1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦአዚዚ መስዋእትነትና የቱኒሲያ ወቅታዊ ይዞታ፤

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 10 2006

እ ጎ አ ታኅሣሥ 17 ቀን 2010 ዓ ም፤ ቅጠላ ቅጠልና ፍራፍሬ በመሸጥ ይተዳደር የነበረው ሙሐመድ ቡዓዚዚ የተባለው ጎልማሳ ቤንዚን አርክፈክፎ ራሱን ሲያቃጥል፤ ቤን አሊንና ዘመዶቻቸውን ከሥልጣን ለማፈናቀል አልሞ አልነበረም። ይሁንና የቡዓዚዚ በገዛ

https://p.dw.com/p/1AcZy
ምስል Creative Commons/Wikipedia

እጁ ሕይወትን የማጥፋት እርምጃ፤ የአብዮቱ መባቻ መሆኑ ነው የዓረቡ ዓለም ተቀጣጣይ የህዝብ መነሣሣት ታሪክ የሚጠቅሰው። ያ ድርጊት ከተፈጸመ ከ 3 ዓመታት በኋላ ቱኒሲያ የዐረቦች አብዮት ጠንሳሽም ሆነ ጀመማሪ መሆኗን ነው በኩራት የምትገልጸው። ይሁንና የቡአዚዚ ራእይ አደጋ እንደተደቀነበት ነው። አገሪቱ አዲስ ጠ/ሚንስትር ለመምረጥ እንኳ መስማማት አልቻለችም።

Sidi Bouzid 3 Jahre nach der Revolution
ምስል DW/K. Ben Belgacem

ሰባት ጎልማሶች፤ ቅዛቃዜ እንዲሁም የተሽከርካሪ ጭስና ጩኸት ባልተለየው ጎዳና ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚውን ይታዘባሉ። እነዚሁ ሰዎች ፣ ቱኒስ ውስጥ የተሽከርካሪዎች ትርምስ በሚታይበት ፓርላማ ህንጻ አጠገብ ነው ተቀምጠው የሚያወጉት። ጊዜያዊ ኑሮአቸውን በዚያ ካደረጉ ከ 120 ቀን በላይ ሆኖአቸዋል ። ባለፉት ሞቃት ወራት ከፓርላማው ህንጻ ፊት በተደረገው ትልቅ የመቀመጥ አድማ ተሳታፊዎች ናቸው። ከሀገሪቱ በመላ የተሰባሰቡ በሺ የሚቆጠሩ ቱኒሲያውያን የፓርላማውን ግቢ በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ነበር ። ዓላማቸው፤ ሕገ-መንግሥት አዘጋጂው ቡድን እንዲፈርስ ለማስገደድ ነበረ። ሆኖም አብዛኞቹ የተቃውሞ ሰልፈኞች ወደ ዕለታዊ ተግባራቸው ተመልሰዋል።

ሰባቱ ሰዎች ግን፤ በዚያ መቆየቱን ሆኗል የመረጡት። ሥራ ስለሌላቸው ፤ ምንም የሚቀርባቸው ነገር የለም። ከአነዚህ ከፊሉ እንዲያውም፤ በፓርላማው አጥር ላይ ራሳቸውን በመስቀል ሕይወታቸውን ለማሳለፍ ሞክረው እንደነበረ ነው የተገለጠው። በሽግግሩ ፓርላማ በዛ ያለ ውክልና ባገኘው እስላማዊው ኢናሃዳ ፓርቲ እጅግ ነው የሚናደዱት። ሹክሪ በልዓድ እና ሙሐመድ ብራሂሚ የመሳሰሉትን የግራ ዘመሙ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ያስገደለ ይኸው እስላማዊው ኢናሃዳ ፓርቲ ነው ብለውም ያምናሉ።አብዮቱ ከፈነዳ ወዲህ ኑሮአቸው እንዳልተሻሻለም ነው የሚገልጹት። ጋዚ ማኽፉዲ የተባሉት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል።

Opfer der Jasmin-Revolution...die Vergessenen in den tunesischen politischen Krisen
ምስል DW/Guizani Tarak

«የፖለቲካ ፓርቲዎችቹ፤ ኢናሃዳ ሆነ ሌሎቹ፤ ቃል የገቡልን ብዙ ነበረ። ግን ባዶ ቃላት ሆነው ነው የቀሩት። ዋናው ዓላማቸው ሥልጣን መጨበጥ ብቻ ነበረ ።ማንም ለኛ የተቻለውን የሚያደርግ የለም። አሁን እኛ በረሃብ አድማ ላይ ነን። በሕይወታችን ላይ አደጋ ነው የደቀንን። ግን ዓላማችን ግልጽ ነው። ይህን የምናደርገው ለሃገራችን ስንል ነው።»

ጋዚ ማህፉዲ፤ ከደቡባዊው ቱኒሲያ፤ ከጎስቋላዋ ንዑስ ከተማ ሲዲ ቡዚድ ነው የመጡት። በዚያች ከተማም ነበረ ያኔ ፍራፍሬና ቅጠላ-ቅጠል በመሸጥ ይተዳደር የነበረው ሙሐመድ ቡዓዚዚ፤ በራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፉ በማቃጠል ሕይወቱን ያጠፋው።ቡዓዚዚ፣ የድህነት ኑሮና የፖሊስ ወከባ፤ የቤን ዓሊን አምባገነን አገዛዝ ለመጠበቅ፣ በህዝብ ላይ

ይፈጽም የነበረው ግፍና ንቀት አንግሽግሾት ነበር። 3 ዓመት ሆነ ሕይወቱን ካሳለፈ! ጋዚ እ ጎ አ ታኅሣሥ 17 2010 ን ምንጊዜም ነው የሚያሳታውሱት።

«ቡዓዚዚ ሞቷል። የኛ ጀግና ነው። የአብዮትን ፍንዳታ ዐይተናል። ግን ጥያቄአችን፤ እስካሁን የተሟላ ምላሽ አላገኘም። ለዚህ ጥያቄም ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ተሠውቷል። በሺ የሚቆጠሩ ቆስለዋል። የአነዚህ ሰማእታት ጉዳይ እስከዛሬ በጥሞና አልተመረመረም። ያን ከማድረግ ይልቅ፤ ይህን አርቃቂ ኮሚቴ ነው የመረጥን። እናም ፓርላማው በአብዮቱ ላይ ክህደት ፈጽሟል። አብዮታችን መሥመሩን ስቷል።»

በፓርላማው ህንጻ ውስጥ አዘውትረው የሚገኙት ሜሬዚያ ላቢዲ፣ ከዚህ የተለየ አመለካከት ነው ያላቸው። ላቢዲ ፤ የኢናኻዳ ፓርቲ አባልና ሕገ-መንግሥት የሚያሰናዳው ም/ቤትም ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው። ቱኒሲያ፤ አድካሚና አዝጋሚም ቢሆን፤ በአዲሱ ህገ መንግሥት በጥሩ ጎዳና ነው የምትራመደው።

Opfer der Jasmin-Revolution...die Vergessenen in den tunesischen politischen Krisen
ምስል DW/Guizani Tarak

እርግጥ ሕዝቡ፣ ለዴሞካራሲ ሥርዓት ሲል ሃይማኖቱን ችላ የሚልበት ሥጋት አልተደቀነም ማለት አይቻልም ሲሉም ላቢዲ ተናግረዋል። እኒሁ የፓርላማ አባልም፤ ቡዓዚዚን እንደማይረሱት ነው የገለጹት። እንዳጋጣሚ እርሱ፤ ራሱን በገዛ እጁ ያቃጠለበት ዕለት የእርሳቸው የልደት ቀን ነውና!

«እሳት የዚያን ወጣት ሰው ገላ አቃጥሎ ለሞት ዳርጎታል። ተስፋችንና ተግባራችንም፤ ይኸው እሳት፣ ዘለዓለማዊ በመሆን፤ በቱኒሲያ በመላ ላገራችን ወጣቶች የሰብአዊ ክብር ነበልባል ሆኖ እንዲቀጥል ማብቃት ነው። »

ከዚያ ውጭ ትርምስ ባለበት ቦታ የሚገኙት ግን ፣ አመለካከታቸው ፍጹም የተለየ ነው።

DW 60 Jahre Tunesien Proteste Mohamed Bouazizi 14.01.2012
ምስል Fethi Belaid/AFP/Getty Images

«አገራችን በሳላፊስቶች አመራር በድህነትና በሥራ አጥነት በመማቀቅ ላይ ናት። በየቦታው የጎስቋሎችን ሠፈሮች ተመልከቱ። ሁኔታው ፤ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው። ይህ ራሱ፣ ሌላ አዲስ አብዮት ጋባዥ ነው። ምናልባት ነገ ላይሆን ይችላል፤ ግን ውሎ አድሮ ፣ ሕዝቡ መነሣሣቱ አይቀሬ ነው።»

ከፓርላማው አጠገብ የመሸጉት ሰዎች የረሃብ አድማ እንዳደረጉ በዚያ ይቆያሉ፤ የሲዲ ቡዚዱ ፣ ሙሐመድ ቡዓዚዚ፣ በከንቱ መስዋእት እንዳልሆነ የፓርላማ አባላቱን አጥብቀው ማስገንዘብ ይሻሉና!

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ