሚገኙት ወ/ሮ ትዝታ ሽመልስ በእንጊሊዛዉያኑ ቤት አብዮት የመሰለዉ ርምጃ ምክያት ይላሉ በመቀጠል፤ «የንግሳዉያኑ ቤተሰቦች ለንግስቲትዋ የሚከፈል፤ ሙሉ በሙሉ ሕዝቡ የሚሰጠዉ ታክስን እየተጠቀሙ ነዉ በአብዛኛዉ ሥራን የሚሰሩት። ቤታቸዉን የሚያድሱትም  ከሆነ፤ መንገድ ጉዞም ካለባቸዉ፤ ኑሮአቸዉንም ለመኖር ሕዝብ ከሚሰጣቸዉ የግብር ገንዘብ ነዉ የሚጠቀሙት። እንደሚመስለኝ ወጣቶቹ የንጉሳዉያን ቤተሰቦች ከዚህ ወጭ ለመላቀቅ ነዉ የፈለጉት ። ሌላዉ ደግሞ ልዑል ሃሪ ከእናቱ ጋር በነበረዉ አጭር እድሜ ግንኙነት እና እናቱን በአደጋ በማጣቱ እና በጣምም ስላዘነ ይመስለኛል። በፎቶ ጋዜጠኞች የሚከበበዉ እና የሚደረገዉ ነገር ሁሉ ከድሮም ያስደሰተዉ አይመስለኝም። ልዑል ሄሪ ሜጌንን ካገባ በኋላ ግን ለዚህ መፍትሄ ለመስጠት ሃሳብ የመጣለት ይመስለኛል። ሌላ የሕይወት መንገድም እንዳለ ለማወቅ ከሚስቱ ርዳትን ያገኘ ይመስለኛል። ሌላ ሌላ ሥራን መስራትን እንደሚችል በከፊል ንግሥቲትዋን ማገዝ እንደሚችል የተረዳ ይመስለኛል።»

UK Monarchie l Prinz Harry und Herzogin Meghan
ምስል picture-alliance/AP/M. Dunham

       
የብሪታንያ ጋዜጦች ወጣቱ ልዑል ከማግባቱ በፊት ከፍቅረኛዉም ሆነ ከጓደኞቹ ጋር ዳንስ ቤት ሲገኝ፤ አልያም ወጣ ያለ ነገር ይሰራ ስለነበር የፎቶ ጋዜጠኞች ተደበቀዉ እያነሱ ፎቶዉን በብዙ ሽህ ዶላር ለጋዜጣ ወይም ለተለያዩ ሚዲያዎች ይለቁበት ነበር። የብሪታንያ አልጋ ወራሽ የልዑል ቻርልስ ባለቤት የነበረችዉ እናቱ ሟችዋ ልዕልት ዲያናም እንዲሁ በፎቶ ጋዜጠኞች በዓለም ላይ በብዛት የሚስጥር ፎቶዎች ከተነሱ ግለሰቦች ከመጀመርያዎቹ ተርታ ትሰለፋለች። እናቱ ልዕልት ዲያና በተሽሎክላኪ ፎቶ ጋዜጠኞች ብዙ ችግር ታይ እንደነበር የሚያዉቀዉ፤ ልጅዋ ልዑል ሃሪ የእናቱ እጣ ፈንታ እንዳይደርስበት ስጋት እንዳለበት ተናግሮአል። ልዑሉ ስጋት ያደረበት በመጀመርያ የልዕልት ዲያና ልጅ በመሆኑ፤ ሁለተኛ ያገባት ሚስቱ የጥቁር ክልስ በመሆንዋ በወግ አጥባቂዉ የብሪታንያዉያኑ ቤተ- መንግሥት መቀላቀልዋን አብዛኛዉ ወጣት ዜጋ የወደደዉ ቢሆንም፤ የስንት መቶ ዓመታት ታሪክና ባህል ያለዉ ንጉሳዉያኑ ቤት “ተደፈረ” የሚለዉ ጥቂት አለመሆኑ ነዉ የተነገረዉ።  ከፎቶ ጋዜጠኞች ጋር መሽሎክለኩ ድካም ያሳደረበት ልዑል ሃሪ ለአንድ መገናኛ ብዙሃን በሰጠዉ ቃለ-ምልልስ “በጣም የሚያስፈራኝ ነገር ታሪክ እራሱን እንዳይደግም ብቻ ነዉ።  በጣም የምወደዉ ሰዉ የእዉነተኛ ሰዉነቱን ተነፍጎ እንደሸቀጥ ሲንገላታ አይቻለሁ። በዚህ ምክንያት እናቴን አጥቻለሁ። በተመሳሳይም በዚህ ጠንካራ ኃይል ዉስጥ አሁን ባለቤቴ ስትወድቅ እያየኋት ነዉ።” ሲል ነበር የተናገረዉ።   
ብሪታንያ መዲና ለንደን ዉስጥ ረዘም ላለ ጊዜ በመምህርነት ሞያ በማገልገል ላይ የሚገኙት ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ቤት ሃይሌ ይባሉ። ቤት ሃይሌ በብሪታንያ በሚያደርጉት የበጎ አድራጎት ስራ፤ በንግስት ኤልሳቤት ሁለተኛ ጋባዥነት በነንጉሳዉያኑ ቤት ግብር በልተዋል።  
«ልዑል ሃሪም ሆነ ባለቤቱ ይህን ዉሳኔ መወሰናቸዉን አብዛኛዉ ሕብረተሰብ ሚዲያዉም ቢሆን ብዙ አይነቅፈዉም።  በተለይ ወጣቱ ትዉልድ ይደግፋቸዋል። በራሳቸዉ ገንዘባቸዉን ሰርተዉ በራሳቸዉ መተዳደር ቢችሉ ፤ በተለይ አጋጠመን ከሚሉት ተፅኖ ራቅ ብለዉ ቢኖሩ ሰዉ ይቀበላል። በሌላ በኩል የልዑል ሄሪንና ባለቤቱን ያልተቀበሉ በበኩላቸዉ በድንገት ያለዉን የንጉሳዉያን ስርዓት ሁሉ እንደመሻር ፤ ሳያማክሩ ያደረጉት ነገር ሲሉ ይተችዋቸዋል። እንደ ባህሉ በቅድምያ ለንግስቲትዋ ተነግሮአት ከዝያም ደግሞ የስዋ ፈቃድ ተጠይቆ ነዉ፤ ወደ ሚዲያ እና ወደ ብዙሃኑ ጆሮ የሚደርሰዉ። ይህን ባለማድረጋቸዉ ሕዝቡ አዝኖባቸዋል። ሌላዉ ንግሥቲቱ ያለባቸዉን ትልቅ ጫና እና ችግር አልተገነዘቡላቸዉም፤ ትንሽ ቆየት ቢሉ ኖሮ ጥሩ ነበር። ለምሳሌ ባለቤታቸዉ ጤና የላቸዉም፤ አሁን በቅርቡ ታመዉ ሆስፒታል ገብተዉ ነበር። የፈረንጆቹ የገና በዓል አካባቢም እንዲሁ ሆስፒታል ገብተዉ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፤ ልዑል አንድሪዉ የሚባለዉ የንግሥቲቱ ወንድ ልጅ አንዳንድ በፈፀማቸዉ አፀያፊ ነገሮች በቅርቡ ከንጉሳዉያኑ ሥራ እንዲባረር ሆንዋል። ልዑል አንድሪዉ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሴቶችን ተገናኝተሃል የሚል ትልቅ ክስ ተነስቶበት ነበር። ይህ ሁሉ በቅርብ የሆነ ነገር ነበር። ንግሥቲቱ ይህን ሁሉ ነገር ይዛ ሳለ የነልዑል ሄሪ ትዕግስት አጥቶ እንደገና መነሳት ትንሽ ትክክል አልነበር። ለሚያልፍ ጊዜ፤ ትንሽ ቆየት ማለት ይችሉ ነበር። »  

Kanada Prinz Harry und Meghan Markle in Toronto
ምስል picture-alliance/empics/N. Denette
London britische Tageszeitungen zu Prinz Harry und Herzogin Meghan
ምስል AFP/D. Leal-Olivas

 
የብሪታንያዉያኑ ንጉሳዉያን ቤተሰብ ለእንጊሊዝ ሕዝብ ምን ትርጉም አለዉ?  
« በታሪክ ዉስጥ ስንመለከት የእንጊሊዝ ንጉሳዉያን ቤተሰብ ከ 16ኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮ፤ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ፤ በጦርነትና በብዙ ነገሮች ዉስጥ እያለፈ የደረስንበት ዓመታት ላይ ደርሰናል። በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዉ ወጣት ማኅበረሰብ የእንጊሊዛዉያኑን ንጉሳዉያን ቤተሰብ ጉዳይ አይወደዉም። ለምድን ነዉ የራሳቸዉን ስራ የማይሰሩት እና ገንዘብ የማያገኙት? ለምንድን ነዉ ሕዝብ ለሃገሪቱ የከፈለዉን ግብር የምንከፍላቸዉ ሲል ይነቅፋቸዋል። ከዝያ ደግሞ ራቅ ብለን ስንመለከት በእድሜ ከ 55 ዓመት በላይ የሆነዉ ማኅበረሰብ በጣም ይደግፋቸዋል።  
ይሁንና እንጊሊዚን እንጊሊዝ የሚያደርገዉ፤ ይህ የንጉሳዉያን ቤተሰብ ታሪክ ነዉ። በሌላ ክፍለ ዓለም እንዲህ አይነት ታሪክ ያለዉ የንጉሳዉያን ቤተሰብ ላይ የለም። ንጉሳዊ ሥርዓቱ በባህልም የተዋቀረ በመሆኑ ጥሩ የቱሪዝም መገኛ ቅርስ ነዉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ወደ ሃገር ዉስጥ የሚያስገቡት የግብር ገቢ እጅግ የላቀ ነዉ። በእድሜ ጠና ያለዉ ማኅበረሰብ እጅግ በጣም ይወዱዋቸዋል። ባለፈዉ ዓመት የተሰራ ጥናት እንደሚያመለክተዉ፤ በእንጊሊዝ ማኅበረሰብ የንጉሳዉያን ቤተሰብን ከአስር ሰባቱ ሰዎች ይወድዋቸዋል። ልዑል ሃሪ ሲያገባ መምህርትዋ ልጅ አስተያየት የሰጠችበት የቴሌቭዥ ፕሮግራም ሰሞኑን በብሪታንያ ቴሌቭዥን ዳግም እየተሰራጨ ነዉ»


በሌላ በኩል ልዑሉና ባለቤቱ ባለፈዉ ሳምንት በኢነስተግራም እና በራሳቸዉ ድረ ገፅ የነገስታቱን ስራ በከፊል እንደሚለቁ ያሳወቁ እንጂ የቤተሰብ በዓል የሚባለዉን የገና በዓል እንኳ ቤት ተቀምጠዉ ከ 95 ዓመት አዛዉንት ንግስት ኤልሳቤት ሁለተኛ ጋር ተሰባስበዉ አላሳለፉም ። ካናዳ ናቸዉ ተብሎአል። ዓመትም የተቀበሉት እያዝያ ነዉ እየተባለ ነዉ። ምናልባትም እዉነት ልዑል ሃሪ የእናቱን ሃዘን ለመርሳት ፤የእናቱ እጣ ፈንታ በሱም ቤተሰብ ላይ እንዳይደርስ ያደረገዉ ርምጃ ይሆን? 
የ35 ዓመቱ ልዑል ሃሪ እና በሁለት ዓመት የምትበልጠዉ ባለቤቱ ሜጌን፤ የፈለግነዉን ሰርተን ነፃነታችን አግኝተን ቆሎ ቆርጥመን እንኖራለን አይነት ነገር ብለዉ ቤተ- መንግስቱን ጥሰዉ በመዉጣታቸዉ፤ ጀግኖች ያልዋቸዉ ብዙዎች ናቸዉ። በአንፃሩ ይህ ጀግንነት አይደለም የቆየ ታሪክን ባህላችን ማጠልሸት እንጂ ያሉም „ጀግኖች” ካልዋቸዉ በቁጥር የሚተናነሱ አይደሉም። በዚህም አለ በዝያ በእንጊሊዛዉያኑ ቤተ-መንግሥት የለዉጥ አብዮትን ማፋፋማቸዉ ተነግሮላቸዋል። የልዑል ሃሪ እናት ልዕልት ዲያና በዚሁ ነገሥታት ቤት አብዮትን ያቀጣጠለች መሆንዋ የሚረሳ ይደለም። ጥንዶቹ ልዑላዉያን በሚቀጥለዉ ሳምንት በአምስት የደቡብ አፍሪቃ ሃገራት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተዘግቦአል።

UK Monarchie l Prinz Harry und Herzogin Meghan
ምስል picture-alliance/AP/F. Augstein

ልዑል ሃሪም እናቱ የጎበኘችዉንና አሁን ተዘግቶ ያለን ሆስፒታል ለመክፈት ወደ አንጎላ እንደምያቀናም እየተነገረ ነዉ። የወጣቶቹ ቀጣይ ርምጃ ምን ይሆን? አብረን የምናየዉ ይሆናል። ቃለ-መልልስ የሰጡንን የምህንድስና ባለሞያዋ ትዝታ ሽመልስን እና መምህርት ቤት ሃይሌን በማመስገን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። 

አዜብ ታደሰ  


ኂሩት መለሰ