1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታንያ ወታደሮች ከኢራቅ መውጣት

ዓርብ፣ ሐምሌ 24 2001

ዩናይትድ ስቴትስ በመስከረም አስራ አንዱ የአሽባሪዎች ጥቃት ክፉኛ ከተመታች በኋላ የብሪታንያ ወታደሮች ከአሜሪካ ጎን ተሰልፈው በኢራቅና አፍጋኒስታን መዝመታቸው ይታወቃል። በተለይ የጦር ሠራዊቱ በኢራቅ በቆየባቸው የስድስት ዓመታት ቆይታ በሀገረ- ብሪታንያ በርካታ ተቃዎሞዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/J156
የብሪታንያ ወታደሮች በባዝራ ኢራቅ
የብሪታንያ ወታደሮች በባዝራ ኢራቅምስል picture-alliance / dpa

የብሪታንያ ወታደሮች የኢራቅ ይፋዊ ግዳጅ ዛሬ አርብ ይጠናቀቃል። ከስድስት ዓመታት በላይ በቆየውና አጨቃጫቂ በነበረው በዚህ ግዳጅ አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ የብሪታንያ ወታደሮች ህይወታቸውን አጥተዋል። ከዛሬ ሁለት ወራት በፊትም ሠራዊቱ በደቡብ ኢራቅ በምትገኘው የባዝራ ወታደራዊ ቀጣና የነበረውን ጥበቃ ለአሜሪካ የጦር ሠራዊት አስረክቧል። በቦታው ለስድስት ዓመታት ሠፍረው የቆዩ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ የብሪታንያ ወታደሮች ተራ በተራ ኢራቅን ለቀው መውጣት መጀመራቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። በስድስት ዓመቱ የኢራቅ ጦርነት ስህተት ተፈፅሞ እንደሆን የሚያጣራ ኮሚሽን በሀገረ- ብሪታንያ መቋቋሙም ታውቋል።

የብሪታንያ ጦር ከአሜሪካን ጎን መሰለፍ

ዩናይትድ ስቴትስ በመስከረም አስራ አንዱ የአሽባሪዎች ጥቃት ክፉኛ ከተመታች በኋላ የብሪታንያ ወታደሮች ከአሜሪካ ጎን ተሰልፈው በኢራቅና አፍጋኒስታን መዝመታቸው ይታወቃል። በተለይ ጦር ሠራዊቱ በኢራቅ በቆየባቸው የስድስት ዓመታት ቆይታ በሀገረ- ብሪታንያ በርካታ ተቃዎሞዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። እንዲያም ሆኖ ጦሩ ለስድስት ዓመታት ሠፍሮ የቆየባትን የደቡብ ኢራቅ የወደብ ከተማዋ ባዝራን ዛሬ በይፋ እየለቀቀ መውጣት ጀምሯል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የብሪታንያ ወታደሮችና የጦር መኮንኖች ግን አሁንም በኢራቅ እንደሚቆዩ ታውቋል። ሻት አል አራብ የተሰኘው ዕለታዊ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አብዱል ሙናም አል ዲራዊ፥

አራት መቶ ወታደሮችና የብሪታንያ ጦር መኮንኖች በባዝራ ይቆያሉ። መኮንኖቹ አዲሶቹን የኢራቅ ወታደሮች፤ በተለይ ደግሞ የባህር ሀይሉን ያሰልጥናሉ።

በኢራቅ የብሪታንያ ወታደሮች ይቆጣጠሩት የነበረውን የጥበቃ ቃጣና ለአሜሪካኖች አስረክበዋል መባሉን ተከትሎም በርካታ የባዝራ ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ እንደወደቁ የሻት አል አራብ ዋና አዘጋጅ ገልጿል። አያይዞም የአሜሪካ ወታደሮች ከጦር ተሽከርካሪያቸው አንድ መቶ ሜትር ወዲህ ማንም እንዲጠጋችው አይፈቅዱም፤ ያን የተላለፈው ላይም ተኩስ ይከፍታሉ ሲል የስጋቱን ምንጭ አብራርቷል። በአንፃሩ የብሪታኒያ ወታደሮች በትራፊክ ቀይ መብራት ወቅት የጦር ተሽከርካሪዎቻቸውን ከኢራቃውያን መኪኖች ጋር አስጠግተው ያቆሙ እንደነበርም ጠቁሟል።

ምርመራ በብሪታንያ ጦር

በርካታ የብሪታንያ ወታደሮች ከኢራቅ እየወጡ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፤ የብሪታንያ ጦር በኢራቅ ቆይታው ስህተት ፈፅሞ ከሆነ የሚያጣራ ኮሚሽን በብሪታንያ መቋቋሙም ተዘግቧል። በብሪታንያ የቀድሞው የማህበራዊ ጉዳይ ሰራተኛ ጆን ማጣራቱ መደበኛ የፍርድ ሂደትን ያካተተ እንደማይሆን ግን ጠቁመዋል። ይልቁንስ፥

ማጣራቱ የፍርድ ሂደት አይደለም፤ ማንምም ፍርድ ቤት አይቀርብም። ሆኖም አንድ ነገር በደንብ ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ። ያም ምንድነው፤ ይሄ ኮሚቴ ነቀፌታ ለማቅረብ የማያንገራግር መሆኑን ነው። በጥሩ ሁኔታ ሊያዙ የሚችሉ መሆን የነበረባቸው ስህተቶች ተፈፅመው እንደሆነም፤ ያለምንም አድልዎ ያንኑ እንናገራለን። ሆኖም ለወደፊት ተመክሮ እንዲሆነንና የሆነውን ነገር ከመሰረቱ ለማግኘት፤ በተቻለ መጠን የጥያቄው ሂደት በህዝብ ፊት መሆን እንዳለበት እረዳለለሁ። አንዳንድ መረጃዎች በምስጢር መሆን እንደሚያስፈልጋቸውም እንገነዘባለን።

አጣሪ ኮሚሽኑ በመንግስት የተያዙ መረጃዎችን እንደሚፈልግና፤ በስድስት ዓመቱ የኢራቅ ቆይታ የተገደሉት አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ ወታደሮች ቤተሰቦችንም አቅርቦ እንደሚጠይቅ አስታውቋል። አንዳንድ ጉዳዩን በጥብቅ የሚከታተሉ አካላት ሚንስትሮቹ ኢራቅ አውዳሚ የጦር መሳሪያ አላት ወደ ሚለው የተሳሳተ ሀሳብ እንዴት ሊደርሱ ቻሉ? ምን አይነትስ ህጋዊ ምክሮችን ተቀብለው ነበር? ለሚሉት ጥያቄዎች አጣሪ ኮሜቴው መልስ እንዲያገኝላቸው ይፈልጋሉ።

ቶኒ ብሌርም ይመረመራሉ

የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ለማጣራት ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ተባባሪነታቸውን ገልፀዋል። ሆኖም የያኔውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ወረራ በመደገፋቸው ከፍተኛ ሕዝባዊ ጥላቻ ተቀስቅሶባቸው እንደነበር አዣንስ ፍራንስ ፕስሬስ ዘግቧል። በእንግሊዘኛው Stop the war Coalition የተሰኘውና በለፉት ዓመታት በለንደን ከተማ ታላላቅ የፀረ ጦርነት ዘመቻዎችን ሲያስተባብር የነበረው ጥምረት፤ ማጣራቱ የሚከናወነው ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከተዘጋ በር ጀርባ ነው ሲል ገልጿል።

አያይዞም የብሪታንያ ሕዝብ፤ የጦር ሠራዊቱ ወደ ጦርነቱ ለመግባት እንዴትና መቼ ውሳኔ እንደተሰጠው ማወቅ ይፈልጋል። ይሁንና ግን ወሳኝ የሆኑ የምስክርነት ሂደቶች ያለ ቃለ መሃላ በምስጢር ይከናወናሉ ሲል ስጋቱን ገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለስድስት ዓመታት በኢራቅ ሠፍረው የቆዩት የብሪታንያ ወታደሮች በጥር ወር ገደማ ወደ አየር ማረፊያው ተጠግተው እንደነበርና አሁን ወደ ኩዌት ድንበር አቅጣጫ መንቀሳቀሳቸው ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ