1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የቦይንግ 737 ማክስ ፈተና

ረቡዕ፣ መጋቢት 4 2011

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ርዕይ 2025 የተባለ ዕቅዱን ለማሳካት በ2.1 ቢሊዮን ዶላር 20 የቦይንግ 737 አውሮፕላኖች አዟል። አየር መንገዱ ከአምስት አመታት በፊት ከቦይንግ በገባው ውል ተጨማሪ 15 ተመሳሳይ አውሮፕላኖች የመግዛት ዕድል አለው። በነዳጅ ቆጣቢነቱ ተቀባይነት ያገኘው 737 ማክስ ግን በኤጀሬ ከደረሰው አደጋ በኋላ ጥያቄ በዝቶበታል።

https://p.dw.com/p/3EwTo
Äthiopien Flughafen Addis Ababa Ethiopian Airlines Boeing 737
ምስል Reuters/A.A. Dalsh

ኢትዮጵያ አራት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ አግዳለች

ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ርዕይ 2025 የተባለ ዕቅድ እሁድ ማለዳ ከአዲስ አበባ በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የጀርባ አጥንት ያክል ነበር። አሰቃቂው አደጋ የ32 ኬንያውያን፣ 18 ካናዳውያን፣ የ9 ኢትዮጵያውያን ጨምሮ የ157 መንገደኞችን ሕይወት ሲቀጥፍ አውሮፕላኑ ብትንትኑ ወጥቶ ታይቷል። የሕክምና ዶክተሮች፣ አምሳደሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ ተማሪዎች እና መምህራን ጭምር ከሟቾቹ መካከል ይገኙበታል።

አውሮፕላኑ ሲወድቅ የቆፈረውን ጉድጓድ እና የአካላቱን መበጣጠስ የተመለከቱ የዘርፉ ባለሙያዎች በከፍተኛ ፍጥነት እና ኃይል ሳይከሰከስ አልቀረም የሚል ጥርጣሬ አላቸው። ነገር ግን ከድምዳሜ ለመድረስ የበርካታ አገራት ባለሙያዎች ምርመራ፤ ረዥም ጊዜ እና ትዕግሥትን ይሻል። የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስቴር መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የአደጋውን መንስኤ የሚያጣራ ኮሚቴ አዋቅሯል። በምርመራው ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ካቀኑት መካከል የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርትር ደኅንነት ቦርድ (National Transportation Safety Board) ባለሙያዎች ይገኙበታል።

Äthiopien Flugzeugabsturz Ethiopian Airlines Flight ET 302
ምስል Getty Images/AFP/M. Tewelde

የቦይንግ 737 ማክስ 8 ዕገዳ

ካፒቴን ያሬድ ጌታቸው የሚያበሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 ቦይንግ 737 -8 ማክስ ከተከሰከሰ በኋላ መሰል አውሮፕላኖችን በማገድ ቻይና ቀዳሚ ሆናለች። ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያን፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሲንጋፖር፣ ብራዚል፤ ኔዘርላንድስ፣ አየርላንድ ቦይንግ ኩባንያ የሚኮራበትን 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከበረራ አግደዋል። አገሮቹ በአውሮፕላኑ ላይ ያስተላለፉት ገደብ ጥብቅ ሆኗል። የጀርመን የትራንስፖርት ምኒስትር አንድሪያስ ሹወር የመንግሥታቸውን ውሳኔ ካሳወቁ በኋላ ቅድሚያ ለደኅንነት ብለዋል። ምኒስትሩ "ጥርጣሬ የፈጠሩ ጉዳዮች ሁሉ ግልፅ እስኪሆኑ ድረስ የጀርመን ሰማይ ለ737 ማክስ አውሮፕላኖች ዝግ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፊያለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

ጀርመንና እና ዩናይትድ ኪንግደም የየትኛውም አየር መንገድ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከሀገራቸው አየር ማረፊያዎች እንዳይነሱ፤ እንዳያርፉ እና የአየር ክልላቸውን እንዳያቋርጡ እገዳ ጥለዋል።

የቻይና ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ሉ ካንግ "የቻይና የሲቪል አቪየሽን አስተዳደር በቦይንግ 737 ማክስ 8 ላይ የተጣለው ገደብ የሚነሳው ከዩናይትድ ስቴትስ የአቪየሽን አስተዳደር ማረጋገጫ ሲገኝ እና  ይኸው አውሮፕላን ደሕንነቱ የተረጋገጠ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ እርምጃዎች በኩባንያው ሲወሰዱ እንደሆነ ብቻ በግልፅ አስቀምጧል። ስለዚህ በደሕንነት ላይ ለተጋረጡ አደጋዎች መፍትሔ ሳይገኝ ገደቡ የሚነሳበትን ቀነ ገደብ ለመናገር ከባድ ነው። ይኸ የመንገደኞችን ደሕንነትም ለማረጋገጥ ኃላፊነት የተሞላበት እርምጃ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

Air China will 60 Boeing 737 bestellen
ምስል picture-alliance/dpa/Ch. Kang

በቦይንግ 737 ማክስ 8 ላይ እገዳ ለመጣል ቸልተኛ የሆነችው አሜሪካም ብትሆን ጉዳዩ ፈተና ውስጥ የከተታት ይመስላል። የአሜሪካ መንገደኞች በኢትዮጵያ ከደረሰው አሰቃቂ አደጋ በኋላ 12.3 ሜትር ከፍታ እና 39.52 ሜትር እርዝመት ባለው ቦይንግ 737 ማክስ ለመሳፈር ዳተኛ ሆነዋል። የመንገደኞች እምቢታ ተደጋጋሚ የቅያሬ ጥያቄ ለሚቀርብላቸው አየር መንገዶች ፈተና ሆኗል።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ ሲከሰከስ በጥቂት ወራት ውስጥ ሁለተኛ ጊዜው ነው። ባለፈው ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢንዶኔዥያ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 መንገደኞች እና የበረራ ሰራተኞችን ጨምሮ የ189 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ሁለቱ አሰቃቂ አደጋዎች የደሕንነት ተቆጣጣሪዎች እና አምራቹን ኩባንያ ግራ አጋብቷቸዋል። አውሮፕላኑ ደሕንነቱ የተጠበቀ ነወይ የሚሉም አልጠፉም።

የኢቢሲንያ አቪዬሽን አካዴሚና የበረራ አገልግሎት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን አማረ ገብረሃና "አደጋው ተመሳሳይ ነው የሚመስለው። [በመጀመሪያው] አደጋ ምርመራ ላይ  የ[አሜሪካ] ፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር እና የቦይንግ ኩባንያ ሲነጋገሩበት የነበረ እና ወደ ተግባርም ይሔዳሉ ተብሎ የሚጠበቅም ነገር ነበር። ከዚያ ጋር የተያያዘ ይሁን አይሁን በዚህኛው ላይ ይኸ ነው ለማለት አይቻልም። ዘመናዊ የሆነ አውሮፕላን በአብዛኛው በሲግናል ነው የሚሰራው። ሲግናሎች በትክክለኛውም መንገድ ሊፈጠሩ ይችላሉ። ወይም ትክክለኛም ባልሆነ መንገድ ሊፈጠሩ ይችላሉ። በዚህም ሆነ በዚያ የተፈጠሩ ሲግናሎች ወይም መልዕክቶች የሚፈለገው ቦታ ላይ ሲደርሱ የተሳሳተ ሲግናል ሊሰጡ ይችላሉ። ያ የተሳሳተ ሲግናል ደግሞ የተሳሳተ መልዕክት ነው። የተሳሳተ መልዕክት ደግሞ አውሮፕላኑ የተሳሳተ ጠባይ ያሳያል ማለት ነው ወይም በተሳሳተ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል ማለት ነው። ከዚያ ጋር የተያያዘ አንዳንድ ነገሮች እንዳሉት ሰነዶች ያሳያሉ። ግን አሁን ይኸ ነው ለማለት አይቻልም። ለዚህ ነው አሁን አንዳንድ አየር መንገዶች ምርመራው እስኪያልቅ ድረስ አውሮፕላኑን የማቆም እርምጃዎች የወሰዱት" ሲሉ ያብራራሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና 737 ማክስ

ከእነዚህ አደጋዎች በፊት ግን ቦይንግ 737 ማክስ 8 የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሳሰሉ ተቋማት እና አምራቹ ኩባንያ ከፍ ያለ ተስፋ የጣሉበት ነበር።

ከፍ ያለ ውድድር በሚስተዋልበት የአውሮፕላን ገበያ የአውሮጳ አገሮች ንብረት የሆነው ኤር ባስ ከዘጠኝ አመታት ገደማ በፊት ኤ-320 (A320) የተባለ ሞዴሉን ይፋ አደረገ። ይኸ የኤር ባስ ሞዴል በዓለም ገበያ ከፍተኛ ተቀባይነት ለማግኘት የረዳው ነዳጅ ቆጣቢነቱ ነበር። ይኸ ለቦይንግ በዓለም ገበያ የተሰነዘረ የከፋ ጥቃት ነበር። ኩባንያው በጥቂት ወራት ውስጥ 737 ማክስ የተባለ ሞዴል አውሮፕላኑን ነዳጅ ቆጣቢ አድርጎ ብቅ አለ። የአቪየሽን ባለሙያው ጆን ስትሪክ ላንድ "የቦይንግ 737 የአውሮፕላን ዝርያ በመላው ዓለም በሚገኙ አየር መንገዶች ተደናቂ ነው። የዚህ አውሮፕላን የቀደሙ ሞዴሎች ሥራ ላይ ከዋሉ ከ50 አመታት በላይ ቢቆጠሩም 737 ማክስ ግን እጅግ የተሻሻለ ሲሆን በረራ ከጀመረም ሁለት አመታት አልሞላውም። አውሮፕላኑ ጭነት የመሸከም አቅሙ የተሻሻለ ሲሆን እጅግ ነዳጅ ቆጣቢ ነው። በዚህም ምክንያት ቦይንግ ለዚህ ሞዴል ብቻ 5,000 ገደማ ትዕዛዝ ተቀብሏል። 350 ያህሉ ደግሞ ሥራ ላይ ናቸው። ስለዚህ እጅግ ተቀባይነት ያገኘ የአውሮፕላን ሞዴል ሲሆን ወደፊትም ይቀጥላል" ሲሉ ስኬቱን ይገልጻሉ።

ቦይንግ እጅግ ዘመናዊ ሲል ያሞካሸውን 737 ማክስ 8 ከመስራት ባሻገር ደንበኞቹን እና የአሜሪካ የአቪየሽን ባለሥልጣናትን አብራሪዎች ያለ ውድ ተጨማሪ ስልጠና ሊያበሩት ይችላሉ ብሎ ማሳመኑን ኒው ዮርክ ታይምስ ፅፏል። 

በአፍሪቃ ሰማይ ስመ-ጥር የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦይንግ 737 ማክስ 8 ተስፋ ከጣሉ አየር መንገዶች መካከል አንዱ ነበር። የቦይንግ ኩባንያ በመስከረም 2014 ዓ.ም. በድረ-ገፁ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚጠቁመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ  20  አውሮፕላኖች ለማሰራት ትዕዛዝ ሰጥቷል። በድረ-ገፁ መሰረት ይኸ 2.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ትዕዛዝ ነው። አየር መንገዱ ከቦይንግ በገባው ውል መሠረት ሌሎች 15 ተመሳሳይ አውሮፕላኖች የመግዛት ዕድል ጭምር ነበረው። ይኸ ቁጥሩን ወደ 35 ከፍ ያደርገዋል። በቦይንግ ኩባንያ አባባል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖቹን ለመግዛት የገባው ስምምነት በብዛት ከሌሎች የአፍሪቃ አየር መንገዶች ከፍተኛ ብልጫ ነበረው።

በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ስምምነቱ ኩባንያቸው በ2025 ሊደርስበት ላቀደው ስኬት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ዕምነታቸውን ገልጸዋል። አቶ ተወልደ "የዛሬው ትዕዛዝ ርዕይ 2025 በተባለው ዕቅዳችን በአመት 18 ሚሊዮን መንገደኞች በማጓጓዝ በአፍሪቃ ቀዳሚ ለመሆን ለያዝንው ውጥን የቁርጠኝነታችን ማረጋገጫ ነው" ብለው ነበር። ዋና ሥራ አስፈፃሚው 737 ማክስ በአፍሪቃ የአቪየሽን ገበያ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ቀዳሚ በማድረግ የርዕይ 2025 የጀርባ አጥንት ይሆናል የሚል ተስፋ ነበራቸው።

Symbolbild A320 Cockpit
ምስል picture alliance/ROPI

በቦይንግ ኩባንያ የደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካ እና ካሪቢያን የሽያጭ ክፍል ኃላፊ ቫን ሬክስ ጋላርድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ትዕዝዛ ለአየር መንገዱም ሆነ ለኩባንያቸው ታሪካዊ እንደሆነ ገልጸው ነበር። ኃላፊው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ737 ማክስ ባለቤት በመሆኑ በአፍሪቃ አየር የሚስተካከለው አይኖርም ሲሉ ተስፋ ሰጥተዋል።

የቦይንግ 737 ማክስ ተስፋ የሆነው ግን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ተመሳሳይ ኩባንያዎች ብቻ አልነበረም። የአቪየሽን ተንታኙ ቲም ሔፈር "737 ለቦይንግ እጅግ አስፈላጊ ነው።  አውሮፕላኑ የኩባንያው የገቢ እና የትርፍ ምንጭ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚገኙ አየር መንገዶች የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል። በየሰከንዱ በተለያየ የዓለም ክፍል አንድ 737 አውሮፕላን ለበረራ ይነሳል። ይኸ አውሮፕላን በአየር መንገዶችም ሆነ በቦይንግ መፃኢ ጊዜ እጅግ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል" ሲሉ ይናገራሉ። አውሮፕላኑ ተቀባይነት ይኑረው እንጂ በኢትዮጵያ ከደረሰው አደጋ በኋላ ጥርጣሬ ውስጥ መውደቁ ቦይንግ በዓለም ገበያ በነበረው ዋጋ ላይ ቅናሽ እንዲገጥመው አድርጓል። ቲም ሔፈር "ይኸ ባለወረቶች አሁን በኢትዮጵያ አየር መንገድ  ከዚህ ቀደም ደግሞ በላየን አየር መንገድ ላይ የደረሱት አደጋዎች በኩባንያው እና በትርፍ ላይ የፈጠሩባቸውን ሥጋቶች ነጸብራቅ ነው" ሲሉ የኩባንያው ዋጋ ያሽቆለቆለበትን ምክንያት ያስረዳሉ።  

የቦይንግ ኩባንያ በዓለም አቀፍ የአክሲዮን ገበያ የነበረው ዋጋ በ7 በመቶ ያሽቆለቆለ ሲሆን 737 ማክስ አውሮፕላኖችን የሚያግዱ አገሮች ቁጥርም ተበራክቷል።

በርካቶች ግን አይናቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተከሰከሰበት ኤጀሬ በተገኘው የመረጃ መመዝገቢያ ሰንዱቅ ላይ አሳርፈዋል። በሰንዱቆቹ የሰፈረው መረጃ ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ካፒቴን አማረ እንደሚሉት ግን ምርመራው ረዥም ጊዜ እና ውስብስብ ሒደት ማለፍ ይኖርበታል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ