1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ኹኔታ ላይ ተወያየ

ዓርብ፣ ነሐሴ 21 2013

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከትግራይ ክልል ጋር የተገናኘውን ግጭትን በተመለከተ ትናንት ባደረገው ውይይት ሁሉም አካላት ተኩስ አቁመው ወደ ውይይት እንዲመጡ አሳስቧል። በውይይቱ የቻይና፣ የሩስያ እና የሕንድ አምባሳደሮች ለፀጥታው ምክር ቤት ባሰሙት ንግግራቸው፦ በአብዛኛው የኢትዮጵያን አቋም አንጸባርቀዋል።

https://p.dw.com/p/3zZCX
UN Hauptquartier in New York
ምስል picture-alliance

ቻይና፣ ሩስያ እና ሕንድ ጣልቃ ገብነትን ተቃውመዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከትግራይ ክልል ጋር የተገናኘውን ግጭትን በተመለከተ ትናንት ባደረገው ውይይት ሁሉም አካላት ተኩስ አቁመው ወደ ውይይት እንዲመጡ አሳስቧል። በውይይቱ የቻይና፣ የሩስያ እና የሕንድ አምባሳደሮች ለፀጥታው ምክር ቤት ባሰሙት ንግግራቸው፦ በአብዛኛው የኢትዮጵያን አቋም አንጸባርቀዋል። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲከበርም አጽንዖት ሰጥተዋል።  

ዩናይትድ ስቴትስ ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥሪያ ቤት የጸጥታው ምክር ቤት ስለ ኢትዮጵያ ሲመክር ለስምንተኛ ጊዜ ነው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዚህ ለተሳታፊዎች ባሰሙት ንግግር፦ «ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ እየገቡ ልወስን የሚሉ ማናቸውንም ኃይላት እንደማትቀበል» አጽንዖት ሰጥተዋል። 

«የፀጥታው ምክር ቤት እውነታ ማጣራቱ ላይ በተቃራኒው የተዛቡ መረጃዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ» ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። «ኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖት፤ በነገድ ወይንም በሌላ ማናቸውም መንገድ ማግለል የለም። እኛ ዝቅተኛ ሥነ ምግባር ያለን ሕዝብ አይደለንም። እሴት ያለን ሕዝብ ነን» ሲሉም አስረግጠዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬሽ በበኩላቸው፦ «በጦርነቱ የሚሣተፉ ኃይላት በሙሉ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ» ጥሪ አቅርበዋል። «በጣም ጠቃሚ የሆነው የኢትዮጵያ አንድነት እና የቀጠናው መረጋጋት አደጋ ውስጥ ገብቷል።» ያሉት ዋና ጸሐፊው፦ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ የነበረ ቢሆንም የሕወሓት ኃይሎች ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ጥቃት ማድረሳቸውን ብሎም አጠቃላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ አለመቻሉንም ተናግረዋል። «ሰኔ 21 የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል ከመቀሌ ቢያስወጣም ሁሉን ወዳቀፈ የተኩስ አቁም ስምምነት ግን አላመራም» ብለዋል። አደገኛ ንግግሮች እና ጎሳን የሚመለከቱ ጉዳዮች የሀገሪቱን የማኅበራዊ ትስስር እየጎዳ መሆኑንም ጠቁመዋል። የሰብአዊ ኹኔታው ተባብሶ ሚሊዮኖችን ለችግር መዳረጉንም በማመልከት «ሁሉም አካላት» በቀጥታ ወደ ተኩስ አቁም እንዲገቡ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ አንድነት እና የቀጠናው መረጋጋት ወሳኝነት ላይ አጽንዖት የሰጡት አንቶኒዮ ጉተሬሽ ወታደራዊ መፍትኄ አለመኖሩንም ተናግረዋል።

ቻይና፦ «ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ብሔራዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት ሊደግፍ ይገባል» ብላለች።  የኢትዮጵያ ለተኩስ አቁም ያደረገችውን ጥረት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊደግፍ እንደሚገባም አሳስባለች። የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊያከብሩ ይገባል ያለችው ቻይና፤  «በሰብአዊነት ድጋፍ ግን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን» አጥብቃ እንደምትቃወም አሳስባለች።

ኬንያ እና ሕንድ ለትግራይ ክልል ግጭት መፍትኄ በኢትዮጵያውያን መሪነት መምጣት እንዳለበት ተናግረዋል። ሕወሃት ከትግራይ ክልል ወጥቶ ግጭቱን ማስፋፋቱ እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ይበልጥ ያጋልጣል ብለዋል የኬንያ ተወካይ። ውይይት እንደሚያሳስፈልግ በመጥቀስም ለዚያ ደግሞ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት «ለቀጥታ መገናኘት እና ውይይት» ሕወሓትን አሸባሪ ማለቱን ለማንሳት መዘጋጀት እንዳለበት የኬንያው ተወካይ አክለው ተናግረዋል። 

Symbolbild I United Nations Emblem
ምስል John Angelillo/UPI/newscom/picture alliance

ሩስያ በበኩሏ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በተቻለ ፍጥነት ውይይት መጀመር እንዳለበት እንደምትስማማ ገልጣለች። ኾኖም ማንኛውም የውጭ ድጋፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፤ የግዛት ምልዕነት ያከበረ፤ እና የፖለቲካ ነጻነት በጠበቀ መልኩ ሊሆን ይገባል ስትል አሳስባለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ሰኔ ወር ውስጥ አድርጎት የነበረው የተናጠል የተኩስ አቁም በህወሓት ኃይሎች መጣሱ እንዳሳዘናትም ሩስያ ዐስታውቃለች። «ኹኔታውን ዝቅ አድርጎ መመልከት እና የተናጠል የማዕቀብ ርምጃዎችን ጨምሮ በሕዝብ የተመረጠ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደር ግጭቱን የሚያባብስ መሆኑን መረዳት ይጠቅማል» ብላለች። ከዚህም ሌላ ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ፤ ውይይቱ መመራት ያለበትም «በራሷ በኢትዮጵያ» መሆን  ይገባዋል ብላለች ሩሲያ።
 «ኢትዮጵያ ውስጥ የተካኼደው የሰኔው ምርጫ የፌዴራሉ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብን አንድነት ማስጠበቅ እንደሚችል አሳማኝ ማረጋገጫ ይሰጣል» ስትልም አቋሟን አሳውቃለች። ኹኔታዎቹን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሳቸው ወደ ቀድሞው ለመመለስ እንደሚችሉ እና በአጠቃላይ ሀገሪቱን ወደ ትክክለኛው የልማት ጎዳና መመለስ የመመለስ አቅሙ እንዳላቸው እምነት እንዳላትም አመልክታለች ብለዋል። 

የአየርላንድ እና የፈረንሳይ ተወካዮች በበኩላቸው፦ ሕወሓትም የአማራ ኃይላትም «ከያዟቸው ቦታዎ» እንዲወጡ «ሁሉን አካታች ውይይት እንዲጀመር» ጠይቀዋል። የሁለቱ ሃገራት ተወካዮች ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉ የፈጠረባቸውን ስጋትም ገልጠዋል። ሕንድ እና ኬንያ ለግጭቱ መፍትኄ መምጣት ያለበት በኢትዮጵያውያን መሪነት ነው የሚል አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል። በተመድ የሰብአዊ ድጋፍ መርኅ መሠረት ጥረቱ በአስቸኳይ መቀላጠፍ እንደሚያስፈልገውት የገለጡት የሕንድ ተወካይ፦ «ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማግኘት የምትችላቸውን ድጋፎች ሁሉ ልታገኝ ያስፈልጋል» ብለዋል። 

በምክር ቤቱ የዩናይትድ ስቴትስ ተወካይ በሁለቱ ወገናት ውጊያ መቀጠሉ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። «የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድር ለቀረበለት ሐሳብ በጎ ምላሽ አልሰጠም» ብለዋል። ወታደራዊ ዘመቻውን ያጧጧፈ ያሉት ሕወሃት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መግባቱ «በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት በመሆኑ በአስቸኳይ መቆም አለበት» ሲሉም ተናግረዋል። በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ተደርጎ ለሰብአዊ  ድጋፍ ያልተገደቡ መንገዶች እንዲከፈቱም ጥሪ አድርገዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ