1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድና የተደፈረችዉ ሕፃን

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 12 2007

የተራቡ-የተጠሙትን በምግብ መጠጥ፤ ሌሎቹን በሳንቲም እያባባሉ፤ በመጫዎቻ እያታለሉ፤ የፈሩትን ከለላ እንሰጣችኋለን እያሉ-አካላቸዉንም፤ ልቡናቸዉንም፤ ቅስማቸዉንም የሚሰብር ግፍ ዉለዉባቸዋል።

https://p.dw.com/p/1GHNz
ምስል picture alliance/AA/Str

ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሠፈረዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት( MINUSCA) አባላት በደል ካደረሰቡባቸዉ ልጆች መካከል ቢያንስ አንዷን እንደሚረዳ ድርጅቱ አስታወቀ።ዓለም አቀፉ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) እንዳስታወቀዉ በሠራዊቱ ባልደረባ የተደፈረችዉን አንዲት የ12 ዓመት ታዳጊ ወጣትና ወላጆችዋን ይረዳል።ሠላም ያስከብራሉ ተብለዉ የዘመቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የፈረንሳይ ወታደሮች ለአካለ-መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ጭምር መድፈራቸዉን የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ ሲያስታዉቁ፤ አፈጣኝ እርምጃም እንዲወሰድ ሲጠይቁ ነበር።ድርጅቱ ታዳጊዋን ወጣት ለመርዳት ቃል ከመግባቱ በስተቀር ሌሎች ተበዳዮችን ለመርዳትም ሆነ በዳዮችን ለመቅጣት ሥለ ማቀድ አለማቀዱ ያለዉ ነገር የለም።

የአስራ-ሁለት ዓመትዋን ታዳጊ ወጣት ደፈረ የተባለዉ አንድ ወታደር ነዉ።የወታደሩ ማንነት፤ የዜግነቱ የትነት፤ በደሉን ያደረሰበት ጊዜ መቼነት በዉል አልተገለጠም። የተጣለበት ቅጣት እንዴትነት ወይም ሥለመቀጣት አለመቀጣቱም-እንዲሁ።የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) የበላይ አንቶኒ ሌክ አሉ-እንደተባለዉ ግን ልጅቱ ከፍተኛ ግፍ ተዉሎባታል።መረዳትም አለባት።አከሉ ቃል-አቀባይ ቫኒና መስትሮክቺሶ

«ሚስተር ሌክ፤ ልጅቱ ከፍተኛ ግፍ የተዋለባት መሆኑ ግልፅ ነዉ ብለዋል።ዩኒሴፍ ለተበዳይዋና ለቤተሰቦችዋ የሕክምና፤የሥነ-ልቡና እና የሕግ ምክርን ጨምሮ የተለዩ ድጋፎችን እንደሚሰጥም አስታዉቀዋል።»

Zentralafrikanische Republik. Bangui Sangaris Operation MISCA
ምስል Pacome Pabandji/AFP/Getty Images

አርማ፤መለዮ-ባንዲራቸዉ፤ ተልዕኳቸዉን ገላጭ ነዉ።ነጭ ገሚስ ክፍት ጎባባ ዘምባባ-የተለጠፈበት ዉሐ-ሰማያዊ አርማ፤ መለዮ- ባንዲራ።የጋራነት፤ የገላጋይ-ሽምጋይነት፤ የደከሞች ረዳትነት ተምሳሌት። ሠላም የማስከበር መለያ።የዓለም አቀፋዊነት መታወቂያ።አንዳንዴ ግን ግባሩ ከተልዕኮ-ምልክቱ ይቃረናል።በተለይ አፍሪቃ ላይ ይደጋጋማል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ዳርፉር የሠፈረዉ ሠራዊት ባልደረቦች ከለላ ድጋፋቸዉን በሚሹ ሴቶች፤ ሕፃናትና ልጆች ላይ የዋሉትን ግፍ-ሠምተን ነበር።ከዚያ በፊት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ።ሶማሊያም ዉስጥም ብዙ ግፍ መድረሱ-ብዙ ጊዜ ተነግሯል።ግን የዘመተዉ ጦር፤ አንደኛ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕዝና ቁጥጥር ሥር ባለመሆኑ-ሁለተኛ ተበዳዮች አደባባይ ወጥተዉ መናገሩን ከተጨማሪ «ዉርደት» ሥለሚቆጥሩት፤ ሰወስተኛ፤- ወቀሳዉን የሚቀብር ዉጊያ በመኖሩ ዝም-ተባለ።ፀጥ።

UN-Finanzierungskonferenz in Addis Abeba
ምስል DW/I. Hell

አሁን ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ናት።አምንስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ እንዳሉት ኋላ የዓለም አቀፉን ድርጅት ሰማያዊ መለዮ ያጠለቁት የፈረንሳይ ወታደሮች ሴቶችን እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ወንድ-ከሴት ሳይለዩ ደፍረዋል።የተራቡ-የተጠሙትን በምግብ መጠጥ፤ ሌሎቹን በሳንቲም እያባባሉ፤ በመጫዎቻ እያታለሉ፤ የፈሩትን ከለላ እንሰጣችኋለን እያሉ-አካላቸዉንም፤ ልቡናቸዉንም፤ ቅስማቸዉንም የሚሰብር ግፍ ዉለዉባቸዋል።

የፈረንሳይ ሹማምንት «ይጣራል» በሚል ማዘናጊያ ጉዳዩን እስካሁን እንዳስተኙት ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለስልጣናት ግን ወቀሳ፤ ትችት፤ ጩኸቱን እንደ ፓሪሶች «ለማረሳሳት» ያደረጉት ሙከራ ከወራት በላይ አልሰራላቸዉም።በቃ-በቃ አሉ ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን።

«ለጉዳተኞቹ-የምናገረዉ-እኛ ከጎናችሁ ነን።በቃ በቃ ነዉ።»

ሁለተኛዉ ለበታቾቻቸዉ ሳይሆን አልቀረም።ፓን አቅማምተዉ፤ አመንትተዉ ቢሆንም በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የድርጅታቸዉ ሐላፊ ባባካር ጌይን ሥልጣን እንዲለቁ አስገደዷቸዉ።ቃል አቀባይ መስትሮክቺሶ እንዳሉት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በደሉን የሚያጣራ ኮሚሽን ሰይሟልም።

«የሰብአዊ መብትና የሕፃናት ጥበቃ ክፍል እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ፖሊስ ያሰባሰቡት መረጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራዊት ያደረሳቸዉን በደሎች እንዲመረምር ሥልጣን ለተሰጠዉ አጣሪ አካል (OIOS) ተሰጥተዋል።»

የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ግፍ የተዋለዉ በበርካታ ሰዎች በመሆኑ ጉዳዩ በቅጡ እንዲጣራ መጎትጎታቸዉን አላቋረጡም።ግንባር ቀደሙ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ