1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦኮ ሃራም

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2007

በናይጀርያ የሚንቀሳቀሰዉ ቦኮሀራም የሚባለው እስልምና አክራሪ ቡድን ጥቃት በጎረቤት ሃገራት በመዛመቱ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ሥጋት ፈጥጥሯል። ቡድኑ ታኅሣሥ 26 ቀን፤ 20017 መጨረሻ በናይጀርያ የሚገኘዉን የአህጉሪቱን የጥምር ወታደራዊ ጦር ሰፈር በቁጥጥሩ ሥር ማድረጉ ይታወቃል።

https://p.dw.com/p/1EFnN

በሌላ በኩል ይኸዉ ፅንፈኛ ቡድኑ በካሜሩን ጥቃትን ጥሎ 15 ሰዎች መገደላቸዉ ተመልክቷል። በናይጀርያ የሚንቀሳቀሰዉ እስልምና አክራሪ ቡድን «ቦኮ ሃራም» ታኅሣሥ 26 ቀን፤ 20017 ዓም ነበር በሰሜናዊ ምስራቅ ናይጀርያ ባጋ ከተማ የሚገኘዉ ዓለም አቀፍ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ጥሎ በቁጥጥሩ ሥር ማድረጉ የተሰማዉ። ቡድኑ ይህን የጦር ሰፈር በጥቂት ሠዓታት የተኩስ ልውውጥ እንደተቆጣጠረ፤ የአዉቶማቲክ መሳርያርያዎችና የታንክ መከላከያ ሮኬቶችን ሁሉ በጁ ማስገባቱ ነዉ የተመለከተዉ። ከዚህ በኋላ ነበር በጦር ሰፈሩ የነበሩት ወታደራዊ ኃይላቱ ቦታዉን ለቀዉ የሸሹት። ቡድኑ የጦር ሰፈሩን ከተቆጣጠረና በርካታ አዉቶማቲክ ከባድ መሳርያዎችን እጁ ካስገባ በኋላ ከተማዋንም በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎአል። በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ የባጋ ከተማ ነዋሪዎች ከተማዋን እየለቀቁ ወጥተዋል። ከኒጀር፤ ከቻድ እንዲሁም ከካሜሩን የምትዋሰነዉ የሰሜናዊ ምሥራቅ ናይጀርያ ከተማ ባጋ በቦኮ ሃራም እጅ መውደቋ በከተማዋ ዙርያ ለሚገኙት አዋሳኝ ሃገራትም ከፍተኛ ሥጋትን ደቅኗል። በናይጀርያ የደሕንነት ጉዳይ ተንታኝ ካቢሩ አዳሙ እንደሚሉት የጦር ኃይላቱ ይህን ዓይነት ጥቃት ለመመከት ምንም ያህል ዝግጅት አላደረጉም፤ ይህ ደግሞ ተቀባይነት የሌለዉ ጉዳይ ነዉ።

« እውነታው ፅንፈኛ ቡድኑ የጦር ሰፈሩን ብቻ ሳይሆን አካባቢዉን ሁሉ በቁጥጥሩ ሥር ማድረጉ እርግጥ ነዉ። የጦር ሠፈሩ ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ቀድሞ የታወቀ ነበር። ታዲያ የናይጀርያ የጦር ኃይል ይህን አይነቱን ጥቃት ለመከላከል ለምንድ ነዉ ዝግጅት ያላደረገዉ? ቡድኑ በጣም በቀላልና እጅግ በጥቂት ጊዜ ዉስጥ የወታደራዊዉን ጦር ሰፈር መቆጣጠሩ መቻሉ ተቀባይነት የሌለዉ ጉዳይ ነዉ።»

በጎርጎሪዮሳዊው 1998 ዓ.ም. የተለያዩ የአካባቢው ሃገራት ጥምር ኃይል በእንግሊዘኛ አፅኅሮቱ «MNJTF» በሚል ይታወቃል። በሰሜናዊ ናይጀርያ የተቋቋመዉ ይኽ ወታደራዊ ማዕከል፤ የአራት ምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ማለትም የናይጀርያ፤ የካሜሩን ፤ የቻድ እና የኒጀር የጦር ኃይሎች የሰፈሩበት ነዉ። እነዚህ ሃገራት ቦኮ ሃራምን ለማጥቃት በየሃገራቱ ወደ 700 ወታደሮችን በአጠቃላይ 2800 ወታደራዊ ኃይላቸዉን ለመላክና ለማጠናከር ተስማምተዉ ነበር። ሃገራቱ ይህን እቅዳቸዉን ሳያሳኩ ፅንፈኛዉ ቡድን የጦር ሰፈሩ ላይ ጥቃት ጥሎ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎታል። ቦኮ ሃራም በባጋ ከተማ የሚገኘዉን የጦር ሰፈር ሲቆጣጠር ቦታዉ ላይ የነበሩት የናይጄርያ ጦር ኃይሎች ብቻ እንደነበሩ ነዉ የተመለከተዉ። ወታደሮቹ የቦኮ ሃራምን ጥቃት በመሸሽ ቻድ አዋሳኝ ወደ ሆነዉ ከፊል በረሃማ አካባቢ መሸሻቸዉ ተዘግቦቧል። ቦኮ ሃራም ይህን የጦር ሰፈር በቀላሉ መቆጣጠሩን በተመለከተ በናይጀርያ ወታደራዊ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ወቀሳና ትችት እየተሰነዘረ ነዉ። እንደ ሂስ አቅራቢዎቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጽንፈኛ ቡድኑ ባጋ ከተማ ላይ አራት ግዜ ጥቃት አድርሶአል። የናይጄርያ ጎረቤት ሃገር በሆነችዉ በኒጀር የከፍተኛ ወታደራዊ አመራር አባል የነበሩት አቦ ኦማሩ እንደሚሉት የቦኮ ሃራምን አይነት ጥቃቶች መከላከል ቀላል አይደለም።

« እንዲህ አይነቱን ጥቃት መከላከል ቀላል አይደለም። «ቦኮ ሃራም» በጎረቤት ሃገራቱ ጥምር ጦር ፊት ለፊት አግኝተህ የምትገጥመው ወታደራዊ ቡድን አይደለም። «ቦኮ ሃራም» በአንፃሩ የዉጭ ወታደራዊ ኃይላትን ለማጥቃት በማሕበረሰብ ዉስጥ ተደባልቆና ተደብቆ የሚጣልበትን ጥቃት የሚከላከል ቡድን ነዉ። ስለዚህም ከዚህ ቡድን ጋር የግድ ተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ እና መወያየት ያስፈልጋል»

እንድያም ሆኖ ወረራዉን ወደ ምሥራቅ በኩል እያሰፋ ወደ ናይጀርያ፤ ቻድና ካሜሩን እየዘለቀ በመጣዉ ቦኮ ሃራም ላይ ናይጀርያ ዉስጥ ያለዉ የሃገራቱ ጥምር የጦር ኃይል ለምን ጥቃት እንደማይሰነዝር ግን ግልፅ አይደለም።
የናይጀርያዋ ባጋ ከተማና፤ በከተማዋ ያለዉ የወታደራዊ ጦር ሰፈር በፅንፈኛዉ እጅ ከወደቀ በኋላ በቀጣይ ማይዱጉሪ የተሰኘችዉ የናይጀርያዋ ቦርኖ አዉራጃ ዋና ከተማ በቦኮ ሃራም እጅ ስር ትወድቃለች የሚል ስጋትን ቀስቅሷል። የናይጀርያዉ ቦርኖ አዉራጃ ፅንፈኛዉ ቡድን ቦኮ ሃራም በብዛት ተከማችቶ የሚገኝበት ቦታ እንደሆነም ተመልክቶአል። አዳማዋ እና ዮቤ የተሰኙት የናይጀርያ ትልልቅ ከተማዎችም በዚሁ ፅንፈኛ ቡድን እጅ ሳይያዙ አይቀርም የሚል ሥጋትም አለ። ቦኮ ሃራም አብዛኛዉን የሰሜናዊ ናይጀርያን ግዛት በመቆጣጠሩ እና ነዋሪዎች አካባቢዉን በመልቀቃቸዉ ወይም ፍርሃት በመንገሱ አካባቢዉ ላይ የሀገሪቱ ሕጋዊ የምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ገቢራዊ እንደማይሆን ተመልክቶአል። በናይጀርያ በሚደረገዉ ምርጫ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታንና ሕዝባዊ ዲሞክራስያዊ ፓርትያቸዉ ቢያሸንፉ በሀገሪቱ የሚገኙት የመንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫዉ ትክክለኛ ያልሆነ ሲሉ ዉድቅ ማድረጋቸዉ አይቀሬ ነዉ። በናይጀርያ ከዚህ ቀደም በታየዉ ልምድ መሰረት ይህ አይነቱ ጉዳይ የሀገሪቱን ሰላም ደህንነትና መረጋጋት ሊያደፈርስ እንደሚችል ይገመታል።

Nigeria - Jäger im Kampf gegen Boko Haram
ምስል DW/Hassan
Infografik Anschläge von Boko Haram BRA


አዜብ ታደሰ / ካትሪን ማታይ


ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ