1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪክ መንግሥታት ኤኮኖሚ

ረቡዕ፣ መጋቢት 26 2004

በአሕጽሮት ብሪክ በመባል የሚታወቁት በተፋጠነ ዕድገት ሲራመዱ የቆዩ አራት መንግሥታት የብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድና ቻይና የኤኮኖሚ ዕድገት ደከም እያለ በቦታቸው ሌሎች ሊተኩ እየተቃረቡ ነው።

https://p.dw.com/p/14XCP
ምስል picture alliance/dpa

በአሕጽሮት ብሪክ በመባል የሚታወቁት በተፋጠነ ዕድገት ሲራመዱ የቆዩ አራት መንግሥታት የብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድና ቻይና የኤኮኖሚ ዕድገት ደከም እያለ በቦታቸው ሌሎች ሊተኩ እየተቃረቡ ነው። በዓለምአቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕድገት በመታየት የመቀጠሉ ሁኔታ ለነዚሁ እያበቃ መሆኑን በወቅቱ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች መተንበይ ይዘዋል።

ብሪክ መንግሥታት ከአሠርተ-ዓመት በላይ የዓለም ኤኮኖሚ መንኮራኩር ሆነው ሲቆዩ ወደፊት በዚሁ ሚና መቀጠላቸው እንግዲህ የማይጠበቅ ነገር እየሆነ ነው። ለዚህም ምክንያቱ በነዚህ ሃገራት እያቆለቆለ መሄድ የያዘው የኤኮኖሚ ዕድገት ነው። ይህ ደግሞ በዓለም ኤኮኖሚም ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ከአሥር ዓመታት ገደማ በፊት ብሪክ የሚለው አሕጽሮተ-ቃል ለተራማጁ አራት ሃገራት መለያ ሆኖ የመነጨው ከአሜሪካ ነበር። ብራዚልና ሩሢያ በጥሬ ሃብታቸው የተነሣ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን ሲስቡ ሕንድና ቻይና ደግሞ በሚሊያርዶች በሚቆጠር ሕዝባቸው ብዛት የርካሽ የሥራ ጉልበትና የዝቅተኛ የምርት ዋጋ ተሥፋን ያጠናክራሉ።

እነዚህ በተፋጠነ ዕድገት መራመድ የያዙት ሃገራት ታዲያ የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ድርሻቸውን በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት መንግሥታት በበለጠ መጠን ከፍ ለማድረግ ከአምሥት ዓመት ጊዜ በላይ አልወሰደባቸውም። ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት እነዚህ የዕድገት መንኮራኩሮች ለዘብ እያሉ ሲሄዱ ነው የሚታየው።

ለምሳሌ ያህል ቻይና ከረጅም ጊዜያት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድ ኪሣራ ሲደርስባት ለሎቹም የብሪክ ሃገራት ችግር ገጥሟቸው ነው የሚገኙት። የኤኮኖሚ ውጤታቸው እያነሰ መሄዱ አልቀረም። ሆኖም በነዚሁ ሃገራት ላይ የሚያተኩሩት የዶቼ ባንክ ባለሙያ ማሪያ ላውራ ላንሴኒ ሁኔታውን ለዘብ አድርገው ይመለከቱታል።

«አሁን እየቀረቡ ያሉት አሃዞች ያለፈው 2011 ዓመተ-ምሕረት ናቸው። በሌላ በኩል በያዝነው 2012 ሁለተኛ አጋማሽ ዕድገቱ እንደሚፋጠን ነው የምንጠብቀው። እያንዳንዱን ዓመት እርስበርሱ ማነጻጸሩ ትክክል አይደለም። ይልቁንም ከቀውሱ በፊትና በኋላ ያለውን ጊዜ መመልከት ነው የሚገባው። እንዲህ ከሆነ ተራማጆቹ ሃገራት በተለይም ቻይናና ሕንድ ወደፊትም ጠንካራ ዕድገት በማሣየት ይቀጥላሉ»

ቻይናና ሕንድ ውስጥ የዘንድሮው 2012 የዕድገት ተመን ወደ ሰባት ተኩልና ሰባት ከመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። እንደቀድሞው የዘጠኝና የአሥር ከመቶ ዕድገት ጨርሶ የሚታለም አይደለም። እርግጥ ይህ ሰባት በመቶ አሃዝም ቢሆን በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት ሃገራት አንጻር አሁንም ትልቅ ዕድገት ነው። ሆኖም ግን በሌላ በኩል ባለፉት ዓመታት ከተለመደው ከአሥር በመቶ በላይ ዕድገት ሲነጻጸር ትልቅ የኋልዮሽ ሂደት መሆኑ አይቀርም። ለዚሁ የዕድገት ጉዞ ጋብ ማለት ምክንያቶቹ ሁለቱ ሃገራት ከውጭ በገፍ ማስገባት ያለባቸው ጥሬ ዕቃ ዋጋ መናር ነው።

Brasilien Wirtschaft Bank in Rio de Janeiro
ምስል AP

ብራዚል ደግሞ እጅግ እየጨመር በሚሄድ የደሞዝ ወጪ፣ በዋጋ ግሽበትና ከውጭ ያለማቋረጥ በሚፈሰው ካፒታል ሳቢያ የምንዛሪዋ ዋጋ በመጨመሩ ፈተና ላይ መውደቋ አልቀረም። ምዕራባውያን ባለሃብቶች በዚያ መዋዕለ-ነዋይ ማድረጉን የሚመርጡት በአገራቸው ቀውስን በመታገል የተነሣ በትንሽ ገንዘብና በአነስተኛ ወለድ አትራፊ መሆኑ ሰለሚከብዳቸው ነው።

በሩሢያ በነዳጅ ዘይት ሃብት ላይ ያለው አንድ-ወጥ ጥገኝነት ዕድገትን የሚያዳክም ሆኗል። አገሪቱ እንግዲህ ኤኮኖሚዋን በፍጥነት በዘመናዊ መንገድ ማዋቀርና ማስፋፋት ይኖርባታል ማለት ነው። ግን ሙስናና መንግሥት በንግድ ውስጥ ዕጁን ማስገባቱ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን የሚያስፈራራ እንጂ የሚያበረታታ ሆኖ አይገኝም። ሃብት ያለው ገንዘቡን ወደ ውጭ ማሸሹን ይመርጣል። ዓመኔታ ሊሰጠው በሚችል ግምት መሠረት ባለፈው 2011 ከሩሢያ ወደ ውጭ እንዲሸሽ የተደረገው ገንዝብ 85 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚጠጋ ነው።

ከዚሁ ሌላ በተፋጠነ ዕድገት ሲራመዱ የቆዩት የብሪክ ሃገራት በምዕራቡ ዓለም ቀውስ ጨርሶ አልተነኩም ለማለት አይቻልም። በኢንዱስትሪ ልማት ወደ በለጸጉት ሃገራት የሚደረገው የውጭ ንግድ እየደከመ ሲሆን የአገር ውስጡ ፍጆት ደግሞ ይህን እጦት ለመሸፈን የሚበቃ አይደለም። ሆኖም በተፋጠነ ዕድገት ሲራመዱ የቆዩት ሃገራት ወደፊትም ለዓለም ኤኮኖሚ ዕርምጃ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው የማሪያ ላውራ ላንሤኒ ዕምነት ነው።

«ይህ ባለፉት ዓመታት በከፊል የታዘብነው ነገር ነው። ከሞላ-ጎደል መላው የኢንዱስትሪ ዓለም ወደ ዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ቀውስ በተንሸራተተበትና ተራማጁ ሃገራት ደግሞ በአማካይ ጥሩ ዕድገት ይዘው በቀጠሉበት ወቅትም እንዲሁ! ይህን ባለፈው ዓመትም አይተናል። እና ይሄው በበለጸጉትና በተራማጁ ሃገራት መካከል ያለው የዕድገት ልዩነት ባለበት ይቀጥላል ብለን ነው የምናምነው። አንዱ ሌላ ጥያቄ እነዚህ ሃገራት የዕድገት መንኮራኩር ለመሆን ይችላሉ ወይ ነው። በኔ አስተሳሰብ ከሕንድና ከቻይና የተቀሩት ለዚህ አይበቁም። ገና በሚገባ ግዙፍ አይደሉም»

በብሪክ ሃገራት እንግዲህ የኤኮኖሚው ዕድገት ደከም እያለ ሲሆን ነገር ግን ሌሎች በፍጥነት የሚያድጉ ሃገራት ደግሞ ብቅ ብቅ በማለት ላይ ናቸው። በኤኮኖሚ ጠበብት ስሌት እነዚህ ሃገራት ገና ከዛሬው ለዓለምአቀፉ ዕድገት ሩቡን ድርሻ ያበረክታሉ። በ 2050 ገደማ እንዲያውም ድርሻው አርባ በመቶ እንደሚጠጋ ነው የሚገመተው።

« ከስድሥት እስከ ስምንት የሚሆኑ ትልልቅና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ ሃገራትን እናያለን። ኢንዶኔዚያን፣ ፖላንድን፣ ሜክሢኮንና ኮሪያን የመሳሰሉ!እርግጥ የነዚህ ሃገራት የዕድገት መጠን አንዱ ከሌላው ይለያያል። ነገር ግን ሁሉም ሊስፋፉ የሚችሉ፤ በከፊልም ርቀው የተራመዱ ማራኪ ገበዮች ናቸው። የተለያዩ ቢሆኑም ለመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችና ኩባንያዎች በጣም ማራኪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አምናለሁ»

ከረጅም ጊዜ አንጻር ጥሩ ዕድል ከሚሰጣቸው ሃገራት መካከል የአሜሪካው መዋዕለ-ነዋይ ባንክ ጎልድማን ሳክስ እንደሚለው ቪየትናምን፣ ፊሊፒንን፣ ፓኪስታንንና ባንግላዴሽን የመሳሰሉት የእሢያ ሃገራትም ይገኙበታል። እርግጥ በአንዳንዶቹ በነዚህ ሃገራት የፖለቲካ አለመረጋጋት የዕድገት መሰናክል ሊሆን መቻሉ የሚጠበቅ ነው። ይህ ለምሳሌ ብዙ ሕዝብ ያላቸውን ግብጽን፣ ኢራንንና ናይጄሪያንም ጭምር ይጠቀልላል።

ለማንኛውም በርከት ባሉ ሃገራት ጠቃሚ የዕድገት ዕርምጃ ሲታይ አንዳንድ ደግሞ መዳከማቸው አልቀረም። ለምሳሌ ደቡብ አፍሪቃ ከተወሰነ የዕድገት ሂደት በኋላ በማቆልቆል ላይ ነው የምትገኘው። በቱርክም የኤኮኖሚው ዕድገት በጣሙን ዝግተኛ ሆኗል። ቱርክ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ስምንት በመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገበች በኋላ ባለፈው ዓመት ከሶሥት በመቶ ለመድረስ እንኳ አልተቻላትም ነበር።

Bauarbeiter in Jonhannesburg
ምስል AP

ደቡብ አፍሪቃን ካነሣን ብሪክ መንግሥታት አፍሪቃይቱን አገር በማከል እንድ ብሪክስ መንግሥታት ሰሞኑን ኒው ዴልሂ ላይ የመሪዎች ጉባዔ በማካሄድ የበኩላቸውን የንግድ ትስስር ለማጠናከርና አዲስ የልማት ባንክ ለማቋቋምም ተስማምተዋል። የባንኩ ዓላማ ወደፊት ዕውን ቢሆን በዓለም ባንክና በእሢያ የልማት ባንክ አርአያ በአዳጊው ዓለም የልማት ፕሮዤዎችንና መዋቅራዊ ዕምጃዎችን ማንቀሳቀስ ነው። ግን ለጊዜው ገና ሃሳብ ነው።

በሌላ በኩል የብሪክስ መንግሥታት የኤኮኖሚ ዕድገት በፍጥነቱም ሆነ በመጠኑ እየቀነሰ የሚሄድ መሆኑን ምዕራባውያን ጠበብት ቢናገሩም እነርሱ በበኩካቸው በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ያላቸውን ድርሻ ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ማለማቸውን አላቆሙም። የብራዚሏ ፕሬዚደንት በዴልሂው ጉባዔ ወቅት የብሪክስ ሃገራት ክብደት በዓለምአቀፍ ደረጃ እየጨመረ እንደሚሄድ ነበር ያመለከቱት።

«ብሪክስ ሃገራት እጅግ ጠቃሚ የዓለም ኤኮኖሚ አንቀሳቃሽ አካል ናቸው። እናም በዓለም ንግድ ላይ አብዛኛውን ድርሻ ያበረክታሉ። በ 2002 በመሃከላችን የነበረው ንግድ ስፋት በ 27 ሚሊያርድ ዶላር ብቻ የተወሰነ ነበር። ባለፈው 2011 ይሄው በግምት 250 ሚሊያርድ ተጠግቷል»

እርግጥ ባለፈው ዓመት ቡድኑን የተቀላቀለችውን ደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ ብሪክስ ግማሹን የዓለም ሕዝብ የሚጠቀልል ቢሆንም እነዚህ ሃገራት በዓለምአቀፉ አጠቃላይ ምርት ላይ ያላቸው ድርሻ ግን በ 22 ከመቶ የተወሰነ ነው። ቢሆንም የነዚህ ሃገራት የፖለቲካ ተሰሚነት ባለፉት ዓመታት እየጨመረ መምጣቱ አልቀረም።

አምሥቱ መንግሥታት የብሪክስን ውስጣዊ ንግድ በብሄራዊ ምንዛሪዎች ለማካሄድ ውሎችን ሲፈራረሙ ይህም የስብስቡን ንግድ ለማቀላጠፍ እጅግ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው። ስምምነቱ በቡድኑ ውስጥ የብድርና የገንዘብ ሽግግር ተግባራትን የሚያቃልል ከመሆኑም በላይ ንግዱን ከአሜሪካ ዶላር ውጣ-ውረድ ተጽዕኖም የሚያላቅቅ ነው የሚሆነው።

ከዚሁ ሌላ ውስጣዊውን ንግድ በማጠናከርና ለነጋዴዎች የቪዛ አሰጣጥን በማቃለል ትብብሩን ለማስፋፋት ታስቧል። ይህ ሁሉ ወደፊት ብሪክስን ምናልባት ወደ ትልቅ ድርጅትነት ለመለወጥ የሚረዳ ሲሆን ውስጣዊውን ንግድም እስከ 2015 ወደ 500 ሚሊያርድ ዶላር እንደሚያሰፋ ነው የሚጠበቀው። ስብስቡ እያደር ደቡብ ኮሪያንና ኢንዶኔዚያን በመሳሰሉት በመራመድ ላይ ባሉ ሃገራት እየሰፋ መሄዱም የሚቀር አይመስልም። ይህም በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ተጽዕኖውን እንደያዘ እንዲቀጥል የሚረዳው ሊሆን ይችላል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዮ ለገሠ