1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ በብዝሃ ህይወት ስብጥር በተፈጥሮ የታደለች ሀገር መሆኗ፤

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 22 2009

ኢትዮጵያ በብዝሃ ህይወት ስብጥር በተፈጥሮ የታደለች ሀገር መሆኗን ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በሀገሪቱና በዉጭ ሳይንቲስቶች ትብብርም በእጽዋቱ ዘርፍ ሰፋ ያለ ጥናት ተካሂዷል፤ አሁንም እየተካሄደ ነዉ። የተገኙ የጥናት ዉጤቶችን መሠረት ያደረገ የጥበቃ ሥራ መሠራት እንደሚኖርበትም ተመራማሪዎቹ ያሳስባሉ።

https://p.dw.com/p/2Rzhe
Äthiopien Wald
ምስል Imago/blickwinkel

የብዝሃ- ሕይወት ስብጥር ጥናት

 

ላለፉት 38 ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ጥናት እና ምርምር ላይ ጊዜያቸዉን አሳልፈዋል። አሁንም በዚሁ መስክ ምርምራቸዉን ቀጥለዋል። አብዛኛዉን የዕድሜ ዘመናቸዉን በእጽዋት ምርምር ያሳለፉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ፤ የጎርጎሪዮሳዊ 2016 ዓ,ምን የብሪታኒያዉ የሮያል ቦታኒክ ጋርደን ዓለም አቀፉን የኪዉ ሽልማት ለማግኘት በቅተዋል። ኩዉ ገልድ የተሰኘዉ ማኅበር በጎርጎሪዮሳዊዉ 1893ዓ,ም የተመሠረተ ሲሆን፤ ዋና ዓላማዉ የምድራችንን እጽዋት ዝርያ ማጥናት፣ መከታተል እና መጠበቅ ላይ ያነጣጠረ ነዉ። ለዚህም በዘርፉ የሚደረገዉን ጥናት ይደግፋል ያበረታታል።

ፕሮፌሰር ሰብስቤ ከተጠቀሰዉ ተቋም ጋር ከ30 ዓመታት በላይ የምርምር ሥራ አብረዉ መሥራታቸዉን ይናገራሉ። እሳቸዉን በሀገራቸዉ ብዝሃ ሕይወት ዘርፍ ያካሄዱት ጥናትና ያበረከቱት አስተዋፅኦ፤ ለሀገሪቱ ሕዝብ እንዲሁም ለመላዉ አፍሪቃ በጥቅም ያከናወኑት ተግባር  ለዚህ ሽልማት እንዳበቃቸዉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽ የተገኘዉ መረጃ ያመለክታል።

Äthiopien Wald
ምስል Dr. Adefris Worku

እሳቸዉ እንደሚሉት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1950ዎቹ እና ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያን ብዝሃህይወት የሚመለከቱ ጥናቶች አልነበሩም። የኢትዮጵያን የብዝሃህይወት መረጃ ለማሰባሰብ ፕሮፌሰር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የጀመሩትን ፕሮፌሰር ሰብስቤ ከባልደረቦቻቸዉ ጋር ተረክበዉ ቀጥለዉበት ሥራዉን ማጠናቀቃቸዉንም ያስረዳሉ።  30 ዓመት በፈጀ  በዚህ ፕሮጀክትም ከኢትዮጵያዉያኑ በተጨማሪ ከ17 ሃገራት የተዉጣጡ ከ119 ሳይንቲስቶች በላይ መሳተፋቸዉንም ይገልጻሉ።  

የእጽዋቱን ምንነት ለማወቅ ስነምህዳሩን ማጥናት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ተመራማሪ ካለፉት አምስት እና አራት ዓመታት በፊት ጀምሮም የኢትዮጵያን የስነምህዳር እጽዋት ሽፋን የሚያመለክት ዳጎስ ያለ የጥናት መጽሐፍ መዘጋጀቱንም አብራርተዋል። እንዲህ ያሉ ጥናቶች በመካሄዳቸዉም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚገኙ 6,000 እጽዋት እጽዋቱ የት እንደሚገኙ ምን እንደሚመስሉ እና የመሳሰሉት አስፈላጊ ዝርዝር መረጃዎች፤ አሉ። ከእነዚህ ዉስጥም 600ዎቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እፅዋት መሆናቸዉን ፕሮፌሰር ሰብስቤ ገልጸዉልናል። 

ኢትዮጵያ የብዝሃ ሕይወት ቋት ናት የሚሉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ የብዝሃ ህይወቱ መገኛ የሆነዉ የሀገሪቱ ደን እየተመናመ በመሄዱ ያላትን ሀብት በአግባቡ እንዳልተጠቀመችም ይናገራሉ። ዋና ሥራቸዉና ትኩረታቸዉ ምርምሩና ግኝቱ ላይ መሆኑን የሚናገሩት የእጽዋት ምርምር ባለሙያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ እንደሚገኙ የታወቀዉ ብርቅዬ የሆኑት እጽዋት ዝርያ እንዳይጠፋ ጥንቃቄ የማድረጉ ሥራ በቅንጅትና በጋራ መከናወን እንዳለበት ሳያሳስቡ አላለፉም።

Äthiopien Wald
ምስል Dr. Adefris Worku

ከጥናትና ምርምሩ ዉጤት ኅብረተሰቡ መረጃዎች እንዲያገኝም በተለያዩ እጽዋት ላይ የተካሄዱ ጥናት እና ምርምሮች ታትመዉ በየዩኒቨርሲቲዎቹ እንዲሰራጩ፤ እንዲሁም ጥናቶቹን ለማየት ለሚፈልጉ እንዲዳረሱም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ከባለሙያዉ ለመረዳት ተችሏል።

የእጽዋት ሳይንስ ተመራማሪዉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ እንደገለጹልን አንዴ የኢትዮጵያ የእጽዋት ዝርያ በሙሉ ከተጻፈ በኋላ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በክልላቸዉ ያለዉን የእጽዋት ዝርያ መጻፍ ይችላሉ። እንዲህ ማድረግ ሲቻል ደግሞ መረጃዉ ለኅብረተሰቡ የተሻለ ቅርበት ይኖረዋል ብለዉም ያምናሉ። የብዝሃ ሕይወት ቋት ያሏት ሀገር ኢትዮጵያም በዩኒቨርሲቲዉ ከሚከናወነዉ ምርምር በተጓዳኝ ሀብቷን የምትጠብቅበትን ስልት ማጠናከር እንደሚገባም ሳይመክሩ አላለፉም።

 ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ