1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦስተን የቦምብ ጥቃት እና የሞት ፍርድ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2007

በአሜሪካን የማሳቹሴትስ ግዛት የሞት ፍርድ ለመጨረሻ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1947 ዓ.ም. ነበር። በግዛቲቱ ፊሊፕ ቤሊኖ እና ኤድዋርድ ጌርትሰን ላይ ብያኔው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የሞት ፍርድ እንዲቀር ተድርጎ ቆይቷል።

https://p.dw.com/p/1EFnC
Boston Marathon Explosion Anschlag 2013
ምስል Reuters

የሞት ፍርድ ደጋፊዎች በተለያዩ ጊዜያት እግዱን ለማስነሳት ያደረጓቸውን ጥረቶች ግዛቲቱ ሳትቀበል ቆይታለች። ሶስት ሰዎች የተገደሉበትንና 260 የቆሰሉበትን የቦስተን ማራቶን የቦንብ ጥቃት ከወንድሙ ጋር ፈጽሟል የተባለው ጆሃር ሳርናዬቭ የክስ ሂደት ታኅሣሥ 27 ቀን፤ 2007 ዓ.ም.ሲጀመር የሞት ፍርድ ደጋፊዎችና ነቃፊዎች እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተዋል።


ጥቃቱ ከተፈጸመ ከወራት በኋላ Boston Globe የተሰኘው የከተማዋ ጋዜጣ በሰራው ጥናት 57% የከተማዋ ነዋሪዎች በጆሃር ሳርናዬቭ ላይ ከሞት ይልቅ ይቅርታ የሌለው የእድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድበት ይፈልጋሉ።33% ደግሞ ፍርዱ ሞት እንዲሆን እንደሚፈልጉ ጋዜጣው የሞት ፍርድን በመቃወም በርእሰ አንቀጹ አስነብቧል።
በቦስተን ሰፎልክ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል አቭሪ መንግስት ከህዝብ አስተያየት የተለየ አቋም በመያዙ ተናደዋል።


«ይህ ንቀት ነው። ጥቃቱ አስከፊ ወንጀል ነው። ከዚህ የባሰ አስከፊ ነገር ማሰብ ይከብዳል። የሞት ፍርድ ሃሳብ የመጣው ፖለቲከኞችና አቃቤ ሕጎች የእኛ ጠባቂ መሆናቸውን ለማሳየት ነው። ይህ ግን መሰል ጥቃቶችን ከመከላከል ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ጥቃት መፈጸም የሚፈልጉ ሽብርተኞች የሞት ፍርድን ፈርተው ያፈገፍጋሉ ብሎ የሚያምን አለ? በፍጹም!»


የቀድሞዋ ዳኛ እና አሁን በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ናንሲ ጌርትነር የፍትህ ሚኒስቴር እንዲህ አይነት ውሳኔዎችን ሲወስን የህዝብ አስተያየትን ከግምት ውስጥ የማስገባት ግዴታ እንዳለበት ይናገራሉ። ቢሆንም የቦስተን ግሎብ የህዝብ አስተያየት ከክሱ አካሄድ የተለየ መሆኑን ይናገራሉ።


«ይህ ብሄራዊ ክስ ነው።በቦስተን ግሎብ ላይ የታየው የህዝብ አስተያየት ቁጥር የሚሰራው ለቦስተን ብቻ ነው። የህዝብ አስተያየት የተሰበሰበው በሃገሪቱ ሌላ ክፍል ቢሆን ኖሮ ቁጥሩም የተለየ በሆነ ነበር»
በቴክሳስ ግዛት በሳን አንቶኒዮ ከተማ በሚገኘው የሴንት ሜሪ ዩኒቨርሲቲ የሽብርተኝነት ሕግ ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ጄፍሪ አዲኮት ጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ከፍተኛ ወንጀል በመሆኑ ቅጣቱም ከባድ ሊሆን ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ። ጄፍሪ አዲኮት የሞት ፍርድ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ለመከላከል እንደሚያስችልም ያምናሉ።

Dschochar Zarnajew Anschläge Boston Marathon Watertown
ምስል picture-alliance/AP


«ጽንፈኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚያቆማቸው ከባድ ቅጣት ነው።እንዲህ አይነት ሰዎች ለሚለማመጣቸው ወይም ለሚደራደራቸው ክብር የላቸውም። ይህ ሰብዓዊ ባሕሪ ነው። ነገር ግን አንተ ያለህን ጉልበት፤እንቅስቃሴ፤እና ሃሳብ የሚስተካከል ሌላ ኃይል ሲመጣ ለመቆም ትገደዳለህ።»


የቦስተን መገናኛ ብዙሃን የሞት ፍርድ ደጋፊ እና ነቃፊዎችን ክርክር ሲያስተናግዱ ቆይተዋል። ናንሲ ጌርትነር የጆሃር ሳርናዬቭ የክስ ሂደት ከሦስት እስከ አራት ወራት እንደሚወስድ ተናግረዋል። በሕግ ፕሮፌሰሯ አስተያየት በክስ ሂደቱ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት ደግሞ በይግባኝ ለአመታት ይዘልቃል። በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ አይደለሁም ያለው ጆሃር ሳርናዬቭ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ቀርበውበታል።


የአሜሪካን ፍትህ ሚኒስቴር የጆሃር ሳርናዬቭን ጉዳይ የሚመለከቱ ገለልተኛ ዳኞችን ለመምረጥ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይሁንና የመገናኛ ብዙሃን ለጉዳዩ የሰጡት ሰፊ ዘገባ የዳኞቹን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል። ለዚህም የጆሃር ሳርናዬቭ ጠበቆች የክስ ሂደቱ በሌላ ከተማ እንዲካሄድ ለማድረግ ጥረት አድርገው ነበር።ጥያቄውን ዳኛ ጆርጅ ኦቶል ሳይቀበሉት ቀርተዋል።


አሁን ቦስተን ለአመታት ታግዶ የቆየውን የሞት ፍርድ መልሶ ወደ አደባባይ ባመጣው የጆሀር የክስ ሂደት ገለልተኝነት ጉዳይ ሌላ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብታለች።


ሪቻርድ ዎከር/እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ