1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ ግብና የሴቶች ጤና

ማክሰኞ፣ ጥር 21 2005

ከሰሀረ በስተደቡብ በሚገኙ ሀገሮች ከእርግዝና ጋ በተገናኘ የጤና እክል በእያንዳንዷ ቀን 452 ሴቶች ህይወት ያልፋል። በሰዓት ደግሞ 18 ሴቶች። እሁድ ዕለት የሁለት ቀናት ጉባኤያቸዉን የጀመሩት የአፍሪቃ ኅብረት መሪዎች አፍሪቃ ዉስጥ በእርግዝናና ወሊድ ወቅት የሚከሰት ሞትን

https://p.dw.com/p/17T3G
ምስል Getty Images

ለመቀነስ የጀመሩትን ጥረት እንደሚያጠናክሩ ተገልጿል።

በጎርጎሮሳዊዉ 2009ዓ,ም ነዉ የአፍሪቃ ኅብረትና የተመ የስነህዝብ የገንዘብ ተቋም UNFPA አፍሪቃ ዉስጥ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የተጀመረዉ ዘመቻ የሚያፋጥን በእንግሊዝኛ ምህፃሩ CARMMA የተሰኘዉን እንቅስቃሴ ይፋ ያደረገዉ። ዓላማዉ የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ማስፋፋትና አፍሪቃ በአምዓቱ የልማት ግብ መሠረት ያለዉን በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥር ወደሶስት አራተኛ የመቀነስ እቅዱን ማሳካት ነዉ። ምንም እንኳን የአፍሪቃ መሪዎች በዚህ ረገድ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነታቸዉን ዳግም ቢያድሱም እዉነታዉ የሚያመለክተዉ ግን አሁንም ከታሰበዉ ለመድረስ ጊዜ እንደሚጠይቅ ነዉ።

Symbolbild schwangere Frau eine Schwangere Baby Babybauch PID Schwangerschaft
ምስል Fotolia/Karen Roach

በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተዉ በበለፀጉ ሀገሮች ከሚታየዉ ይበልጥ ከሰሀራ በስተደቡብ በሚገኙ የአፍሪቃ ሀገሮች ሴቶች በእርግዝ እና በወሊድ ወቅት በሚያጋጥሙ እክሎች መቶ ጊዜ እጥፍ ህይወታቸዉ ያልፋል። በወሊድ ጊዜ የበርካታ እናቶች ህይወት እንደሚያልፍባቸዉ ከተጠቀሱ ከአስር ሀገሮች ስምንቱ የሚገኙት እዚያዉ አፍሪቃ ዉስጥ መሆኑን ያመለክታል።

ግንባር ቀደም የተባሉት ደግሞ ናይጀሪያና ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ናቸዉ። ቤኒን በጤና ጣቢያዎችና ሃኪም ቤቶች መረጃዎችን በማሰባሰብ የነፍሰጡር እናቶችን ህይወት ለመታደግ ጥረቷን ማጠናከሯ ተገልጿል። ማላዊ፤ ታንዛኒያና ዛምቢያ ደግሞ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችን በስፋት ማዳረስ ከተሳካላቸዉ ሀገሮች ተርታ ተሰልፈዋል። እንዲያም ሆኖ ዘገባዎች እንደሚሉት በተለያዩ አህጉሮች በስፋት ከሚከሰተዉ የእናቶች ሞት 57 በመቶ የሚሆነዉ የሚደርሰዉ አፍሪቃ ዉስጥ ነዉ።

የእናቶችን ህይወት ለአደጋ የሚያደርሰዉ በወሊድ ጊዜ ከፍተኛ የደም መፍሰስ፤ በባክቴሪያ መመረዝ፤ በእርግዝና ወራት የደም ግፊት ከፍ ማለት እንዲሁም ጥንቃቄ የጎደለዉ ዉርጃ መሆናቸዉን ነዉ UNFPA የሚያመለክተዉ።

እስካሁን የእናቶችን ሞት በመቀነሱ ረገድ የተመድን የአምዓቱን ግብ ያሳካችዉ ሀገር ኢኳቶሪያል ጊኒ ብቻ መሆኗ ነዉ የሚነገረዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ