1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ ዉሳኔ ፍልስጤምና እስራኤል

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2005

ጉባኤተኞች አልነፈጋቸዉም።ፍልስጤም መንግሥት ያልሆነ የድርጅቱ አባል እንዲሆን የቀረበዉን ሐሳብ፥-አንድ መቶ ሰላሳ-ስምት አባል ሐገራት በድጋፍ፥ ዘጠኝ በተቃዉሞ።አርባ-አንድ በተአቅቦ አፀደቁት።ራማላሕ-ጋዛ ዉድቅት ነዉ።ፍልስጤም ግን አልተኛም።ተደሰተ፥ ጨፈረ፥ፈነደቀ።

https://p.dw.com/p/16v5Q
Das Eingangstor der Vereinten Nationen (united nations, Nations Unies), aufgenommen am Montag (26.12.2011) in Genf. Foto: Fredrik von Erichsen
የተመድ አባል ሐገራት ባንዲራምስል Picture-Alliance/dpa

የዘመን ሒደት የእስራኤሎችን ሐያል-አይበገሬነት አስመስክሮ፣ የአረቦችን ሽንፈት፣የርስ በርስ መጠፋፋት ዉድቀትን አረጋግጦ፣ ከበቀደሙ ሐሙስ ሲደርስ የኒዮርኩ ታሪክዊ ዉሳኔ የታሪክ ገፁን የግልብጥ ገልጦ-እራሱን ደገመ።ወሳኙ ያኔም-አሁንም አንድ ድርጅት ነዉ።ጉዳዩ ተመሳሳይ።የድሮዉን ዉሳኔ ለመቀልበስ የፎከሩት በዘንድሮዉ ዉሳኔ የመፈንደቃቸዉ፣ በያኔዉ ዉሳኔ የቦረቁት ያሁኑን የማጣጣላቸዉ ተቃርኖ እንጂ፥ የስልሳ-አምስት ዓመቱን አስተምሕት በዜሮ የማጣፋቱ ዚቅ።ያኔ የተወሰነዉ እንዲወሰን የሕዝብ መብት፧ ነፃነትን የማስከበር ፍትሐዊነትን የመሟገቻ ሰበብ፣ ሐብት-ጉልበታቸዉን ማስፈራሪያ ዱላ ያደረጉት፣ ያሁኑን የመቃወማቸዉ ግጭት እንጂ ሥጋቱ።ዉሳኔዉ መነሻ፣ ዳራዉ ማጣቃሻ፥ ተቃርኖ ግጭቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ሕዳር 29 1947 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ቅዳሜ ነዉ።ኒዮርክ ቅዝቃዜዉ ጨምሯል።ቀኑም ተገባዷል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፍልስጤም ለሁለት እንዲገመስ ወሰነ።በዉሳኔዉ መሠረት ግዛቱ ለሁለት ተገምሶ፥-በአንደኛዉ ገሚስ አይሁዶች፥ በሁለተኛዉ አረቦች መንግሥት ይመሠርታሉ።ታሪካዊቷ የእየሩሳሌም ከተማ በልዩ መስተዳድር ትገዛለች።

እየሩሳሌም።ሌሊቱ ተጋምሷል።አረብ አይሁድ ግን ተፋጠዋል። ዉሳኔ ቁጥር 181 እዝባር ሁለት፥ በሰላሳ-ሰወስት ድጋፍ፥ በአስራ-ሰወስት ተቃወሞ። በአስር ድምፀ ተአቅቦ መፅደቁን ሲሰሙ-አይሁዶች ቦረቁ።የሁለት ሺሕ ዘመን ነፃ ሐገር-የመመሥረት ሕልማቸዉ እዉን ሆነ።የፍልስጤሞች ምኞት ተስፋ ግን ተነነ።አረብ በገነ።

ነጋ።ሕዳር ሰላሳ፥በድፍን አለም የተበተነዉ አይሁድ ሲፈነጥዝ፥ ሲቦርቅ አድሮ ለመዋል ታድሟል። እየሩሳሌም ዉስጥ ግን ስድስት አይሁዶች ተገደሉ።ብዙ ንብረታቸዉ ጠፋ።የዳዊት ኮኮብ ምልክት ያላት ባንዲራ ግን ጋዜጠኛዉ እንዳለዉ ትዉለበለባች።

ግንቦት-ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት። የእስራኤሌ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ «ከ1967 በፊት የነበሩት ሐምሳ-ዓመታት በሙሉ የግጭት ዓመታት ነበሩ» አሉት ሥለ ፍልስጤም-እስራኤሎች ግጭት ለጠየቃቸዉ ጋዜጠኛ።«ታዲያ አሁን ምንድነዉ አዲሱ» አከሉ።ኔታንያሁ ያኔ አልተወዱም። ዘንድሮ እንዳሉት ግን ግጭት የማያጣዉያ ምድር፥ ያኔ አዲስ ታሪክ ታወጀበት። አዲስ ጦርነት አረበበበት።

ሕዳር-29 2012 ሐሙስ።ኒዮርክ መሽቷል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ዉሳኔ ቁጥር 181/2 ያሳለፈበትን ስልሳ-አምስተኛ ዓመት ሌላ-ዉሳኔ በማፅደቅ እንዲዘክረዉ የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር ፕሬዝዳት ማሕሙድ አባስ ተማፀኑ።በሳቸዉ ቋንቋ ለፍልስጤሞች ነፃነት የልደት ሰርቲፊኬት ጠየቁ።

«ክቡራትና ክቡራን፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለፍልስጤም መንግሥት የመሆን እዉነታ እንዲያዉቅ እና የልደት ሰርቲፊኬት እንዲሰጠን እማፀናለሁ።»

ጉባኤተኞች አልነፈጋቸዉም።ፍልስጤም መንግሥት ያልሆነ የድርጅቱ አባል እንዲሆን የቀረበዉን ሐሳብ፥-አንድ መቶ ሰላሳ-ስምት አባል ሐገራት በድጋፍ፥ ዘጠኝ በተቃዉሞ።አርባ-አንድ በተአቅቦ አፀደቁት።ራማላሕ-ጋዛ ዉድቅት ነዉ።ፍልስጤም ግን አልተኛም።ተደሰተ፥ ጨፈረ፥ፈነደቀ።

«በጣም እኮራለሁ፥ ፍልስጤም በመሆኔ ኮርቻለሁ።እኒሕ ፕሬዝዳት ይወክሉኛል።ያንፀባረቁት ሕልማችንን ነዉ።» አለች ወጣቷ።

ሰዉዬዉ ቀጠሉ፣-«ጥሩ ይመስለኛል። መንግሥት እንፈልጋለን።እንደተቀረዉ ዓለም በራሳችን መንግሥት መተዳደር እንፈልጋለን።ሁሉም በየራሱ መንግሥትና ሐገር ነዉ-የሚኖረዉ። እኛ ብኛ ነን የሌለን።»

ሴዮዋ አከሉበት፥-«ፍፁም ጠቃሚ እርምጃ ነዉ።ለረጅም ዘመን ጠብቀናል።ይሕን ዕለት ከስልሳ ዓመት በላይ ጠብቀናል።»

ለአይሁዶች ግን ዉሳኔዉ አናዳጅ፥ለሰላም የማይፈይድ፥ የፍልስጤሞች ደስታም እሳቸዉ እንዳሉት ባዶ ጩኸት ነዉ።

«ምንም በሌለ ነገር ብዙ ይጮኻሉ።መነጋገር አይፈልጉም፥ መደራደር አይፈልጉም።እኛ እስራኤሎች መነጋገር እንፈልጋለን።እነሱ ያንን ሊያሳዩን ነዉ የሚሹት።ሌለኛዉ ቀጠሉ ዉሳኔዉን ታላቅ ቧልት፥ እያሉ።

«ፍልስጤሞች፥ ፍልስጤም ይሕቺ ናት ብለዉ ለተቀረዉ ዓለም ማሳየት ከቻሉ፥ ሐገራቸዉን ይገባናል የማለት መብት አላቸዉ።ይሕ ቀን ታላቅ ቀልድ ነዉ።»

የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መንግሥት ቃል አቀባይ ማርክ ሬጌቭ ደግሞ የእየሩሳሌሙ ነዋሪ ቧልት ያሉትን ዉሳኔ፥ ድራማ በማለት ደገሙት።

«ወደፊት የሚያጉዘን ብቸኛዉ መንገድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉስጥ ትርጉም የለሽ ቲያትር ማሳየት አይደለም።ብቸኛዉ መንገድ እስራኤልና ፍልስጤሞች ችግሮቻቸዉን በጋራ ለማስወገድ ትርጉም ያለዉ የሰላም ድርድር ማድረግ ነዉ።እና የምናቀርበዉ ይሕንን ነዉ።ቀጥታ፥ የፊት ለፊት የሰላም ድርድር።»

ሕዳር ተገባዷል 1947 የዓለም አቀፉ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፍልስጤም ለሁለት እንዲገመስ በተረቀቀዉ ሐሳብ ላይ ድምፅ የሚሰጥበት ዕለት ተቃርቧል።የአረብ አይሁዶችን ግጭት-ዉዝግብ፣ የብሪታንያን ሁለቱን የማላተም መርሕ የሚያዉቁት የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆርጅ ካትሌት ማርሻል ጁኒየር ሐገራቸዉ ተጣድፋ አቋም እንዳትይዝ፥ መምከር ማሳሰባቸዉን ፕሬዝዳንት ሐሪ ኤስ ትሩማን አልወደዱትም።

የዚያን ቀንም ፕሬዝዳንቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩን አልፈዉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሐገራቸዉን አምባሳደር ሔርሼል ቬስፓሲያን ጆንሰንን አስጠርተዉ፣ፍልስጤምን «እሁለት የመክፈሉ ረቂቅ እንዲፀድቅ ካለደረግሕ የምንከፍለዉ ዋጋ አይተመንም» በማለት አስጠነቀቋቸዉ።


አምባሳደር ጆንሰን የማይታጠፈዉን ትዕዛዝ ለማስፈፀም ረቂቁን ይቃወማሉ ተብለዉ የሚጠረጠሩ መንግሥታት ተወካዮችን እያደኑ «አይሁዶች መንግሥት እንዳያቋቁሙ መቃወም የሕዝብን ፍላጎት፣ መብት፣ ነፃነትን፣ መርገጥ፣ ፍትሕ ርዕትዕትን መደፍለቅ ነዉ-እያሉ ያግባቡ፣ ያንገራገሩትን ያስፈራሩ ገቡ።

ሕዳር ሃያ-ስምንት ሁለት ሺሕ አስራ ሁለት።ሮብ።የጆንሰን የመብት፥ ነፃነት ሙግት ክርክር ላሁኗ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ለሒላሪ ክሊንተን የሞተ ጉዳይ ነዉ።በሮሞች፣ በቱርኮች፣ በእንግሊዞች ሲረገጡ ዘመነ-ዘመናት ያስቆጠሩት፣ ስልሳ አምስት አመታት በእስራኤሎች ለተጨቆኑት ፍልስጤሞች ዓለም አቀፉ ድርጅት የነፃነት አይደለም መንግሥት ያልሆነ እዉቅና መስጠቱ ክሊንተን ለሚወክሏት ዩናይትድ ስቴትስ ለሕዝብ-ሠላም ነፃነት አፍራሽ ነዉ።


«በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉስጥ ምንም ቢደረግ ይሕ መንግሥት፥ ይሕ ፕሬዝዳት፥ በርገጥኝነት እኔ ራሴ የምንደግፈዉ ዉጤት እንዲመጣ አይረዳም።ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ብቸኛዉ መንገድ ቀጥታ ድርድርን መቀጠል ነዉ።ለዚሕ የተመቻቸ ድባብ እንፈልጋለን።እና ሁለቱም ወገኖች ትርጉም ወዳለዉ ሰላማዊ ድርድርና ወደ መፍትሔ ለመመለስ የሚደረገዉን ጥረት ከሚያነቅፍ እርምጃ እንዲታቀቡ አሳስበናል።»

እርግጥ ነዉ ክሊንተን እንዳሉት ለፍልስጤሞች ነፃነት ቁልፉ አንድም ዋሽግተን አለያም እየሩሳሌም እንጂ-አባስ እንዳሉት ኒዮርክ አይደለም።ጠቅላይ ሚንስትር ይትሳቅ ራቢን እና ሊቀመንበር ያሲር አረፋት በ1993 የሠላም ዉል ተፈራራሙ ከተባለ ወዲሕ ሥለ ሰላም ድርድር ዉይይት፥ ያልተወራ፥ ያልተነገረበት ዘመንም የለም።ጦርነት እንጂ ሰላም ግን የለም።ለፍልስጤሞች እልቂት ግድያ-እንጂ ነፃነት የለም።

የዋሽግተን-እየሩሳሌም መሪዎች ለአሳዛኙ የእልቂት ግድያ ዑደት፥ በዉጤት አልባዉ ድርድር ባዶ ተስፋ ለተሰላቸዉ ዓለም፥ ተስፋ ለቆረጠዉ ፍልስጤማዊ መልስ ሊሰጡ በተገባ ነበር።ማሕሙድ አባስ ዓለም አቀፉን ድርጅት «የልደት ሰርቲፊኬት» ሲጠይቁ፥-ዉሳኔዉ የሕዝባቸዉን የዘመነ-ዘመናት የነፃነት ፍላጎት ምኞች እንደማያሟላ አላጡም።

ግን የመስተዳድራቸዉን ሕልዉና ለማቆየት ለሕዝባቸዉ ብዙ ያልሰለቸ አዲስ ተስፋ መስጠት ነበረባቸዉ።ሰጡት።ዉሳኔዉንም ታሪካዊ አሉት።

«አሁን መንግሥት አለን።ፍልስጤሞች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታሪካዊ ድል አገኙ። ለፍልጤም የሐገርነት እዉቅና መሰጠቱ ሁሉንም ነገር ይቀይረዋል።ድላችሁ የጦርነት፥ የቅኝ ገዢዎችና ግዛትን በጉልበት የሚይዙ ሐይላትን መጓጎጡን ግን እንዳትዘነጉት።»

ድጋፍም በርግጥ ገበዩበት።ሐምሌ-1945 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ ፀደቀ።ድርጅቱ በይፋ ተመሠረተ።በአሜሪካኖች ሐሳብ፥ በአሜሪካኖች ግፊት፥ጥረት የተመሠረተዉ የአዲሱ ድርጅት የክብር እንግዳ-አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳት ነበሩ።ሐሪ ኤስ ትሩማን

ሐምሳ ሐገራትን ለወከሉት ጉባኤ-አሉም።«ከጥቂት ዓመታት በፊት ይሕ ደንብ ኖሮን ቢሆን ኖሮ፣ ከሁሉም በላይ ገቢራዊ የማድረጉ ፍላጎት ቢኖረን ኖሮ እስካሁን የሞቱት ሚሊዮኖች ዛሬ በሕይወት በኖሩ ነበር።ለወደፊቱ ደንቡን በፍቃዳችን ከጣስነዉ ደግሞ ዛሬ በሕይወት ያሉ ሚሊዮኖች መሞታቸዉ ምንም አያጠራጥርም።»

የዚያን ግዙፍ ድርጅት ጠንካራ ሕግ የጣሰዉ፥ ለመጣስ አቅም-ጉልበቱ ያለዉ መንግሥት ማን-ማንነት ብዙ አነጋጋሪ፥ አከራካሪ ነዉ።ሕጉ ከፀደቀበት እስካሁን በተቆጠረዉ ስልሳ-ሰባት ዘመን ግን በየስፍራዉ በተጫረዉ ጦርነት ሚሊዮነ-ሚሊዮናት ማለቃቸዉ ግን ሐቅ ነዉ።

ዙፉ ድርጅት ባለፈዉ ሐሙስ ያሳለፈዉ ዉሳኔ የግጭት-ጦርነት ታሪክን በግጭት ጦርነት ታሪክ ለሚደግመዉ ለመካከለኛዉ ምሥራቅ ሠላም የሚተክረዉ መኖር አለመኖሩ ወደፊት የሚታይ ነዉ።ዉሳኔዉን በመቃወም ግን የዚያ ድርጅት መስራች፥ሐያል-ታላቅ ሐገር ድምፅ በድምፅ የመሻር ሥልጣን ካላቸዉ ሐገራት ብቸኛዋ ሆናለች።ዩናይትድ ስቴትስ።

አምባሳደር ሱዛን ራይስ ሐገራቸዉ ከአንድ መቶ ሰላሳ-ስምት የዓለም ሐገራት ለመነጠሏ ምክንያት የሚሉት አላጡም።

«የዛሬዉ ተገቢ ያልሆነ አፍራሽ ዉሳኔ ወደ ሰላም የሚያጉዘዉን መንገድ ለማደናቀፍ ተጨማሪ እንቅፋት አስቀምጧል።ዩናይትድ ስቴትስ የተቃወመችዉም ለዚሕ ነዉ።»

የ1949ኙ ዉሳኔ እስራኤልና ፍልስጤሞች ሁለት መንግሥት ይመስርቱ የሚል ነበር።ፈረንሳይ ዉሳኔዉን ደግፋለች።አምባሳደር ዤራልድ አራሁድ እንዳሉት ሐገራቸዉ ዉሳኔዉን የደገፈችዉ ሁለት መንግሥታት ይመሥረቱ የሚለዉን ሐሳብ ገቢር ለማድረግ ይጠቅማል ብላ በማመኗ ነዉ።

«ፈረንሳይ የሁለት መንግሥታት መፍትሔን ደግፋ ድምፅ ሰጥታለች። ሁለት መንግሥታት ለሁለት ሕዝቦች የሚለዉን።እስራኤልና ፍልስጤም ዓለም አቀፍ እዉቅና ባለዉ ድንበር፥ በሰላምና በፀጥታ ጎን ለጎን ይኖሩ የሚለዉን ሐሳብ በመደገፍ ፈረንሳይ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ፊት ስትጥር ቆይታለች።ዛሬም የሰላም ሒደቱ የገጠመዉን እንቅፋት ለማስወገድ (ይረዳል) በሚል ሐሳቡን ደግፋለች።»

ሩሲያምና ቻይናም ደግፈዉታል።ብሪታንያ ድምፅዋን አቅባለች።ከአዉሮጳ ትላልቅ ሐገራት ድምፅዋን ያቀበችዉ ሌለኛዋ ሐገር ጀርመን ናት።ጀርመን ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት ሥለ አይሁዶች ካላት መጥፎ ታሪክ ጋር ሲተያይ ድምፅዋን ማቀብዋ የሚበዛባት ነዉ።የጀርመኑ አምባሳደር ፔተር ቪቲሽ እንዳሉት ደግሞ ወደ ድርድሩ መንገድ መመለሻዉ ጊዜ አሁን አሁን።

«እዉነተኛ ድርድር የሚቀጥልበትን መንገድ መፈለጊያዉ ጊዜ አሁን ነዉ።ለዚሕ ስኬት የድርሻችንን እንወጣለን።»

የእስራኤል ካቢኔ ዉሳኔዉን ዉድቅ አድርጎታል።እስራኤል በሐይል በያዘችዉ የፍልስጤም ግዛት ተጨማሪ የአይሁድ ሠፈራ መንደሮችን ለመገንባት ወስናለች።ከዚሕ ቀደም በተደረገዉ ስምምነት መሠረት ለፍልስጤም ራስ ገዝ ማስተለለፍ መስጠት የሚገባትን የቀረጥ ገንዘብም አቋርጣለች።ሰላም ይወርድ ይሆን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

GettyImages 157171574 Palestinians celebrate in the West Bank city of Ramallah on November 29, 2012 after the General Assembly voted to recognise Palestine as a non-member state. The UN General Assembly on Thursday voted overwhelmingly to recognize Palestine as a non-member state, giving a major diplomatic triumph to president Mahmud Abbas despite fierce opposition from the United States and Israel. AFP PHOTO / ABBAS MOMANI (Photo credit should read ABBAS MOMANI/AFP/Getty Images)
ፍልስጤም ደስታምስል AFP/Getty Images
Palestinian President Mahmoud Abbas holds a letter requesting recognition of Palestine as a state as he addresses the 66th session of the United Nations General Assembly, Friday, Sept. 23, 2011 at UN Headquarters. (AP Photo/Mary Altaffer)
አባስምስል AP
Israel's Prime Minister Benjamin Netanyahu arrives to a news conference in Jerusalem October 9, 2012. Israeli Prime Minister Netanyahu called on Tuesday for an early election, seeking to strengthen his political position after signalling that any military action against Iran could be months away. REUTERS/Ronen Zvulun (JERUSALEM - Tags: POLITICS)
ኔታንያሁምስል Reuters
Palestinian president Mahmud Abbas addresses the crowds as Palestinians celebrate his successful bid to win U.N. statehood recognition in the West Bank city of Ramallah on December 2, 2012. President Abbas returned from New York to the West Bank after winning upgraded UN status for the Palestinians on November 29, telling cheering crowds: 'Yes, now we have a state.' AFP PHOTO/ABBAS MOMANI (Photo credit should read ABBAS MOMANI/AFP/Getty Images)
ረመላሕምስል ABBAS MOMANI/AFP/Getty Images
Palestinians wave their national flag as they celebrate their successful bid for UN non-member observer state status in the West Bank city of Ramallah on December 2, 2012. Palestinian president Mahmud Abbas returned to the West Bank after winning upgraded UN status for the Palestinians, telling cheering crowds: 'Yes, now we have a state.' AFP PHOTO/AHMAD GHARABLI (Photo credit should read AHMAD GHARABLI/AFP/Getty Images)
ረመላሕምስል AHMAD GHARABLI/AFP/Getty Images

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

























ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ