1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታንያ የአውሮጳ ኅብረት መልቀቂያና አስተያየቱ

ሐሙስ፣ መጋቢት 21 2009

ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት አባልነት የምትወጣበትን ደብዳቤ ለኅብረቱ ካቀረበች በኋላ ከኅብረቱ አባል ሃገራት ፖለቲከኞች እና ነዋሪዎች የመልካም እድል አስተያየቶች  ተሰምተዋል። ብሪታንያ የሊሳቦኑን ዉል አንቀፅ 50 መሠረት በማድረግ ባቀረበችዉ ከኅብረቱ መልቀቅያ ደብዳቤ ላይ ፊርማቸዉን ያኖሩት የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/2aMqi
Großbritannien Brexit Symbolbild
ምስል picture-alliance/empics/Y. Mok

EU-austritt Groß-Britannien REAX - MP3-Stereo

 

 የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ በቀጣይ ሃገራቸዉ ከአዉሮጳ ኅብረት ጋር ልትሰራባቸዉ ባቀደቻቸዉ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዉይይት ለማካሄድ ዝግጅት ላይ መሆንዋን ተናግረዋል።  የኅብረቱ ፖለቲከኞች በበኩላቸዉ ይህ በቀጣይ በፍችዉ የድርድር ጠረቤዛ ላይ የሚታይ ይሆናል ሲሉ ነዉ አስተያየታቸዉን የሰጡት።

« መልካም ጉዞ፤ ትክክለኛ ዉሳኔ እንዲሆን እመኛለሁ። የኤኮኖሚ እድገትዋ ሳያቆለቁል እስካሁን ካለችበት ተሻሽላ ማየትን እሻለሁ።»

UK Kundgebung 'Unite for Europe'
ምስል picture-alliance/ZUMAPRESS.com/J. Goodman

ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት የመልቀቅያ ማመልከቻ በይፋ ማስገባትዋን ተከትሎ አንድ ጀርመናዊ የሰጡት አስተያየት ነዉ። ላለፉት 40 ዓመታት የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሆና የዘለቀችዉ ብሪታንያ ከኅብረቱ የምትፋታበትን ደብዳቤ ትናንት በይፋ ስታቀርብ ቀኑ ታሪካዊ ሆኖ በታሪክ ማኅደር ሊመዘገብ በቅቶአል። በቀጣይ  27 ቱ የኅብረቱ አባል ሃገራት ከብሪታንያ ጋር የሚለያዩበትን መንገድ ለመቀየስ የሁለት ዓመት ጊዜ ተሰጥቶአቸዋል። የብሪታንያዉ ከፍተኛ ልዑክ ቲም ቦሮ ትናንት በኅብረቱ ዋና መቀመጫ ብረስልስ ላይ በይፍ ደብዳቤዉን ካስረከቡ በኋላ ዋና ጥያቄ  ሆኖ የታየዉ ብሪታንያ ለዚህ ፍች ለብረስልስ መክፈል የሚኖርባት ገንዘብ ስንት ይሆን የሚለዉ ነዉ። ብሪታንያ በየሳምንቱ ለኅብረቱ መቀመጫ ለብረስልስ 350 ሚሊዮን የብሪታንያ ፓዉንድ ትከፍላለች። ይህ ይከፈላል የተባለ ገንዘብ  ብሪታንያ ከኅብረቱ ለመገንጠል በሃገሪቱ በነበረዉ ዘመቻ ሲሰማ የነበረ የመቀስቀሻ ነጥብ ነበር። የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ብሪታንያ በይፋ የኅብረቱን  መልቀቅያ ስታቀርብ ብሪታንያ ከኅብረቱ ጋር በአጋርነት እንድትቆይ ምኞታቸዉን ተናግረዋል።

«ብሪታንያና  የአዉሮጳ ኅብረት ቅርብ አጋር ሆነዉ ግንኙነታቸዉን እንዲቀጥሉ እመኛለሁ። ከብሪታንያ ጋር ያለን የጋራ እሴቶቻችን የመጨረሻ ሳይሆን፤ ብሪታንያ ለኔ የአዉሮጳ አካል ነበረች አሁንም አካል ሆና ትቀጥላለች።»    

ትናንት ለኅብረቱ ከቀረበዉ የኅብረቱ መልቀቅያ «ብሪግዚት» ማመልከቻ በኋላ ግን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም።  በብረስልስ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 7 ሰዓት 20 የብሪታንያዉ ከፍተኛ ልዑክ ቲም ቦሮ ለአዉሮጳ ኅብረት መሪዎች  ምክርቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ቱስክ የብሪታንያ ሕዝብ የአዉሮጳ ኅብረትን ለመልቀቅ ወስኑዋል ሲሉ ቴሬዛ ሜይ ያስተላለፉትን የኅብረቱን መልቀቅያ ማመልከቻ የሰጡበት ሰዓት።

ቱስክ ከብሪታንያ የተቀበሉትን ይህን ደብዳቤ በሚያነቡበት ወቅት የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ በለንደን ፓራላማ ንግግር እያደረጉ ነበር።

UK Kundgebung 'Unite for Europe'
ምስል picture-alliance/ZUMAPRESS.com/J. Goodman

« ዛሬ የራሳችንን ዉሳኔና ዳግም በማሳለፍ የራሳችንን ሕግ እናፀድቃለን።  እኛ ዋንኛ በምንላቸዉ ነገሮች ላይ ቁጥጥሩን ዳግም ራሳችን እናደርጋለን። አንዲት ጠንካራና ፍትሃዊ ብሪታንያን በመመስረት ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን በኩራት ሃገራችን ሲሉ የሚጠርዋትን ሃገር እንገነባለን።»   

የፍችዉ ሂደት ጥሩ አጋርነትና ጓደኝነትን የተላበሰ ምንም አይነት አተካራ ያልታየበት ነዉ። ለአዉሮጳ ኅብረት መሪዎች ምክር ቤት ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ቱስክ ከብሪታንያ የደረሳቸዉ ደብዳቤም ተመሳሳይ ነዉ። « እናጣችኋላን፤  እናፍቁናላችሁ ። «እናመሰግናለን ደህና ሁኑ» 

እንድያም ሆኖ የፍችዉ ሂደት እንዲህ በቶሎ የሚጠናቀቅ አይሆንም። እስከ ጎርጎረሳዊዉ 2019 ዓ,ም መጀመርያ ድረስ በሚዘልቀዉ በዚህ ፍቺ ጊዜ 21 ሽህ የአዉሮጳ ኅብረት ደንቦችና ሕግጋት በብሪታንያና በአዉሮጳ ኅብረት የፍች ድርድር ጠረቤዛ ላይ ይቀርባሉ። ኅብረቱ ምናልባትም 60 ቢሊዮን ይሮ ሊያስከፍላት ይችላል። 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ