1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድና የዓለም ሠላም

ሰኞ፣ ጥቅምት 15 2008

ድርጅቱ ዓለም አቀፍ ማሕበር በመሆኑ ሕጉ የሚከበረዉ አባላቱ በተለይ ደግሞ ሐያል መንግሥታቱ ሕጉን በትክክል አክብረዉ ሲያስከብሩትና ሲተባበሩ ብቻ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GuVT
ምስል Reuters/L. Jackson

የተመድና የዓለም ሠላም

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዘቬልት በ1942 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እንደዘበት ያሉት ዛሬ ለምናቀዉ ግዙፍ ድርጅት ጥንስስነት ይበቃል ብሎ የገመተ ከነበረ-እሱ በርግጥ ነብይ ነበር።የዚያ ዘመኑ ሐይል ዓለም ጎራ ለይቶ በሚጠፋፋ፤ ዓለምን በሚያጠፋበት መሐል ፕሬዝደንት ሩዘቬልት «የተባበሩት መንግሥታት» ሲሉ የበርሊን፤ሮም፤ ቶኪዮ ጠላቶቻቸዉ የሚመሯቸዉን ሐይላት የሚወጉትን መንግሥታት ትብብር ባንድ ስም ለመጥራት ነበር።በሰወስተኛ ዓመቱ ግን ሩዘቬልት ያወጣቱት ስም፤ የዓለም ማሕበር መጠሪያ ሆነ።1945።ያን ስም የያዘዉ የዓለም ማሐበር ዘንድሮ-ቅዳሜ ሰባኛ ዓመቱን ደፈነ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስም፤ ዓላማ፤ ምግባሩ ስኬት-ዉድቀት የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ ።

«እኛ የተባበሩት መንግሥታት ሕዝቦች፤ተከታታዩን ትዉልድ ከጦርነት መንፈስ ለመከላከል ቆርጠናል።ጦርነቱ በኛ የሕይወት ዘመን በሰዉ ልጅ ላይ ተነግሮ የማያዉቅ ጥፋትና ሐዘን አድርሷል።---ለመሠረታዊ የሠብአዊ መብቶች፤ለሰዉ ልጅ ክብር፤ለሴቶችና ወንዶች እኩልነት፤ለሐገራት ትንሽም ሆኑ ትልቅ እኩልነት መከበር ቆመናል።---ዓለም አቀፍ ሕግጋት እንዲጠበቁ፤ ፍትሕና ሐላፊነት በተገቢዉ መንግድ መወጣት ከሚደርስባቸዉ አደጋ ለመከላከል ለመጠበቅ፤ ማሕበራዊ ዕድገትን ለማስረፅና ሰፊ ነፃነት የተላበሰ የተሻለ ኑሮን ለመመስረት እንጥራለን።---እንደ ጥሩ ጎረቤት በሠላም አብሮ ለመኖር መቻቻልን ገቢር ለማስፈን፤ ዓለም አቀፍ ሠላምን ለማስፈን-----»

USA UNO Konferenz Libyen
ምስል Getty Images/A. Burton

እያለ ይቀጥላል።

«በዚሕ የተባበሩት መንግሥታት መተዳደሪያ ደንብ ተስማምተናል።እነሆ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት መሥርተናል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዘላለም ይኑር»

ዋና ፀሐፊ ፓን ጊሙን እንደሚሉት ከሰባ-ዓመት በፊት የቅዳሜን ዕለት የመጀመሪያዉን ጠቅላላ ጉባኤዉን ያደረገዉ ድርጅታቸዉ በሰባ-ዓመት ታሪኩ አያሌ ምግባሮችን አከናዉኗል።የአባላቱ ቁጥርም በአራት እጥፍ ገደማ አድጓል።

«ተቋማችን በጎ ምግባሮቹንና እራሱን ከተለዋዋጩ የዓለም ሁኔታ ጋር ለማጣጣም ያደረጋቸዉን ለዉጦች ሲያስታዉስ በኩራት ነዉ።ዛሬ፤ ድርጅታችን በ1945 ከነበሩት አባላት በአራት እጥፍ የጨመሩ አባላት አሉት።ዓለማችን በአፅናፋዊዉ ትብብር ይበልጥ እየተለወጠች ነዉ።»

ይበሉ እንጂ የግዙፉን ድርጅት ሁለንተናዊ ሥራና መርሕ የሚዘዉረዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ነዉ።የምክር ቤቱ አባላት፤ በተለይም ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉ መንግሥታት ቁጥር ዛሬም እንደ ዛሬ ሰባ ዓመቱ ነዉ።አምስት።የድርጅቱ አባል መንግሥታት በአራት እጥፍ ካደገ፤ ዓለም ብዙ ከተለወጠች የድርጅቱ መዋቅር፤ ሥራና አሠራር፤ ከተለወጠችዉ ዓለም ጋር መለወጥ ነበረበት።የድርጅቱ መርሕ አርቃቂ አፅዳቂዎችም ብዛትም እንዲሁ።

New York Ban Ki Moon ruft Welt zu Solidarität mit Flüchtlingen auf
ምስል picture-alliance/AA/C. Ozdel

እዉነቱ ግን ተቃራኒዉ ነዉ።አፍሪቃና ደቡብ አሜሪካ ድምፅን በድምፅ በመሻሩ ሥልጣን ጨርሶ አልተወከሉም።እስያን የሚያክል ግዙፍ ክፍለ-ዓለም አንድ አባል ብቻ ነዉ ያላት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አመሠራረትን ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በተለይም ጦርነቱን በድል አድራጊነት ያጠናቀቁን መንግሥታት ከመራችዉ ከዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲካ ነጥሎ ማየት ሲበዛ ከባድ ነዉ።ስሙን የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት እንደዘበት አወጡት።ሩዘቬልት «የተባበሩት መንግሥታት» ያሉት፤ ጦርነቱን ኋላ በድል አድራጊነት ያጠናቀቁት 22 መንግሥታት ጠላቶቻቸዉን በጋራ ለመዉጋት ጥር 1942 ሲስማሙ ነበር።

የሩዘቬልት ሐሳብ ወይም ስያሜ ግን በጦርነቱ አሸናፊዎች ትብብር አላበቃም። የጦርነቱ ፍፃሜ ሲቃረብ ያ-ስም «ድርጅት» ታክሎበት አሮጌዉን የዓለም መንግሥታት ማሕበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንን) የሚተካዉ አዲስ ማሕበር መጠሪያ ሆነ።ዓላማዉም ከአስከፊ ጦርነት የወጣችዉ ዓለም ዳግም ከጦርነት እንዳትገባ መከላከል ወይም ሠላሟን ማስከበር ነበር።የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ሲፀድቅ ሩዝቬልትን የተኩት ፕሬዝዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን ያሉትም ይሕንኑ ነበር።

«እነዚሕ በዘር፤ በሐይማኖት፤በቋንቋ እና በባሕል በጣም የሚለያዩ ሐምሳ ሐገራት ከዚሕ ስምምነት መድረሳቸዉን የተጠራጠሩ ብዙዎች ነበሩ።እነዚሕ ልዩነቶች ግን በንድ የማይናወጥ ፅናት ምክንያት ተረስተዋል። ጦርነት የሚወገድበትን መንገድ በመፈለግ-ሥምምነት።»

ዓለም ግን ዛሬም በሰባ ዓመቷ ከጦርነት አልተላቀቀችም።እርግጥ ነዉ ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ድርጅታቸዉ የዓለምን ሠላም ለማስከበር ብዙ መጣሩን፤ ጦርነት፤ ግጭት፤ ዉጊያ ባሉባቸዉ አካባቢዎች በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ማዝመቱን ይናገራሉ።

Bildergalerie amerikanische Präsidenten
ምስል Getty Images

«የተባበሩት መንግሥታት የሠላም አስከባሪና የልዩ ፖለቲካዊ ተልዕኮ መሥሪያ ቤት ዛሬ ከ128 ሺሕ በላይ ሠላም አስከባሪ አሥፍሯል።ይሕን ያሕል ሐይል ከዚሕ በፊት ሠፍሮ አያዉቅም።ሠብአዊ ርዳታ የሚያቅርቡ ወገኖች ከዚሕ ቀደም ከተደረገዉ በበለጠ ሁኔታ ብዙ ችግረኞችን ለመርዳት እየሞከሩ ነዉ።አለመረጋጋትን ለማስወገድ የቀየስነዉ ሥልት ግን እጅግ እየተለጠጠ ነዉ።»

አንዳዶች እንደተቹት ዓለም-ብሎ ብያኔ አፍሪቃን፤ እስያን፤ ደቡብ አሜሪካን የሚያካትት ከሆነ ዓለም ድርጅቱ ከመመሥረቱ በፊትም ሆነ-በኋላ ከጦርነት ተለቅቃ አታዉቅም።ዛሬም ብሷል።ከፍልስጤም እስራኤሎች ዉጊያ፤ እስከ ሶማሊያ፤ ከደቡብ ሱዳን እስከ ዩክሬን፤ ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ እስከ ኢራቅ፤ ከአፍቃኒስታን እስከ ሶሪያ ከጦርነት፤ እልቂት፤ ፍጅት ሌላ-ሌላ ዜና የለም።

የሰባ ዓመቱ አዛዉንት ማሕበር መተዳደሪያ ደንብ ወይም ቻርተር ሲፀድቅ ብዙ የተጨበጨበለት መንግሥታት በጋራ ማሕበራቸዉ አማካይነት የዓለምን ሠላም ያስከብራሉ፤ ለድርጅቱ ደንብ ይገዛሉ በሚል ተስፋ፤ ተስፋዉን ባደነደነዉ ቃል-ኪዳን ምክንያትም ነበር።

«ይሕ መተዳደሪያ ደንብ ከጥቂት ዓመታት በፊት ኖሮን ቢሆን ኖሮ፤ ከሁሉም በላይ ገቢር ለማድረግ ፍቃደኝነቱ ቢኖር ኖሮ ዛሬ የሞቱ ሚሊዮኖች በሕይወት በኖሩ ነበር።ለወደፊቱ ደንቡን ገቢራዊ ለማድረግ ካልፈቀድን ዛሬ የሚኖሩ ሚሊዮኖች መሞታቸዉ የማይቀር ነዉ።ለዕቅድም፤ ለእርምጃም ጊዜ አለዉ።አሁን ግን ጊዜዉ የገቢራዊ እርምጃ ነዉ።»

Josef Stalin Franklin Roosevelt und Winston Churchill
ምስል picture alliance/Everett Collection

ሚሊዮኖች ዛሬም እያለቁ ነዉ።ብዙ ሚሊዮኖች እየተሰደዱ ነዉ።ከሁሉ የከፋዉ ያኔ ሐገር የነበሩ ብዙ ግዛቶች አንድም ፈርሰዋል፤ አለያም መንግሥት አልባ ቀርተዋል ወይም እብዙ ቦታ ተሰነጣጥቀዋል። ትሩማን ገቢራዊ ለማድረግ «ፈቃደኛ ካልሆንን» ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ፤ ደካሞች ከጣሱት ቀለል ሲል በማዕቀብ ሲበዛ በጦር ይቀጣሉ።ሐያላኑ መንግሥታት ግን ያንኑ ደንብ እንዳሻቸዉ ያደርጉታል።እንዳሻቸዉ ለማድረጋቸዉ ቀጪ፤ተቆጪ አይደለም ተቺም የላቸዉም።

ድርጅቱ ዓለም አቀፍ ማሕበር በመሆኑ ሕጉ የሚከበረዉ አባላቱ በተለይ ደግሞ ሐያል መንግሥታቱ ሕጉን በትክክል አክብረዉ ሲያስከብሩትና ሲተባበሩ ብቻ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ድርጅቱ ሐያል አባላቱን የሚያግባቡ ጉዳዮች ገቢር በማድረጉ ረገድ ተሳክቶለታል።

በርካታ ሐገራት ከቅኝ አገዛዝ እንዲላቀቁ ያደረገዉ አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።የሠብአዊ መብት ይዞታ እንዲሻሻል፤ ልማት እንዲስፋፋ፤ የሴቶች እኩልነት እንዲጠበቅ ብዙ ጥሯል።ምግብ፤ ጤና፤ ትምሕርት እንዲዳረስ ያደረገዉ ጥረትም አበረታች ዉጤት አሳይቷል።ሠላምን የማስከበር ዋና ሐላፊነቱ ን በተገቢዉ መንገድ ተወጥቷል ማለት ግን ያሳስታል።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞዉ የጀርመን አምባሳደር ሐንስ ሐይንሪሽ ሹማኸርም በዚሕ ይስማማሉ።ምክንያቱም ሹማኸር እንደሚሉት የድርጅቱ ድክመት ብቻ አይደለም-የአባላቱ በጣሙን የወሳኝ አባላቱ ልዩነት ወይም ጠብ ጭምር እንጂ።

«የድርጅቱን ሐላፊነቶች፤- በሚወስዳቸዉ እርምጃዎች ከፍሎ ማየት ያስፈልጋል።ልማትን በማበረታት፤ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግልን (በማገዝ) ሰብአዊ መብትን በማስከበሩ ረገድ ሐላፊነቱን ተወጥቷል።ሠላምና ፀጥታን ማስከበሩ ግን ብዙ ችግሮች አሉበት።ችግሮቹን የፈጠረዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነዉ ማለት አይችልም።አባል መንግሥታት እንጂ።አባላቱ ቀዉስ ሲፈጠር ብዙ ጊዜ የትብብር መንፈስን በማፍረስ እና ለችግሩ መፍትሔ እንዳይገኝ በማገድ ችግሩን ያባብሱታል።የቅርብ ምሳሌ የምትሆነዉ ሶሪያ ናት።»

UN-Sicherheitsrat Resolution zu Syrien Chemiewaffen 27.09.2013
ምስል Getty Images

ከድርጅቱ እኩል ያረጀዉ የፍልስጤም እስራኤሎች ጠብ የሩቅም-የቅርብም፤ የኢራቅ መወረር የመሐልም-የቅርብም፤ የዩክሬን ዉዝግብ-የቅርብ አብነት የማይሆኑበት ምክንያት የለም። ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ድርጅታቸዉ ከዘመኑ ጋር የሚጣጣም መዋቅር፤መርሕና አሠራር እንዲኖረዉ ማሻሻያ ያሉትን ነጥብ ለድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ አቀርበዋል።ጉባኤዉ ማሻሻያዉን መቀበል አለመቀበሉን ለማወቅ ጊዜ ያሻዋል።ቁም ነገሩ ግን ጉባኤዉ ማሻሻያዉን ተቀበለዉ አልተቀበለዉ አይደለም፤ ዋሽግተን፤ ሞስኮ ብራስልሶች-ምን አሉ እንደሁ እንጂ?

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ